ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የማረሚያ ቤት ቅዱስ በር መክፈታቸው ለታራሚዎች የተስፋ መልዕክት ነው!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዘንድሮ የአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓል ዋዜማ ዕለት ታኅሳስ 15/2017 ዓ. ም. የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በርን በይፋ በከፈቱበት ወቅት የ 2025 (እ.አ.አ) የኢዮቤልዩ ዓመት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ያስጀመሩ ሲሆን፥ ቀጣዮቹ ቀናት በሮም የሚገኙ ሌሎች የሦስት ዋና ዋና ባዚሊካ በሮችንም እንደከፍቱ ታውቋል።
የረቢቢያ ማረሚያ ቤት አምስተኛው የቅዱስ በር መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለረዥም ዓመታ ሲደረግ በቆየው የኢዮቤልዩ ባሕል ለመጀመሪያ ጊዜ ሮም በሚገኝ ማረሚያ ቤት አምስተኛውን ቅዱስ በር ይከፍታሉ። ይህን በማድረግ ሁሉም ታራሚዎች የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ እና በአዲስ የመተማመን ስሜት እንዲመለከቱት ይጋብዛሉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማረሚያ ቤቱን እንደ “የተስፋ ተጓዥ” በመሆን የሚጎበኙት ሲሆን፥ ይህም በማረሚያ ቤቱ ለሚገኙት አቅመ ደካሞች በተለይም የማረሚያ ቤቱ ሠራተኞች እና ካኅናት ጎበኚ የሌላቸውን በፍቅር እና በትጋት ሊንከባከቡ እንደሚገባ የሚሳስብ እንደሆነ ታውቋል።
የረቢቢያ ማረሚያ ቤት ሐዋርያዊ አገልጋይ የሆኑት አባ ሉሲዮ ቦልድሪን ከቅዱስነታቸው ጉብኝት ቀደም ብሎ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፥ “ታራሚዎቹ ከኅብረተሰቡ ርቀው እና ተለይተው የቅዱስነታቸው ቅርበት የሚሰማቸው በመሆኑ ጉብኝታቸውን በደስታ እየጠበቁት ነው” ብለው፥ በጉብኝታቸው መጽናናትን በማግኘት ሁላችንም የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመትን በተስፋ ለመዝለቅ ቃል መግባት አለብን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለታራሚዎች የማያቋርጥ አሳቢነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለታራሚዎች ያላቸውን ቅርበት በማጽናናት እና በጸሎት ሲመሰክሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። በርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት ሁሉ ለታራሚዎች ያላቸውን ጥልቅ እና የማያቋርጥ አሳቢነትን በማሳየት፣ ርህራሄ እና ክብር እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ ኅብረተሰቡም ታራሚዎችን እንደ ተገለሉ ሳይሆን እንደ ግለሰብ ማየት እንደሚገባ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይህ አቋማቸው እያንዳንዱን ሰው እንደ እግዚአብሔር ልጅ በማየት፥ ምህረትን እና ቤዛነትን መሠረት ባደረገ በካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮ ሥር የሰደደ መሆኑን የሚያጎላ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ነፃነታቸውን የተነፈጉ ታራሚዎች የቅጣቱ ክብደት በየቀኑ እንደሚሰማቸው፣ ፍቅርን እና አክብሮትን ማጣት ከሚሰማቸው ስሜቶች መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑ አስባለሁ” ማለታቸው ይታወሳል።
በእስር ቅጣት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥረት ማድረግ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለታራሚዎች ያላቸው ተቆርቋሪነትን ጨምሮ ለሰው ልጆች በሙሉ የተፈጥሮ ክብር እውቅና እንዲሰጥ ጥሪ ያቀርባሉ። ከካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮ ጋር በተጣጣመ መልኩ ማረሚያ ቤቶችን እንደ ማገገሚያ ተቋማት የመመልከት አስፈላጊነትን አፅንዖት ሰጥተው፥ ማረሚያ ቤቶች የቅጣት ቦታ ብቻ ሳይሆኑ ታራሚዎችም ፍትህን የማግኘት መብት እንዳላቸው ገልጸዋል። “የሰው ልጅ መናቅ የለበትም” በማለት ከሚያቀርቡት መልዕክቶች ጋር ከባድ ጥፋት የፈፀመም ከሰብዕናው ጋር ወደተሻለ ሕይወት የመለወጥ አቅም እንዳለው በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
የዚህ ተሟጋችነት ቁልፍ ገጽታ የሞት ቅጣት እንዲሠረዝ ደጋግመው የሚያቀርቡት ጥሪ እና የዕድሜ ልክ እስራትን በግልፅ በመተቸት፥ “ድብቅ የሞት ፍርድ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፥ ይልቁንም ለመልሶ ማቋቋም እና ለማኅበራዊ ትስስር ቅድሚያን የሚሰጡ ሥርዓት እንዲኖርም ይሟገታሉ።
በእስር ቅጣት ላይ ተሐድሶ እንዲደረግ ጥረት ማድረግ
የቅዱስነታቸው ጥሪ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ፥ ለምሳሌ በታራሚዎች ቁጥር መብዛት የሚፈጠረው መጨናነቅ፣ ኢ-ሰብዓዊ ሁኔታዎች እና እስረኞችን ማግለል የመሳሰሉ ችግሮችን ለመፍታት ሰፊ ጥረቶችን አድርገዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ መንግሥታት በተሃድሶ የፍትህ መርሃ-ግብሮች ላይ ይበልጥ እንዲሰሩ በማሳሰብ፥ የወንጀል ምልክቶችን ብቻ ሳይሆን የችግሩ ማኅበራዊ መንስኤዎችን መፍታት አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። በተጨማሪም ከበቀል ይልቅ በመልሶ ማቋቋም እና በፈውስ ላይ ያተኮረ የፍትህ ሥርዓት እንዲሰፍን፣ ግንኙነቶችን እንደገና የሚገነቡ እና ማኅበረሰቦችን የሚያስተካክሉ አካሄዶች እንዲኖሩ ያሳስባሉ።
በማኅበረሰቡ ለተገለሉት ትኩረት መስጠት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ የሚያቀርቡት ጥሪ ጭብጥ ለተገለሉት፣ በተለይም ለድሆች እና ተጋላጭ ለሆኑት እንዲሁም በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ለሚገኙት የሚሰጥ ተመጣጣኝ ያልሆነ ፍርድን የሚመለከት ነው።
ቅዱስነታቸው በእነዚህ ወገኖች መካከል ከፍተኛ ቅጣት እንዲጣል አስተዋጽኦ በሚያደርጉ ፍትሃዊ ባልሆኑ ሥርዓቶች ላይ በማትኮር፥ ኅብረተሰቡ የወንጀሎቹ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶችን እንዲያገኝ አሳስበዋል። ያቀረቡት የፍትህ ጥያቄም በግለሰቦች ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን አስከፊውን የድህነትና የወንጀል አዙሪት በሚያራምዱ መዋቅሮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ታውቋል።
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ማረሚያ ቤቶች ያደረጓቸው ጉብኝቶች
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተግባር ከቃላት በላይ በተግባር የሚጨበጥ ሲሆን፥ በየዓመቱ በሕማማት ሳምንት ሐሙስ ሙስሊም ታራሚዎችን እና ሴቶችን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ታራሚዎች እግር የማጠብ ሥነ-ሥርዓት ተምሳሌታዊ ምልክት በመሆን የኅብረተሰቡን ጭፍን ጥላቻ በመቃወም የአብሮነትን መልዕክት የሚያስተላልፍ እንደሆነ ታውቋል።
በተጨማሪም በየጊዜው በሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶቻቸው ወቅት ማረሚያ ቤቶችን የሚጎበኙ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. በአሜሪካ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በፊላደልፊያ የሚገኘውን ማረሚያ ቤት እና በ2016 በሜክሲኮ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የቹዳድ ዩአሬዝ ማረሚያ ቤትን ጉብኝተው “ታራሚዎች ራሳቸውን የመለወጥ አቅም አላቸው” ሲሉ ማስገንዘባቸው ይታወሳል።
የእግዚአብሔር የሁልጊዜ መሐሪነት እና ቤዛነቱም ለሁሉ ነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ደጋግመው እንደገለጹት፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ መሐሪ፣ ቤዛነቱም ለሁሉ እንደሆነ፣ ሌላው ቀርቶ እጅግ ከባድ ወንጀል የሠሩትም ቢሆኑ ምሕረትን እንደሚያገኙ፥ በቅርቡ በሕማማት ሳምንት ሐሙስ ሮም ውስጥ በሚገኝ የሬቢቢያ የሴቶች ማረሚያን በጎበኙበት ወቅትም “ኢየሱስ ይቅር ማለት አይሰለቸውም” በማለት፥ እንዲሁም በሚያዝያ ወር በጣሊያን-ቬኒስ በሚገኝ የሴቶች ማረሚያ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክትም፥ የማረሚያ ቤት ሕይወት ከባድ ቢሆንም ሕይወትን መልሶ ለመገንባት የሚያግዝ ቦታ ሊሆን እንደሚችል እና ታራሚዎች ዘወትር በተስፋ ወደፊት እንዲመለከቱ” በማለት ማበረታታቸው ይታወሳል።