በሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚደረግ የመንፈሳዊ ጉዞ ልምድ የወንድማማችነት መገለጫ ነው።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በየዓመቱ በካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የእያንዳንዱ ወጣት መልካም ተግባራት የሚታዩበት፣ ቸርነት እና እውነተኛ መንፈሳዊ እሴቶች የሚገለጡበት በዓል መሆኑን ትናንት ግንቦት 10/2013 ዓ. ም በቫቲካን ውስጥ የቀረበው የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል መርሃ ግብር አመልክቷል። መርሃ ግብሩን የተዘጋጀበትን ሰነድ በቫቲካን በማቅረብ ያስተዋወቀው በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል።
የኢየሱስ ንጉሥ ክብረ በዓል
ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በማከልም ዓመታዊው የወጣቶች ፌስቲቫል በሁሉም ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች የሚከበረው በኢየሱስ ንጉሥ በዓል ዕለት መሆኑን አስታውቋል። ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ምኞት በመጥቀስ እንደገለጸው የክርስቶስ ንጉሥ በዓል በሚከበርበት ወቅት መላዋ ቤተክርስቲያን የዓለም ወጣቶችን ወደ ፊት በማቅረብ ለወጣቶች የምታደረገውን ሐዋርያዊ እንክብካቤዎቿን፣ ጸሎቶቿን፣ ወጣቶች ነቁ ተዋናይ የሚሆኑባቸውን መድረኮች የምታመቻችበት አጋጣሚ መሆኑን ሰነዱ ገልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በየሦስት ዓመታቱ በተለያዩ አገራት በመገኘት የሚመሩት መደበኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ቢኖርም ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች በየዓመቱ በግል የሚያዘጋጁት እና በርካታ ወጣቶች የሚያሳትፉበት ብሔራዊ የወጣቶች ፌስቲቫል መኖሩ ይታወቃል።
ከወጣቶች ጋር ለሚደረግ ተልዕኮ ቅድሚያን መስጠት
በየዓመቱ የሚያዘጋጁ ብሔራዊ የወጣቶች ፌስቲቫል የሚሰጡት ጥቅም በዓሉ በሚከበርባቸው አገሮች ወጣቶች ብቻ ሳይሆን መላው ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ የሚያድግበት መሆኑን የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ሰነድ አመልክቶ መርሃ ግብሩ ወደ ሁሉም የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ የጳጳስት ሲኖዶስ እና ከፍተኛ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሀገረ ስብከቶች፣ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራት እና በመላው ዓለም ለሚገኙ ወጣቶች የሚደርስ መሆኑን አስታውቋል። የሐዋርያዊ አገልግሎት መርሀ ግብሩ ዋና ዓላማ በየሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ቁምስናዎች ለሚያዘጋጁት ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓላት ትልቅ ዋጋን ለመስጠት፣ ወጣቶች ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን በመስጠት ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን በፍሬያማነት እንዲወጡት ለማድረግ መሆኑን የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ሰነድ አመልክቷል።
የቤተክርስቲያን የተልዕኮ ልምድ የሚገለጽበት
በየዓመቱ የሚከበረው የወጣቶች ፌስቲቫል፣ ወጣቶች የእምነታቸውን ታላቅነት ተገንዝበው ደስታቸውን የሚገልጹበት እና በተመሳሳይ መንገድም ቤተክርስቲያን የወንጌል ተልዕኮ ልምዷን የምታካፍልበት እና የቅድስና ጥሪዋን በጥልቀት ለማስተንተን መልካም አጋጣሚ መሆኑን ሰነዱ አክሎ አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የክርስቲያናዊ ሕይወት ጉዞ ልምድ የሚታይበት፣ ሕያው እና ደስተኛ የእምነት ጎዳናን እና የኢየሱስን መልክ ውበት መመልከት የሚቻልበት አጋጣሚ መሆኑን ሰነዱ በተጨማሪ አስታውቋል። የወጣቶች ፌስቲቫል መርሃ ግብሩ ወጣቶች በጋራ የቤተክርስቲያን አንድነትን የሚረዱበት እና ራሳቸውም የአንዲት ቤተክርስቲያን አካል መሆናቸውን የሚያቁበት አጋጣሚ መሆኑ ታውቋል። በዚህም ወቅት ወጣቶች ከሁሉ አስቀድመው ማወቅ ያለባቸው ቤተክርስቲያናቸው የምታሰተምረውን ለማድመጥ ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ እንዳለባቸው ሰነዱ አሳስቧል።
ለወጣቶች የቀረበ ልዩ ግብዣ
በሀገረ ስብከቶች እና በቁምስናዎች የሚከበሩ ዓመታዊው የወጣቶች ፌስቲቫል፣ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ሃብቶቿን ለወጣቶች ለማካፈል ምን ጊዜም ዝግጁ መሆኗን በገሃድ የምትገልጽበት፣ ወጣቶችም ብቸኝነት እና የመገለል ስሜት ሳይሰማቸው የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለማድረግ መሆኑ ሰነዱ አመላክቷል። በመሆኑ ወጣቶች በሙሉ ዓመታዊ የወጣቶች ፌስቲቫልን በድምቀት ለማክበር ልዩ ጥሪ የተደረገላቸው መሆኑን እንዲያውቁ እና መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ ሃብቶችን በጋራ ለመካፈል የተጠሩ መሆናቸውን ሊያውቁ እንደሚገባ ሰነዱ አስታውቋል። የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ሰነድ በማጠቃለያው፣ በሀገረ ስብከቶች እና በቁምስናዎች የሚከበሩ ዓመታዊው የወጣቶች ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ለእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት እና ቁምስና ሕይወት ጠቃሚ ዕድሎችን በማዘጋጀት፣ ወጣቶች እርስ በእርስ ተገናኝተው የመንፈሳዊ ሕይወት ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት እና በጋራ የሚወያዩበት ሰፊ መድረክ መሆኑን አስታውቋል።