ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የማረሚያ ቤት ቅዱስ በርን ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈቱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ዛሬ የምከፈተው ሁለተኛ ቅዱስ በር የዚህ ማረሚያ ቤት በር እንዲሆን እፈልግ ነበር” በማለት ተናግረዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. ለሚከበረው የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት መግቢያነት ታኅሳስ 15/2017 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የከፈቱት የመጀመሪያው በር የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዶስ በር እንደ ነበር ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም-ረቢቢያ ወደሚገኘው አዲሱ ማረሚያ ቤት ሲደርሱ በሩን የመክፈት አስፈላጊነት በቦታው ለነበሩት የማረሚያ ቤቱ ሠራተኛች እና ታራሚዎች እንዲሁም እንግዶች አስረድተዋል። በማረሚያ ቤቱ “የአባታችን ሆይ!” ጸሎት ቤት ፊት ለፊት ባደረጉት ንግግር፥ ሁሉም ሰው የልቡን በር እንዲከፍት ጠይቀው፥ ተስፋ ፈጽሞ የማያሳዝን መሆኑን ለመረዳት ዕድል እንዲረው አሳስበዋል።
ልብን እና በሮችን መክፈት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የማረሚያ ቤቱን ቅዱስ በር ከተሻገሩ በኋላ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል። በጉብኝታቸው ታሪካዊነት ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከትም፥ “ቅዱስ በርን የመክፈት ሥነ-ሥርዓት ውብ ምልክት ነው” ሲሉ ገልጸው፥ ነገር ግን በሮችን ከመክፈት በላይ በቦታው የነበሩት ታራሚዎችም ልባቸውን እንዲከፍቱ አደራ! ብለው፥ “ልብን መክፈት የወንድማማችነት ምልክት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
በሕይወት እንዳንኖር የሚያደርጉን የተዘጉ እና የደነደኑ ልቦች እንዳይኖሩን በማሳስብ፥ የኢዮቤልዩ በዓል ልባችን ለተስፋ ክፍት እንዲሆን የሚያደርግ ጸጋን እንደሚሰጠን በመግለጽ፥ አስቸጋሪ እና ፈታኝ በሆኑ ጊዜያት እንኳን ተስፋ የማያስቀይም መሆኑን አረጋግጠዋል።
ተስፋ ምርኩዛችን ነው!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ተስፋን በገመድ ታስሮ በባሕር ዳርቻ ከሚቆም መልህቅ ጋር በማመሳሰል፥ “ገመዱ ከባድ በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ እጃችንን ሊጎዳው ቢችልም ነገር ግን ሁል ጊዜ ከፊታችን አንድ ነገር በመኖሩ የተስፋ መልህቅ በአስቸጋሪ ጊዜያትም ወደ ፊት እንድንሄድ ያግዘናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ልባችን በግማሽ ተዘግቶ አይቆይ!
“የሰው ልብ ሲዘጋ እንደ ድንጋይ ይጠነክራል፤ ርኅራኄንም ያጣል!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ልቡ ሙሉ በሙሉ ሲዘጋበት ወይም ግማሽ ሲዘጋበት እያንዳንዱ ሰው ማወቅ እንድሚችል አስረድተው፥ የከፈቱት ቅዱስ በር “የልባችን በር ምልክት ነው” በማለት እስረኞች ለተስፋ ክፍት እንዲሆኑ ምክሯቸውን ለግሠዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለታራሚዎቹ እንደሚጸልዩላቸው ተናግረው ጸሎታቸውንም ጠይቀዋል።
ቅዱስነታቸው ስጦታ ተበርክቶላቸዋል
በመስዋዕተ ቅዳሴው ፍጻሜ ላይ ታራሚዎች እና ዘቦቻቸው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስጦታን ያበረከቱ ሲሁን፥ ከእነዚህም መካከል የቅዱስ በር ምልክት፣ ዘይት፣ ዳቦ ቆሎ እና ከሴራሚክስ የተሰሩ የጥበብ ሥራ ውጤቶችን የያዘ ቅርጫት በስጦታነት ቀርቦላቸዋል።
የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቀድሞው የማረሚያ ቤቱ መኮንን በአርቲስት ኤሊዮ ሉሴንቴ የተሠራውን የክርስቶስ አዳኝ ሥዕል ያበረከተ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በበኩላቸው ዝግጅቱን የሚዘክር ብራናን ለማረሚያ ቤቱ በስጦታነት አበርክተዋል።