ካርዲናል ፓሮሊን፣ ረሃብን ለማስወገድ አዲስ ሞዴሎችን መከተል እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ምግብ ለሕይወት፣ ፍትሃዊነት ያለው የምግብ አቅርቦት እና ምግብ ለሁሉም” በሚል ርዕሥ በሦስት ዙሮች የተካሄደውን የአውታረ መረብ ሴሚናር በጋራ ያዘጋጁት የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት፣ በዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት እና በዓለም የግብርና ልማት ፈንድ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ክፍል፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቫቲካን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ምክር ቤት መሆናቸው ታውቋል።
የሴሚናሩ ዓላማ
የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማህበራዊ ሕይወት እና በሥነ-ምህዳር መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳየት ጥረት ያደረጉበት መንገድ መሆኑ ይታወሳል። በዚህ መንገድ በመመራት እና የማኅበራዊ ሕይወት ሥርዓቶችን በማክበር፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ለዓለማች ሕዝብ በቂ እና ፍትሃዊ የምግብ አቅርቦት እንዲኖር ያስፈልጋል በማለት በሴሚናሩ ወቅት ሃሳብ የቀረበ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ዓመታ ውስጥ በተለይም እ. አ. አ 2020 ዓ. ም. በዓለማች ውስጥ ከፍተኛ የምግብ እጥረት የታየበት እና በርካታ ሰዎች በረሃብ የተጠቁበት ዓመት እንድነበር ተገልጿል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በሴሚናሩ መዝጊያ ወቅት ባሰሙት ንግግር፣ በምግብ አቅርቦት ማንም ተለይቶ ለከፋ ረሃብ መዳረግ እንደሌለበት አሳስበው፣ ይህን በተግባር ለመተርጎም አዳዲስ የምግብ ምርት ማሳደጊያ ሞዴሎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ እና ጥበቃ ማድረግ፣ ረሃብን ማጥፋት፣ ሰብዓዊ ክብርን እና የጋራ ጥቅምን ማስደግ ይገባል ብለዋል።
በምግብ ስርዓቶች ላይ የሚደረግ ዓለም አቀፍ ጉባኤ
ከግንቦት 8 - 16/2013 ዓ. ም. ድረስ በቆየው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሳምንት ውስጥ በርካታ ዝግጅቶች መቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሴቶች ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ዕድል ያገኙበት፣ የየአካባቢዎቹ ቀደምት ነዋሪዎች በተለያዩ ዝግቶች እንዲሳተፉ የተደረጉበት፣ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችም በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ባጋጠማቸው ችግር ላይ እርስ በእርስ እንዲወያዩ እና የመፍትሄ ሃሳቦችን እንዲለዋወጡ መደረጉ ታውቋል። ዓላማው ይህ ብቻ ሳይሆን በሚመጣው ሐምሌ ወር የተባበሩት መንግሥታት ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ገንቢ እና የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲቀርቡ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በመጭው መስከረም ወር 2014 ዓ. ም በኒውዮርክ ከተማ የሚደረግ ሲሆን፣ በዚህ ጉባኤ ላይ የዓለም ምግብ ስርዓቶች የተመለከተ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።
የአገራት ኢኮኖሚዎች ማዕከላዊነት
በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የስነ ምጣኔ ሃብት ተመራማሪ የሆኑት እህት አሌሳንድራ ስመሪሊ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ዘላቂ የምግብ አቅርቦት ሥርዓትን ለማሻሻል የየአገራት የግል እና የጋራ ጥረት መደረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በሦስት ዙር የተካሄዱ የአውታረ መርብ ሴሚናሮችን ያስታወሱት እህት አሌሳንድራ በቂ የምግብ ምርት አቅርቦትን የሚያሳድጉ ገንቢ ሃሳቦች ከአገራቱ መሪዎች መቅረብ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። አክለውም ብዙን ጊዜ የጥቂት ሰዎች ፍላጎትን እና ምኞትን ለማሟላት ሲባል የሕዝቦች ድምጽ ሲታፈን ይታያል ብለዋል።
ሴሚናሩ የተመለከቷቸው ጉዳዮች
በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የስነ ምጣኔ ሃብት ተመራማሪ እህት አሌሳንድራ ስመሪሊ በሦስት ዙር የተካሄዱ ሴሚናሮችን መሠረት በማድረግ ባደረጉት ንግግራቸው ለማኅበራዊ ዕድገት በሚደረግ ጥረት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን፣ ለልማት ተቋማት የገንዘብ ድጎማ እንዲደረግላቸው፣ ገንዘብ፣ ሥራ እና ቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ክብር የማያስጠብቁ እና ለጋራ ጥቅም የማይውሉ ከሆነ ለተለያዩ ቀውሶች፣ ከእነዚህም መካከል በሰው ሕይወት ላይ አደጋን ለሚያስከትል የአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ምክንያት ይሆናሉ ብለዋል።