ብፁዕ ካርዲናል ቸርኒ በመልእክታቸው ስጋቶችን አስወግዶ እና ሰላምን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ!
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የዛሬው፣ በየጊዜው እየተለዋወጠ ያለው ዓለም መለያ ሲሆን "የጋራ ጥቅምን በትክክል የሚያገለግል፣ የማይገሰስ የሰው ልጅ እሴት የሚጠብቅ እና መሰረታዊ መብቶቻችንን የሚያጎለብት መሆኑን ለማረጋገጥ በጥንቃቄ መመርመርን ይጠይቃል።" በቫቲካን በቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ሐብት ልማት ለማስፋፋት የሚሰራው ጽሕፈት ቤት ዋና ጸኃፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ ሐሙስ ማለዳ ታኅሳስ 04/2016 ዓ.ም በቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያስተላለፉትን መልእክት ባቀረቡት ገለጻ ላይ ይህንኑ አስረድተዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሪ ቃል ለ57ኛው የዓለም የሰላም ቀን መልዕክታቸውን ሲያቀርቡ ፍትሃዊ እና ወንድማማችነት የሰፈነበት ዓለም ለመገንባት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመለየት የፈለጉትም ለዚህ ነው ብለዋል።
በኒውሮሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የአለም አቀፍ ፕሮጄክት አስተባባሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማቲዩ ጊለርሚን ከሊቀ ጳጳሱ መልእክት ጎን ለጎን አቅርበዋል ። በሮም የቴክኖ-ሳይንስ ሥነ-መለኮት እና ሥነ-መለኮት ትምህርት ምስጫ ተቋም ሉምሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ባርባራ ካፑቶ፣ በጣሊያን የቶሪኖ ፖሊቴክኒክ ፕሮፌሰር እና የአውሮፓ ላቦራቶሪ ለመማር እና የማሰብ ችሎታ ሲስተምስ ማህበር መስራች በስብሰባው ላይ ንግግር አድርገዋል።
የአንትሮፖሎጂካል (የስነ-ስብዕ) ተግዳሮቶች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.አ.አ በ2024 ለዓለም የሰላም ቀን ባስተላለፉት መልእክት “ኢእኩልነት፣ ኢፍትሐዊነት፣ ውጥረት እና ግጭት” ሊያስከትል የሚችለውን “በአጭበርባሪነት እና በጥቅም ብቻ የሚመራ ቴክኖሎጂን ጥበብ የጎደለው አጠቃቀምን” ትኩረት እንደሚስብ ብፁዕ ካርዲናል ቸርኒ ጠቁመዋል። አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኒካል ብቻ ሳይሆን ተግዳሮቶች እንዳሉት ከመልዕክቱ በመጥቀስ “ነገር ግን አንትሮፖሎጂካል፣ ማህበራዊ፣ ትምህርታዊ እና ፖለቲካዊ” እንዲሁም ለጦርነት አላማ መጠቀሙ አስፈሪ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ የተራቀቀ እና አጥፊ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ "የሰውን ሃላፊነት ከጦርነት ቦታ ማስወገድ" ይችላል ብለዋል።
ቴክኖሎጂ ላይ ትምህርት
"አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማህበራዊ ፍትህንም አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል" ሲሉ ብፁዕ ካርዲናል ቸርኒ ንግግራቸውን የቀጠሉ ሲሆን ምክንያቱም በስራ አለም ለምሳሌ "የእውቀት ማሽኖች" እና ሮቦቲክስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ስራዎችን እየጠራረገ እያጠፋ ነው፣ ይህም በድህነት ውስጥ ትልቅ አስተዋጾ እና ጭማሪ እንዲኖር ያደርጋል" ያሉ ሲሆን በመረጃው መስክ ግን "ሁለቱንም ቃላት እና ምስሎችን ለማጣመም አዳዲስ መንገዶች አሉ፣ ሆን ተብሎ የተሳሳተ መረጃ ለመስጠት እና ለማጭበርበር እና እነዚህም የሲቪል ስርዓቱን እና ዴሞክራሲያዊ መንግስትን በእጅጉ አደጋ ላይ ይጥላሉ"፥ እናም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳሉት በእዚህ ረገድ ትምህርት ወሳኝ ነው፣ "አልጎሪዝምን (ስልተ ቀመር) እና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን የሚነድፉትን ሰዎች የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰማቸው ማድረግ" እና "ሁሉም ሰው በተለይም ወጣቶች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አውቀው እንዲጠቀሙ እና በተለይም በድሆች እና በአካባቢው ላይ ስለሚኖራቸው ተጽእኖ በጥልቀት እንዲያስቡ ማሰልጠን" ይገባል በማለት ቅዱስነታቸው ለዓለም የሰላም ቀን ባስተላለፉት መልእክት ላይ መጥቀሳቸውን ካርዲናል ቸርኒ አክለው ገልጸዋል።
የቁጥጥር ፍላጎት
ካርዲናል ቸርኒ በመቀጠል "አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እድገትን እና አጠቃቀምን ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ለመቆጣጠር በአገራት ውስጥ ውጤታማ ደንቦች እንዲሁም የባለብዙ ወገን ስምምነቶች እና አስገዳጅ ስምምነቶች ያስፈልጋሉ" ብለዋል ። ለዚህም ነው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልእክታቸው ላይ የሀገር መሪዎች፣ የፖለቲካ ባለስልጣናት እና የሲቪል ማህበረሰብ መሪዎች በጋራ ሀላፊነት እንዲወጡ ያሳሰቡት እና ሁሉም ሰው “የተሻለ ሰላማዊ እና የተሻለ ዓለም ለወደፊት ትውልድ ለማስረከብ ከፈለግን በትኩረት እንዲከታተሉ እና ጥሩ ምርጫ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል” ብለዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መልእክት ለማስተዋወቅ እና ጭብጡን እና አንድምታውን በተሻለ ሁኔታ ለመፈተሽ እና ለመረዳት፣ በቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማትን ለማስፋፋት የሚሰራው ጽሕፈት ቤት በጣሊያንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በፖርቱጋልኛ፣ በስፓኒሽ እና በፈረንሣይኛ ቋንቋዎች በርካታ የመልቲሚዲያ መርጃዎችን እንዲሁም የመረጃ ቁሳቁሶችን እና ሥነ-መለኮታዊ አስተምህሮዎችን አዘጋጅቷል።