ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከጣሊያን የባንክ ተቋማት ተወካዮች የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከጣሊያን የባንክ ተቋማት ተወካዮች የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ባንኮች ለጦርነት ሳይሆን ለመልካም ተስፋ እንዲሠሩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ ልዩ የጣሊያን የባንክ ተቋማት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው የባንኮችን ሥነ-ምግባር በማስታወስ ባስተላለፉት መልዕክታቸው፥ የፋይናንስ ሴክተሩ መዋዕለ ንዋዩን በብዝበዛ እና በጦርነት ላይ ሳይሆን በልማት እንዲያፈስ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ታኅሳስ 7/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው አንዳንድ የጣሊያን የባንክ ተቋማት ልዑካን ባደረጉት ንግግር፥ በሰዎች ላይ ትርፍን የሚሰበስቡ ተቋማትን በማስጠንቀቅ፥ ይህም ብዝበዛን እና ማኅበራዊ የኑሮ አለመመጣጠንን እንደሚያስከትል አስረድተዋል። “የፋይናንስ ሴክተሩ የሰዎችን መብት የሚረግጥ ከሆነ፣ በሰዎች መካከል የኑሮ አለመመጣጠንን የሚያባብስ ከሆነ እና እራሱን ከተወሰነለት እና ከሚፈለገው የአገልግሎት መስመር የሚያርቅ ከሆነ ዓላማውን የሚክድ እና ወደ ኋላ የቀረ ኢኮኖሚ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የፋይናንስ ሥነ-ምግባራዊ ኃላፊነቶች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የፋይናንስ ሥነ-ምግባራዊ ኃላፊነቶችን እና በኅብረተሰቡ ላይ ያለውን ተፅእኖ በማንፀባረቅ ባደረጉት ንግግር፥ የፋይናንስ ሴክተሩ ማካተትን እና ዘላቂነትን ለማጎልበት ያለውን አቅም በማጉላት፥ የሰዎችን ፍላጎቶች ከማሟላት ወደ ኋላ ማለት እንደሌለበት አሳስበዋል።

አንዳንድ ታሪካዊ ምሳሌዎችን በመጥቀስ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ቤተ ክርስቲያን ጣሊያን ውስጥ አቅም ለሌላቸው ሰዎች የብድር ሥርዓቶች ለማመቻቸት፣ የባንክ ሥራዎችን እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት በሚል ዓላማ በ15ኛው ክፍለ ዘመን ለተቋቋመ “ሞንቲ ዲ ፒዬታ” ለተሰኘ የገንዘብ ተቋም ማኅበረሰባዊ ዕውቀቶች ያሉባቸው ሃሳቦችን በማካፈል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷን አስታውሰዋል።

ችግር ውስጥ ለወደቁት ሰዎች ማኅበረሰባዊ የብድር ሥርዓቶች ለማመቻቸት በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 13ኛ ይፋ ያደረጉትን “ሬረም ኖቫሩም” ወይም “አዳዲስ ነገሮች” የተሰኘ ማኅበረሰባዊ ሐዋርያዊ ሠነድን አስታውሰው፥ የእነዚህ ተነሳሽነቶች ዋና ዓላማ ሁል ጊዜም ምንም ለሌላቸው ሰዎች ዕድሎችን ለመስጠት እንደሆነ በመግለጽ፥ የፋይናንስ ሴክተሩ ማኅበራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል።

ለትርፍ ቅድሚያን የሚሰጡ አሉታዊ ዘመናዊ የባንክ ልምዶች
ሥነ-ምግባርን የተላበሱ የፋይናንስ ልማዶች መኖራቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጊዜያችን የሰዎችን ፍላጎት ከማገልገል ይልቅ ትርፍን በማስቀደም ኋላቀር የሆነ ኢኮኖሚያዊ ባህሪን በማጎልበት ላይ የሚገኙ የአንዳንድ ባንኮች ልምዶችን ተቃውመዋል።

እነዚህ ባንኮች የሰውን ጉልበት ለመበዝበዝ ወደ ሌላ አገር መዛወራቸውን፣ አራጣ አራማጆችን ተጠቃሚ ለማድረግ መቋቋማቸውን፣ የተቸገሩትን ችላ በማለት የፋይናንስ ሥርዓቶቻቸው ገንዘባቸውን በአንድ ቦታ በመሰብሰብ ትርፋቸውን ለማሳደግ ሲሉ ብቻ መዋዕለ ንዋያቸውን በሌላ ቦታ በማፍሰስ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ይህ የግንኙነት መቋረጥ ተጋላጭ ማኅበረሰቦች ራሳቸውን እንደተበዘበዙ እና ወደ ጎን እንደተተዉ አድርገው እንዲቆጥሩ ያደርጋቸዋል ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስጠንቅቀዋል።

“የፋይናንስ ሴክተሩ የሰዎችን መብት የሚረግጥ ከሆነ፣ በሰዎች መካከል የኑሮ አለመመጣጠንን የሚያባብስ ከሆነ እና እራሱን ከተወሰነለት እና ከሚፈለገው የአገልግሎት መስመር የሚያርቅ ከሆነ ዓላማውን የሚክድ እና ወደ ኋላ የቀረ ኢኮኖሚ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል። 

የፋይናንስ ሴክተሩ የሰው ልጅ ዕድገትን ማስቀደም አለንበት!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን የባንክ ተቋማት የበለጠ ሰብዓዊ አቀራረብ ማዘጋጀታቸውን በማስታወስ በቫቲካን የተቀበሏቸውን ተወካዮች አመስግነዋል። ፋይናንስን “የኢኮኖሚው የደም ዝውውር ሥርዓት ነው” በማለት ገልጸው፥ “በቂ የፋይናንስ ሥርዓት ከሌለ ዘላቂነትን ለማካተት እና ለማስፋፋት የሚያስችል ዋነኛ የሰው ልጅ ልማትን ማምጣት አይቻልም” ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል። “ስለዚህ ባንኮች ግምታዊ እና አጥፊ የሆኑ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቶች፣ የመኖሪያ አካባቢ ድህንነትን የሚጎዱ እና ጦርነትን የሚያበረታቱ በመሆናቸው ሊወገዱ ይገባል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም፥ “ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት፥ አራጣ አስተሳሰብን ወደማራመድ፣ የሰው ልጅ የመኖሪያ አካባቢን ወደሚጎዱ እና ጦርነትን ወደሚያበረታቱ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቶች የሚለውጥ አይደለም” ብለዋል።

ተስፋን የሚሰጥ የዕዳ ጫና ስረዛ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጪው የጎርጎሮሳውያኑ አዲስ ዓመት 2025 የሚከበረውን የኢዮቤልዩ ተስፋን በመጠባበቅ እንደተናገሩት፥ “ይህ በዓል በብዙ ሰዎች በተለይም በድሆች ሕይወት ውስጥ ተስፋን እና መልካም የወደፊት ሕይወትን ለመፍጠር ቅድመ ሁኔታን የሚያመቻች ነው” በማለት በማደግ ላይ ያሉ አገራት ዕዳቸው እንዲሠረዝላቸው ያቀረቡትን ጥሪ ደግመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንንችስኮስ በመጨረሻም አባ ፕሪሞ ማዞላሪን በማስታወስ፥ “ባንኮች ማኅበራዊ ፍትህ እንዲከበር የማበረታታት፣ የአካታችነት አስተሳሰብን የማበረታታት እና የሰላም ኢኮኖሚን የመደገፍ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው” በማለት በቫቲካን ለተቀበሏቸው ለጣሊያን የባንክ ተቋማት ተወካዮች ያደረጉትን ንግግር ደምድመዋል።

 

17 December 2024, 16:28