ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የተስፋ ነጋዲያንን ያስታወሱበትን የታኅሳስ ወር የጸሎት ሐሳብ ይፋ አደረጉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለታኅሳስ ወር እንዲሆን በማለት ያዘጋጁትን የጸሎት ሐሳብ በዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ይፋ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ወራዊው የጸሎት ሃሳባቸው፥ በመጪው የጎርግሮሳውያኑ 2025 የኢዮቤልዩ ዓመት እያንዳንዳችን የተስፋ ተጓዦች ለመሆን መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“መጪው የኢዮቤልዩ በዓል በእምነታችን እንድንጠነክር፣ በሕይወታችን ውስጥ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናውቅ እና ወደ ክርስቲያናዊ የተስፋ ተጓዥነት ለመለወጥ እንዲረዳን እንጸልይ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከብርሃነ ልደቱ በዓል ቀጥሎ የሚገባው የአውሮፓውያኑ 2025 የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት ከመጀምሩ በፊት ለታኅሳስ ወር እንዲሆን ያዘጋጁትን የጸሎት ሃሳብ በዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ይፋ አድርገዋል።

በዓለማችን ውስጥ እየደረሰ ባለው መከራ እጅግ ያዘኑት ቅዱስነታቸው፥ የሰው ልጅ ትልቅ ተስፋ እንደያስፈልገው ገልጸው፥ “ክርስቲያናዊ ተስፋ ሕይወታችንን በደስታ የሚሞላ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” ብለው፥ የሕይወታችን መሪ እንደሆነም ተናግረዋል።

“ተስፋን አጥብቀን መያዝ አለብን” በማለት ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ እግዚአብሔር ሕይወታችንን በተስፋ እንዲሞላው፣ በዙሪያችን ላሉ ሰዎች ሁሉ የተስፋ ስጦታዎች እንድንሆን ክርስቲያኖችን በሙሉ ጋብዘዋል።

ሕይወትን ከሚሰጠን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን ግንኙነት ለማወቅ እርስ በርሳችን መረዳዳት እንደሚገባ እና ያንን ሕይወት በደስታ ለመቀብል እንደ ተስፋ ምእመናን ጉዞ መጀመር እንዳለብን አሳስበው፥ “ወደ መጪው የኢዮቤልዩ ዓመት መግባት ደግሞ የሕይወታችን ቀጣዩ ደረጃ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ቤተ ክርስቲያን የኢዮቤልዩ በዓልን ለማክበር በምትዘጋጅበት በዚህ ወቅት ካቶሊካዊ ምዕመናን የተስፋ ነጋዲያን እንዲሆኑ መጠራታቸው የ2025 የቅዱስ ዓመት መሪ ሃሳብ እንደሆነ በመግለጽ፥ “ተስፋ ምን ጊዜም ቢሆን ፈጽሞ አያሳዝንም” ሲሉ አስረድተዋል።

በሕይወት ፈተናዎች ውስጥ የተስፋ መልዕክት ማስተላለፍ
ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ከታኅሳስ ወር የጸሎት ሃሳብ ዓላማ ጋር ይፋ ባደረገው መግለጫ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክት የተዘጋጀው በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር መሆኑን አስታውቋል።

የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በከፍተኛ ደረጃ በተስፋፋበት ወቅት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ብቻቸውን ሆነው ለመላው ዓለም እና ለሮም ከተማ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ በታላቅ ፈተናዎች መካከል የሚገኝ የሰው ልጅ ደካማነት ለመግለጽ ማዕበል የሚያናውጣትን ጀልባ በመጠቆም የወንጌል ዘይቤን መጠቀማቸውን አስታውሷል።

በዓለማችን ውስጥ የተለያዩ አገራት በግጭት እና በጦርነት በሚገኙበት በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን የራሷን ተስፋ የማጠናከር እና ለዓለም የማካፈል ሥራ አለባት። በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንዳሉት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁሉም ክርስቲያኖች ምንም ዓይነት ውዝግብ እና ችግር ቢያጋጥማቸው ተስፋ ምመቁረጥ እንደማይገባ ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ለወጣቶች ታስቦ በተዘጋጀ የቪዲዮ መገናኛ በኩል ባስተላለፉት ጥሪ፥ ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የማያስከፋ የተስፋ መልዕክት እንዲቀበል እንጸልይ” በማለት አሳስበዋል።

 

10 December 2024, 16:23