ካርዲናል ፓሮሊን ወደ አርስ እና ወደ ሉርድ ቤተ መቅደሶች መንፈሳዊ ጉብኝት ያደርጋሉ።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በፈረንሳይ አገር የሚገኙ ሁለት መንፈሳዊ ሥራዎችን የሚገበኙ መሆናቸው ታውቋል። የመጀመሪያ መንፈሳዊ ጉዟቸው በፈረንሳይ ወስጥ በአርስ ከተማ የሚገኝ መንፈሳዊ ሥፍራ ሲሆን፣ በዚህ ሥፍራው ሐምሌ 28/2012 ዓ. ም. ተገኝተው፣ በቅዱስ ጆቫኒ ማርያ ቪያኒ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓትን የሚመሩ መሆናቸው ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በመቀጠልም በፈረንሳይ በሚያደርጉት ሁለተኛ ይፋዊ ጉብኝታቸው፣ የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር ነሐሴ 9/2012 ዓ. ም. የሚከበረውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰታ መታሰቢያ ዓመታዊ ክብረ በዓልን በሉርድ ከተማ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅድስ የሚያከብሩ መሆናቸው ታውቋል።
የቫቲካን ዜና፤
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በፈረንሳይ አገር የሚያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከገባ ወዲህ የመጀመሪያ መሆኑ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በአርስ ክፍለ ሀገር የቆሞሳት ባለደረባ በሆነው በቅዱስ ጆቫኒ ማርያ ቪያኒ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ እንደሚገኙ የቤተ መቅደሱ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት ክቡር አባ ፓትሪስ ቾኮሎስኪ ለቫቲካን ኒውስ አረጋግጠዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ሐምሌ 28/2012 ዓ. ም. በቅዱስ ጆቫኒ ማርያ ቪያኒ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓትን እንዲመሩ መጋበዛቸው ሲታወቅ ከሰዓት በኋላ በሚካሄደው እና “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከካህናት እና ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ሆነው የሚያደርጉት ጉዞ” በሚል ርዕሥ በተዘጋጀ ኮንፈረንስ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።
የካርዲናል ኤሚል ቢያዬንዴ ማስታወሻ፤
ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በቅዱስ ጆቫኒ ማርያ ቪያኒ ቤተ መቅደስ ወስጥ በኮንጎ ብራዛቪል ጳጳስ በነበሩ፣ በካርዲናል ኤሚል ቢያዬንዴ ስም እንዲጠራ የተወሰነውን ጸሎት ቤት ባርከው እንደሚከፍቱት ይጠበቃል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1977 ዓ. ም. ያረፉት የኮንጎ ብራዛቪል ጳጳስ፣ ብጹዕ ካርዲናል ኤሚል ቢያዬንዴ ብጽዕና ሂደት በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳይ አጥኚ ጽሕፈት ቤት እየታየ መሆኑ ታውቋል። በአርስ በሚገኝ ቅዱስ ጆቫኒ ማርያ ቪያኒ ቤተክርስቲያን፣ ካርዲናል ኤሚል ቢያዬንዴ ለከፈተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ወደ ፈረንሳይ ሊዮን ከተማ በመጡበት ጊዜ ሳያቋርጡ ጸሎታቸውን ለቅረብ የሚሄዱበት ቤተክርስቲያን መሆኑ ሲታወቅ ወደ ፈረንሳይ በመጡ ቁጥር ቤተክርስቲያኑን ሲጎበኙት መቆየታቸውን የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ክቡር አባ ፓትሪስ ቾኮሎስኪ ገልጸዋል። ክቡር አባ ፓትሪስ በማከልም፣ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሥፍራው ተገኝተው ጸሎት ቤቱን መባረካቸው የቆሞሳትን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማጠናከር እና ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በኋላ በተለይም የአፍርካ ባሕሎች በቤተክርስቲያን ሕይወት ጎልተው እንዲታዩ የሚያደርግ፣ እንዲሁም የ21ኛው ክፍለ ዘመን የካህናት አገልግሎትን የበለጥ እንዲጠናከር የሚያግዝ መሆኑን ክቡር አባ ፓትሪስ ቾኮሎስኪ አስረድተዋል።
በሉርድ የሚደረግ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት፤
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሉርድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ነሐሴ 9/2012 ዓ. ም. የሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ ደንቦችን በማክበር የሚከናወን መሆኑን ክቡር አና ፓትሪስ አስታውቀዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ወደ ሉርድ ቤተ መቅደስ የሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉብኝት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ አድርገው ከሾሟቸው ከጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 2013 ዓ. ም. ወዲህ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሉርድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የሚያሳርጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የፍልሰታ ማርያም ማኅበርተኞች የሚያደርጉትን 147ኛ ዙር ብሔራዊ የንግደት ሥነ ሥርዓት የሚያስታውስ መሆኑ ታውቋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ይህን ዓመታዊ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍልሰታ መታሰቢያ ክብረ በዓልን በሥፍራው ተገኝተው ማክበር የማይችሉ ምዕመናን በማኅበራዊ መገናኛዎች በኩል በቀጥታ የሚተላለፈውን መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት መከታተል የሚችሉ መሆኑ ታውቋል።