ካርዲናል ኩርት ኮህ የጠበቀ ትስስር መፍጠር ለክርስቲያን ሕብረት የሚደርገውን ጥረት ይደግፋል አሉ!
ክርስቲያኖች ሕብረት እንዲፈጥሩ ለማድረግ የሚሰራው ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ኩርት ኮህ በአሁኑ ጊዜ የክርስቲያን ሕብረት እንዲፈጠር እየተጋ የሚገኘው ጳጳሳዊ ምክር ቤት የተመሰረተበትን 60ኛው ዓመታዊ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልእክት ክርስቲያናዊ የሆነ ሕብረት ለመፍጠር የሚደርገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ቢታይበትም ቅሉ ብዙ ተግዳሮቶች እየገጠሙት እንደ ሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል።
የቫቲካን ዜና
“ለክርስቲያናን ሕበረት ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው ሁለት ዝግጅቶች በአሁኑ ጊዜ በመታሰቢያነት እየተከበሩ” መሆኑን የገለጹት ካርዲናል ኩርት ኮህ እነዚህም የዛሬ 25 አመት ገደማ እ.አ.አ. በግንቦት 25/1995 ዓ.ም በላቲን ቋንቋ “Ut unum sint” በአማርኛው “አንድ ለመሆን” በሚል አርዕስት በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ይፋ ያደርጉት ሐዋርያዊ መልእክት እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን ይህ ሐዋርያዊ መልእክ በክርስቶስ ስም የሚጠሩ የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የእምነታቸው ስር መሰረት አንዱ ክርስቶስ በመሆኑ የተነሳ በሕብረት ቅዱስ ወንጌልን ለዓለም እንዲያበስሩ ጥሪ የሚያቀርብ ሐዋርያዊ መልእክት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
ሁለተኛው መታሰቢያ ደግሞ እ.ኤ.አ. በሰኔ 5/1960 ዓ.ም. በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ክርስቲያናዊ ሕብረት ለመፍጠር እና ለማስፋፋት ይችላ ዘንድ ይህንን ጉዳይ በትኩረት የመከታተል ኃላፊነት የተጣለበት ጳጳሳዊ ምክር ቤት የዛሬ 60 ዓመት ገደማ እንዲመሰረት ማደረጋቸው በመዘከር ላይ እንደ ሚገኝ ገልጸዋል።
ካርዲናል ኩር ኮህ ጨምረው እንደ ገለጹት እ.ኤ.አ. ከ 1960 ዓ.ም. ጀምሮ ቤተክርስቲያኗ ክርስቲያናዊ የሆነ ሕብረት ለመፍጠር የተለያዩ ንቅናቄዎችን እና ውይይቶችን ማድረግ መጀመሯን የገለጹ ሲሆን ከእነዚህ ውይይቶች ብዙ ፍሬ መገኘቱን ጨምረው ገልጸዋል። ሆኖም “ክርስቲያናዊ ሕብረት መፍጠር አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ቢቻልም፣ ነገር ግን በየትኛው ቅርፅ እና ዓይነት መከናወን እንደ ሚገባው በሚገልጸው ሐሳብ ላይ አለመግባባት መኖሩን” ካርዲናል ኮህ ገልጸዋል።
የሆነ ሆኖ እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን ሕብረትን ለመፍጠር ልዩ አስተዋፅ ማድረግ እንደምትችል የገለጹት ካርዲናል ኮህ “ሕብረት እና ብዝሃነት የሚጣረዙ ነገሮች አይደሉም፣ ክርስቲያናዊ ሕብረት አንዱ ያለውን ስጦታ ለሌላው መስጠትን ያካተተ ነው” ብለዋል።
ካርዲናል ኩር ኮህ ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩ እንደ ገለጹት “ለምሳሌ በቤተክርስቲያኗ ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል ማዕከላዊ መሰረት መሆኑን ከተሃድሶ ከተወለዱ አብያተ ክርስቲያናት መማር እንችላለን፣ ከኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ “ሲኖዶሳዊነትን” እና ስለ ጳጳሳት አንድነት ልንማር እንችላለን፣ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ደግሞ አለማቀፋዊነትን እና የክርስቲያን ሕብረት ለመፍጠር በቤተክርስቲያኗ የምታደርገውን ጥረት እንማራለን” በማለት ካርዲናል ኮህ ገልጸዋል።
ካርዲናል ኮህ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ በቅድሚያ በተለያዩ አብያተ-ክርስቲያናት መካከል የወዳጅነት ግንኙነት ጠብቆ ለማቆየት የሚረዳ እና ያለፈውን ጭፍን ጥላቻን ለማስወገድ ጠቃሚ የሆነውኑ ውይይቶችን ማድረግ መቀጠል እንደ ሚገባ ገልጸዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእውነት ላይ የተመሰረተ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደ ሆነ የገለጹት ካርዲና ኮህ በታሪክ ሂደት ውስጥ ክፍፍል እንዲፈጠር ያደረጉት “አወዛጋቢ ጥያቄዎች ሥነ-መለኮታዊ ትንተኔዎች” እውነተኛ የሆነ ውይይት በማድረግ ሊፈቱ እንደ ሚገባ ጨምረው ገልጸዋል።
ሦስተኛው ደረጃ ደግሞ መንፈሳዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ሕብረት መፍጠር እንደ ሆነ የገለጹት ካርዲናል ኮህ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ” የሚለውን የኢየሱስን ክህነታዊ ጸሎት ጥልቀት እና ስምምነት ማክበር ተገቢ ነው ካሉ በኋላ ካርዲናል ኮህ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሁሉም የሐይማኖት ተቋማትና የተለያየ ሐይማኖት ተከታዮች ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸውና እውነተኛ የሆነ የሐይማኖት ነፃነት እንዲኖር መጣር እንዳለባቸው ይታወቃል።
ከሁሉም በላይ የሁሉም የሐይማኖት ተቋማት አለመግባባትን የሚፈጥረውን ጥላቻና ትምክተኛነትን አስወግደው የውይይት ባሕልን ማዳበር ይጠበቅባቸዋል። የአንድ አንድ ሐይማኖት ተከታይ ምዕመናን ከምሕረት ተግባራት ቅኝት ውጭ ሆነው በምያስተላልፉት እኩይ በሆነ ምልእክት ላይ ተመርኩዘው ልዩነቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉት ሙከራ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም።
በሚያሳዝን ሁኔታ በዕየለቱ የጥቃት ድርጊቶች፣ ጦርነቶች፣ አፈና፣ የሽብር ጥቃቶች፣ ግድያ እና ውድመት ሳንሰማ ያለፍንበት ቀን የለም፣ አንዳንድ ጊዜ ይህ አሰቃቂ የጭካኔ ተግባር በሐይማኖትና በእግዚኣብሔር ሥም ሲፈጸም ማየት በጣም ያሳዝናል። እነዚህን የእግዚኣብሔርን ሥም የሚያጎድፉና የሰው ዘር ሁሉ ያለውን የሃይማኖት ጥማት የማያረኩ ተግባራትን በግልጽ ማውገዝ ይጠበቅብናል።
የምሕረት ምስጢራዊነት በቃል ብቻ የሚገለጽና የሚከበር ሳይሆን ነገር ግን ከሁሉም በላይ በተግባር፣ እውነተኛ በሆነ በፍቅር፣ ወንድማቻችንን በማገልገልና ቅን በመሆነ መልኩ ያለንን ማጋራት የሚገለጽ ነው። ቤተክርስቲያናችን ይህንን ዓይነት የሕይወት መንግድ ለመከተ በከፍተኛ ሁኔታ ትሻለች፣ እንዲሁም ግማሽ አካሏ በሁሉም ሰዎች መካከል “አንድነት እና ፍቅር እንዲሰፍን የማድረግ ተግባር” በማከናወን ላይ ያተኮረ ነው (Nostra Aetate, 1)። በተመሳሳይ መልኩም ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ይህንን የሕይወት መንገድ እንዲከተሉ የተጠሩ ሲሆን በተለይም አሁን ባለንበት ወቅት የሰላም መልዕክተኞችና መልካም ግንኙነቶችን የሚያቀላጥፉ፣ ጥላቻን፣ መከፋፈልንና አለመቻቻልን የሚዘሩትን ሰዎች እንዲያወግዙ፣ እኛ ያለንበት ወቅት የወንድማማችነት እንደ ሆነ እንዲመሰክር ነው የተጠራነው። ይህም ተግባር እግዚኣብሔርን የሚያስደስትና በፍጥነት ለአሁኑ ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ከሁሉም በለይ የሁሉም ሐይማኖት መጠርያ ወይም መለያ የሆነውን ፍቅርን ማረጋግጥ ያስችለናል።
ይህ የምንራመድበት ጎዳን ይሁን። ዓላማ የለሽ የሆነውን የአለመግባባት መንገድና ትምክተኛነትን እናስወግድ። በአንድ አንድ አማኞች ምክንያት በሚፈጸመው ጥቃት ምክንያት የሚሰራጨው አፍራሽ መልዕክት ከምሕረት ተግባራት ቅኝት ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ በድጋሚ እንዳይከሰት መጣር ያስፈልጋል። በአንጻሩም በሁሉም ስፍራዎች የተለያየ ሐይማኖት የሚከተሉ ምዕመናን ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲገናኙና እውነተኛ የሐይማኖት ነጻነት እንዲመጣ መጣር ያስፈልጋል። ይህም በእግዚኣብሔር ፊት፣ በሰዎችና በመጭው ጊዜ ላይ የተሰጠን ኃላፊነት ነው፣ ይህም የማያባራ ጥረት የሚጠይቅ እና ያለ ግብዝነት መፈጸም ይኖርበታል። ለሁሉም መልካምነት በተስፋ አብሮ የሚያስጉዘንን ጎዳና እንድንይዝ የቀረበ ጥሪ እኛን የሚፈታተን ጥሪ ነው።
የተለያየ እምነት የሚከተሉ የሐይማኖት ተቋማት በችግሮች የቆሰለውንና ችግረኛ ለሆኑ የሰው ልጆች የእግዚአብሔር ምሕረትና ፍቅር የሚሸከሙ ሕይወት የሚያመነጩ ማሕጸን እንዲሆኑ፣ ኩራት እና ፍርሃት ባጸኑት ግድግዳዎች ውስጥ ዘልቆ በማለፍ የመርዳዳት እና የተስፋ በሮች እንዲከፈቱ ማድረግ ይገባል።