ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለአዳዲስ ካርዲናሎች ከኢየሱስ መንገድ ፈጽሞ እንዳይርቁ አደራ ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስልጣናቸው እንዳይታለሉ እና እንዳይደናገጡ፣ ነገር ግን ሁል ጊዜ በኢየሱስ መንገድ እንዲሄዱ እና ከሰዎች ጋር የመገናኘትን ፍቅር እንዲያሳድጉ ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 28/2017 ዓ.ም ለ21 አዳዲስ ካርዲናሎች ሲመተ ካርዲናልነት በሰጡበት ወቅት መናገራቸው ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ ዕለት ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ለሃያ አንድ አዲስ ካርዲናሎች ቡድን “በኢየሱስ መንገድ ላይ እንዲሄዱ፡ በትህትና፣ በመደነቅ እና በደስታ” እንዲመላለሱ አበረታተዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ አዳዲሶቹ ብፁዓን ካርዲናሎች ሲመት ላይ በተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ  እንዳሳሰቡት፣ ኢየሱስ ወደ እየሩሳሌም መውጣቱ ለዓለማዊ ክብር ብሎ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ሆነ አስታውሰው ይህንን አብነት ተከትለን እግዚአብሔርን የሕይወታችው ማዕከል አድርጋችሁ የሕብረትና የአንድነት ገንቢዎች መሆን አለባችው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ካርዲናሎቹን ለእዚህ ሲመት አጭተው እንደ ነበረ አስታውቀው የካርዲናሎች ተመራጮች አመጣጥ “የእግዚአብሔርን መሐሪ ፍቅር በምድር ላይ ላሉ ሰዎች ሁሉ ማወጇን የቀጠለችውን የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነት የሚገልጽ” መሆኑን በማመልከት ነው።

በትሕትና በእግዚአብሔር ፊት ቁሙ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የማርቆስን ወንጌል በማስታወስ በኢየሩሳሌም ኢየሱስ እኛን ወደ ሕይወት ለመመለስ በመስቀል ላይ እንደሚሞት ተናግሯል። ደቀ መዛሙርቱ “ለድል አድራጊው መሲሕ የሚሆን የቁልቁለት መንገድ” እያሰቡ ሳለ “ወደ ቀራንዮ የሚያደርሰውን አስቸጋሪ አቀበት መንገድ እርሱ መረጠ” ሲሉ ገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተመሳሳይ ነገር በእኛ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ገልጸዋል:- “ልባችን ሊሳሳት ይችላል፣ ይህም ለጌታ ባለው ከልክ ያለፈ ሰብዓዊ ቅንዓት በክብር መሳብ፣ በሥልጣን ማታለል እንዳንደናቀፍ" መጠንቀቅ ይኖርብናል ያሉ ሲሆን “ለዚህም ነው ወደ ውስጥ መመልከት፣ በእግዚአብሔር ፊት በትህትና መቆም እና መጠየቅ አለብን፡ ልቤ ወዴት እየሄደ ነው? ወደ የት ነው የምያመራው? ምናልባት የተሳሳተ መንገድ ሄጄ ይሆን? ” በማለት

በትህትና በእግዚአብሔር ፊት በመቆም ወደ ውስጥ ማየት አለብን ብለዋል።

ወደ ልብ ተመለስ

ቅዱስ አባታችን በመቀጠል አዲሶቹ ካርዲናሎች በኢየሱስ መንገድ ለመጓዝ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

“በኢየሱስ መንገድ ላይ መጓዝ ከምንም ነገር በላይ ወደ እርሱ መመለስ ማለት ሲሆን እርሱን በነገር ሁሉ መሃል ማድረግ ማለት ነው” በማለት ሁለተኛ የሆኑ ነገሮችንና ውጫዊ ገጽታዎችን እንዳይፈልጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ቅድሚያ መሆን ላለበት ነገር ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

“ካርዲናል” የሚለው ቃል የሚያመለክተው እሱን ለመጠበቅ፣ ለመደገፍ እና ለማጠናከር በር ውስጥ የገባ ማንጠልጠያ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው "ውድ ወንድሞቼ፡ ኢየሱስ እውነተኛ ድጋፍ፣ የአገልግሎታችን “የስበት ማዕከል”፣ ሕይወታችንን በሙሉ የሚመራው “ዋናው ነጥብ” ነው ብለዋል።

የመገናኘት ፍላጎት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል “ኢየሱስ ብቻውን ሄዶ አያውቅም” ያሉ ሲሆን “በኢየሱስ መንገድ መሄድ ማለት ከሰዎች ጋር የመገናኘትን ስሜት ማዳበር ማለት ነው” ብለዋል።

አክለውም ኢየሱስ የመጣው “የቆሰሉትን የሰው ልጆችን ለመፈወስ፣ የልባችንን ሸክም ለማቅለል፣ የኃጢአትን እድፍ ለማንጻት እና የባርነትን እስራት ለመበጣጠስ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በመንገዱ ላይ "የተሰቃዩትን እና ተስፋ ያጡ ሰዎችን ፊት ስያገጥሙት" ኢየሱስ የወደቁትን አንስቶ የታመሙትንና ልባቸው የተሰበረውን ፈውሷል ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተናግረዋል።

የህብረት እና አንድነት ፈጣሪዎች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ “በኢየሱስ መንገድ መሄድ ማለት በመጨረሻ የሕብረትና የአንድነት ገንቢዎች መሆን ማለት ነው” ሲሉ ራሳችንን እንዳንመለከት ከሚከለክለው “ከፉክክር” እና “የጠላትነት ግድግዳ” እንዲጠነቀቁ መክረዋል፣ እናንተ የአንዱ አባት የእግዚአብሔር ልጆች ናችው ብለዋል።

ከተለያዩ አስተዳደግ እና ባህሎች የተውጣጡ፣ የቤተክርስቲያኒቱን ካቶሊካዊነት የሚወክሉትን አዳዲሶቹ ካርዲናሎች “የወንድማማችነት ምስክሮች፣ የሕብረት እና የአንድነት ገንቢዎች” እንዲሆኑ አሳስቧቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ባደረጉት ስብከት ማጠቃለያ ላይ ከቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ንግግር በመጥቀስ “በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ሁሉም ሰው እንደ ቤቱ እንዲሰማው፣ መገለል ወይም ማግለል እንዳይኖር ፍላጎታችን ነው፣ ይህም በበጎ አድራጎት ወይም ጥረታችን ላይ አንድነታችንን በእጅጉ ይጎዳል። አንዳንዶቹ በሌሎች ላይ ጉዳት ማድረስ አይገባቸውም” በማለት ተናግሯል።

በማጠቃለያም ለ21 አዲስ ካርዲናሎች “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፣ እርስ በርሳችሁም የወንጌል አገልጋዮች ሁኑ” ያሏቸው ሲሆን በትህትና፣ በመደነቅ እና በደስታ በኢየሱስ መንገድ ተመላለሱ ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን አጠናቀዋል።

09 December 2024, 15:28