ፈልግ

ሕጻናት በዩክሬይን እና ሩስያ ጦርነት ወቅት የብርሃነ ልደቱን በዓል ሲያከብሩ ሕጻናት በዩክሬይን እና ሩስያ ጦርነት ወቅት የብርሃነ ልደቱን በዓል ሲያከብሩ  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በጦርነት በተገደሉት ሕፃናት በማዘን ተኩስ እንዲቆም ጸሎት አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ታኅሳስ 13/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኚዎች ካቀረቡት ስብከት በኋላ የእኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት መርተዋል። በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ መጭውን የብርሃነ ልደቱ በዓል ምክንያት በማድረግ ባቀረቡት ጥሪ፥ በሁሉም የጦር ግንባሮች ተኩስ አቁም እንዲደረግ አሳስበዋል። ስቃይ እና መከራ በደረሰባቸው እንደ ሞዛምቢክ፣ ዩክሬን እና ቅድስት ሀገር በመሳሰሉ አገሮች፣ ሰላም፣ ተስፋ እና እርቅ እንዲወርድ በድጋሚ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጦርነት እና በዓመፅ ምክንያት የሚደርስባቸውን መከራ በጽናት ለሚታገሡት በሙሉ ያላቸውን ጥልቅ አሳቢነት ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው እሑድ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኚዎች ይህን የገለጹት፥ ለአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓል ሦስት ቀናት ብቻ በቀሩበት ማለትም ታኅሳስ 13/2017 ዓ. ም. እንደ ነበር ታውቋል።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ባስተላለፉት የሰላምታ ንግግር፥ በድህነት እና በዓመፅ መካከል የሚገኘውን የሞዛምቢክ ሕዝብ አስታውሰው፥ ለዚህ ሕዝብ ያላቸውን ትኩረት እና አሳቢነት በመግለጽ፥ “በእምነት እና በፈቃደኝነት የተደገፈ ውይይት እና የጋራ ጥቅም ፍለጋ አለመተማመንን እና አለመግባባትን እንዲያሸንፍ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። በሌሎች የግጭት ቀጠናዎች በንጹሃን ሕጻናት ላይ የሚፈጸመውን ጭካኔያዊ ተግባራትንም አውግዘዋል።

“በሥቃይ ውስጥ በምትገኝ የዩክሬን ከተሞች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ቀጥሏል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እነዚህ ጥቃቶች አንዳንድ ጊዜ በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎች እና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ጉዳትን እንደሚያደርሱ ገልጸዋል። “የጦር መሣሪያዎች ድምጽ ቆሞ የብርሃነ ልደቱ መዝሙሮች ይዘመሩ!” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሁሉም የጦርነት ግንባሮች፣ በዩክሬን፣ በቅድስት አገር፣ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት እና በመላው ዓለም ውስጥ በብርሃነ ልደቱ በዓል ወቅት ተኩስ እንዲቆም እንጸልይ” ብለዋል። ብዙ የጭካኔ ተግባር በሚፈጸምባት ጋዛ ውስጥ በጦር መሣሪያ የሚገደሉ ሕጻነትን፣ በግፍ በሚፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶች የሚወድሙ ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን በሐዘን አስበዋል።

ቅዱስነታቸው ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲመሩ
ቅዱስነታቸው ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲመሩ

“ሕጻናት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው!”
እሑድ በሮም እና አካባቢዋ በጣለው ከባድ ብርድ ምክንያት የእኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት እና መልዕክት ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከሕጻናት እና ከእናቶቻቸው ጋር በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ ያሳለፉትን የደስታ ጊዜን አስታውሰዋል።

በጎ አድራጎት ያለበትን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ያዘጋጁት በቫቲካን ውስጥ የሚገኙ የቅዱስ ቪንሴንት ማኅበር እህቶች እንደነበሩ ታውቋል። በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው መዋዕለ ሕጻናት የ102 ዓመት ታሪክ ያለው መሆኑ ታውቋል። መዋዕለ ሕጻናቱን በበላይነት የሚያስተባብሩ እህት አንቶኒዬታ ኮላቺን ለፍቅር አገልግሎታቸው ምስጋናን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ልባቸው በደስታ እንደተሞላ በመግለጽ እያንዳንዱ ሕጻን የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው የሕጻኑ ኢየሱስ ምስል ባርከዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ ሕጻናት በየቤታቸው ባዘጋጇቸው የብርሃነ ልደቱ ትዕይንቶች ላይ የሚያስቀምጧቸውን እና ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይዘው የመጡትን የሕጻኑ ኢየሱስ ምስሎችን ባርከዋል። “ልማዱ ቀላል ቢመስልም ነገር ግን ጠቃሚ ምልክት አለው” ሲሉ ተናግረው፥ ሁሉም ሰው አያቱን እንደሚያስታውስ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ፥ “በእነዚህ ቀናት ውስጥ ማንም ሰው ብቻውን እንዳሆን!” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

ሕጻናት በየቤታቸው የሚያዘጋጇቸው የብርሃነ ልደቱ ትዕይንቶች
ሕጻናት በየቤታቸው የሚያዘጋጇቸው የብርሃነ ልደቱ ትዕይንቶች
23 December 2024, 16:39