የኢስቶኒያ  ሊቀ ጳጳስ የነበሩ አቡነ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች የኢስቶኒያ ሊቀ ጳጳስ የነበሩ አቡነ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በሰማዕትነት የተገደሉ የኢስቶኒያ ሊቀ ጳጳስ የአቡነ ኤድዋርድ ብጽዕናን አጸደቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በሶቭየት ኅብረት አገዛዝ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1942 ዓ. ም. በሰማዕትነት የተገደሉት የጀርመናዊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች ብጽዕናን አጽድቀዋል።ኢየሱሳዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤድዋርድ በወቅቱ ኢስቶኒያ ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርክርት ላይ እንደ ነበሩ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳምንታዊው የረቡዕ አስተምህሮአቸው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ፣ ሊቀ ጳጳሳ አቡነ ኤድዋርድን ጨምሮ የሃያ አንድ ወንዶች እና ሴቶች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የብጽዕና አዋጆችን ይፋ እንዲያደርጉ ሥልጣን ሰጥተዋቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1931-1942 ዓ. ም. የኢስቶኒያ ሐዋርያዊ አስተዳዳሪ ሆነው ያገለገሉት የሊቀ ጳጳስ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች ሰማዕትነት አጽድቀዋል።

በትውልድ ጀርመናዊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ኤድዋርድ የሶቪየት ኅብረት ጦር ኢስቶኒያን ከወረረ ከአንድ ዓመት በኋላ ተይዘው ወደ ሳይቤሪያ እስር ቤት ተወስደው የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው እንደ ነበር ይታወሳል። ሊቀ ጳጳስ ኤድዋርድ ፕሮፋይትሊች የሞት ፍርድ ከመፈረዱ አስቀድሞ በየካቲት 22/1942 ዓ. ም. በኪሮቭ እስር ቤት መሞታቸው ይታወሳል።

ብጽዕናው በሩቅ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን የሚያስተላልፈው መልዕክት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአቡነ ኤድዋርድ ፕሮፊትሊች ብጽዕና ማጽደቃቸውን በደስታ የተቀበሉት፥ በኤስቶኒያ የታሊን ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ፊሊፕ ጆርዳን፥ ዜናው የተሰማው በአገሪቱ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያዊ አስተዳደር ምሥረታ 100ኛ ዓመት በማክበር ላይ እያለች መሆኑን አስታውቀዋል።

አቡነ ጆርዳን ከቫቲካን ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በኢስቶኒያ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዋን ብጹዕ በማግኘቷ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ “የቤተ ክርስቲያን ዓላማም ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ እና እንዲቀደሱ መርዳት በመሆኑ ለቤተ ክርስቲያናቸው እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። “በኢስቶኒያ ቤተ ክርስቲያን ብጹዕ ማግኘት ክርስቲያናዊ የቅድስና ተልዕኮን እውን እንደሚያደርገው እና ሰዎች ቅድስናን ማግኘት የሚቻል መሆኑን እንዲያምኑ ያግዛል” ብለዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኢስቶኒያን ሐዋርያዊ አስተዳደርን ወደ ታሊን ሀገረ ስብከትነት ደርጃ ከፍ ካደረጉት ከሦስት ወራት በኋላ ነው ዜናው የተሰማው” ብለዋል። የፈረንሳይ ተወላጅ የሆኑት አቡነ ፊሊፕ ጆርዳን፥ “ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤድዋርድ ፕሮፋይትሊች ልክ እንደ ሙሴ ነበሩ፤ የተስፋይቱን ምድር ለማየት ፈልገው ነገር ግን በዓይናቸው ሊያዩዋት አልቻሉም” ብለዋል።

አቡነ ጆርዳን አክለውም፥ ኢስቶኒያ በካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር ዝቅተኛ እና በሩቅ እንደምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ብትታይም ነገር ግን የብጽዕና አዋጁ በቅርብ የምትገኝ እንደሆነች እንዲሰማቸው ማድረጉን ጠቁመዋል። “የወቅቱ ሁኔታ የተወሳሰበ ቢሆንም የሞስኮ ሀገረ ስብከት የአቡነ ኤድዋርድ ፕሮፋይትሊች የብጽዕና ሂደትን ያስጀመረው ከ21 ዓመታት በፊት በመሆኑ ለሩሲያ ካቶሊኮች አስደናቂ ዜና ነው” ብለዋል።

የእምነት ፣ የተስፋ እና የሰላም ምሳሌ ነው!
የታሊን ሀገረ ስብከት የመገናኛ መምሪያ ቢሮ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ማርጌ-ማሪ ፓስ የሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤድዋርድ ብጽዕና ጉዳይ በመምራት እና የሕይወታቸው ታሪካዊ እውነታዎችን በመሰብሰብ እና የነባር ሥራዎቻቸውን ሥነ-መለኮታዊ ይዘት በመገምገም የሀገረ ስብከቱ ቀኖናዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚፈለጉትን የፍርድ እና የሕግ ግዴታዎች በማስፈጸም አገልግለዋል።

ወ/ሮ ፓስ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት፥ “ሰማዕቱ ሊቀ ጳጳስ ለብዙ ሰዎች የእምነት እና የተስፋ ምሳሌ ይሆናሉ” ብለው፥ “የሊቀ ጳጳሱ መሪ ቃልም ‘እምነት እና ሰላም’ የሚል ነበር” ሲሉ ተናግረው፥ “ሊቀ ጳጳስ ኤድዋርድ በጣም ፈታኝ በሆነ ጊዜም ቢሆን እምነትን እና ሰላምን ሁል ጊዜ በልባችን ውስጥ ለመጠበቅ እንደሚያበረታታን እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል።

የኮምፒየን ሰማዕታት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ታኅሳስ 9/2017 ዓ. ም. የኮምፒየን ሰማዕታቱን ለዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ይፋ ባደረጉበት ሥነ-ሥርዓት ላይ፥ የቅዱስ አውግስጢኖስ ብፁዕት ቴሬዛ (በቤት ስሟ፥ ማርያ ማዳሌና ክላውዲያ ሊዶይን) እና በሰማዕትነት የተገደሉ 15 ቄርሜሎሳውያን ጓደኞቿን፣ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ በእምነታቸው ምክንያት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 17/1794 በጥላቻ የተገደሉ ሰማዕታት ስም በቅዱሳን መዝገብ ውስጥ እንዲካተት አድርገዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በተጨማሪም በጣሊያን ካልቨንዛኖ ዲ ቬርጋቶ በተባለ አካባቢ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 7/1910 ተወልደው በጥቅምት 1/1944 በፒዮፔ የተሰዋው የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዴ ላሳል ማኅበር ካኅን እና የእግዚአብሔር አገልጋይ የአባ ኤሊያ ኮሚኒ ሰማዕትነት አጽድቀዋል። እንዲሁም ዛሬ ሮማንያ ተብላ በምትጠራ አገር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 28/1896 ዓ. ም. ተወለደው እና በመስከረም 29/1980 የተሰውት የአልባ ኢሊያ ጳጳስ የነበሩ የእግዚአብሔር አገልጋይ አቡነ አሮን ማርተንን ሰማዕትነት አጽድቀዋል። ጣሊያን ውስጥ በዛሬዋ ትሪኒታፖሊ በምትባል አካባቢ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 23/1829 ተወልዶ ነሐሴ 9/1902 በአንግሪ ግዛት የተሰዋው የእግዚአብሔር አገልጋይ እና የቅድስተ ቅዱሳን ቤዛ ማኅበር አባል አባ ጁሴፔ ማርያ ሊዮን ሰማዕትነት እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ 15/1914 በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ተወልዶ መጋቢት 25/1991 እዚያው የተሰዋው የእግዚአብሔር አገልጋይ ምዕመን ፒየር ጎርሳት ሰማዕትነት አጽድቀዋል።

 

19 December 2024, 17:23