ጸሎት እና አስተንትኖ ጸሎት እና አስተንትኖ   ርዕሰ አንቀጽ

“ለመንጋው በሩን ፈጽሞ የማይዘጋ የእረኛው ልብ”

የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አስተምህሮን መሠረት ያደረገ፣ “በራስ መተማመንን መለመን” የሚል የወጣው አዲሱ ሠነድ፥ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሕይወትን የሚጋሩ ጥንዶች መንፈሳዊ ድጋፎችን ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል የሚያመቻች ነው። የቫቲካን መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ አዘጋጅ አንድሬያ ቶርኔሊ በዚህ ሠነድ ላይ በማሰላሰል የሚከተለውን ሃሳብ አካፍሎናል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስ አውግስጢኖስ ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ቃል በላቲን ቋንቋ ሲደግመው፥ “Nemo venit nisi tractus” ወይም፥ “ወደራሱ የሳበኝ አባቴ ካልጠራው በቀር ወደ እኔ የሚመጣ የለም” በማለት ጽፏል። በኢየሱስ ክርስቶስ መማረክን በማስመልከት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፥ እምነት እንዴት እንደሚስፋፋ እና በሂደቱ መካከል ዘወትር የመንፈሳዊ ጸጋ ተግባር መኖሩን በማስታወስ ተናግረዋል። ምንም እንኳን ደካሞች እና አቅመ ቢሶች ብንሆንም እግዚአብሔር ዘወትር ቀድሞ ወደ እርሱ ዘንድ እንድንጓዝ ይጠራናል፣ ይጋብዘናል፤ ወይም ቢያንስ ያንን እርምጃ የመውሰድ ፍላጎታችንን በውስጣችን ያቀጣጥላል።

የእግዚአብሔር ልብ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ወደ እርሱ ለሚቀርቡት፥ ታሪካቸው እና የሕይወት አካሄዳቸው ምንም ይሁን ምን፥ በረከትን ለማግኘት በትህትና ወደ እርሱ ለሚመጡት ሰዎች ደንታ ቢስ አይደለም። ከአርያም ምሕረት እና ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው እና ደካማነታቸውንም አውቀው ወደ እርሱ ለሚቀርቡት እግዚአብሔር የልቡን ብርሃኑን አያጠፋባቸውም።

በተዘበራረቀ ሕይወት ውስጥ ሆነው በትንሿ ቀዳዳ በኩል ቡራኬው እንዲደርሳቸው የሚለምኑ ሰዎች ጸሎት እና ጸጋውም ሥራ ላይ እንደሚገኝ የእግዚአብሔር ልብ በእርግጥ ይመለከታል። ስለዚህም የሰዎች የመጀመሪያ ጭንቀት ያችን ትንሿን ቀዳዳ መዝጋት ሳይሆን ከእነርሱ በፊት ያሉት ሰዎች እግዚአብሔር  ለሕይወታቸው ያለውን ዕቅድ በመረዳት ቡራኬውን እና ምሕረቱን መቀበል እና መማጸን ነው።

የዚህ መሠረታዊ ግንዛቤ ትርጉም፥ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የእምነት አስተምህሮ ጽሕፈት ቤት፥ “በራስ መተማመንን መለመን” በሚል ርዕሥ፥ መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች ሕይወትን የሚጋሩ ጥንዶች መንፈሳዊ ድጋፎችን ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል ማመቻቸት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ውስጥ በሚገባ ተንጸባርቋል። ለጥንዶቹ የሚሰጥ ይህ መንፈሳዊ ድጋፍ የሕይወት ምርጫቸውን ማጽደቅ ሳይሆን ወይም ከርቀት ሲያዩት ጋብቻን  ሊመስሉ የሚችሉ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶችን ወይም ሌሎች ዝግጅቶችን የማስወገድ አስፈላጊነትን ያስረዳል።

ይህ ሠነድ የጋብቻ ምስጢርን በማስመልከት የሚሰጠውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን በጥልቀት ይመረምራል።  ለሁለት ወንድ እና ሴት ተጋቢዎች የሚሰጥ የተክሊል ምስጢርን በድንገት ከሚሰጥ የጋብቻ ቡራኬ ይለያል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዛሬ አሥር ዓመት “የወንጌል ደስታ” በሚል ርዕሥ ይፋ ባደረርጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ቁ. 17 ላይ፥ “ቤተ ክርስቲያን የአባልነት ክፍያን የምትጠይቅ አይደለችም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ካለበት ችግሩ ጋር የሚኖርባት የእግዚአብሔር ቤት ናት” በማለት ጽፈዋል።

የሠነዱ ምንጭ ቅዱስ ወንጌል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞላ ጎደል በእያንዳንዱ የወንጌል ገጽ ላይ ወጎችን፣ ሃይማኖታዊ መመሪያዎችን እና ተግባራዊነታቸውን እንዲሁም ማኅበራዊ ስምምነቶችንም ጭምር  ይጥሳል። የሚመጻደቁትን እና እራሳቸውን ንጹሃን ብለው የሚጠሩትን፥ አንዱን ከሌላው ለማራቅ በሥርዓት እና በሕግ እራሳቸውን የሚከላከሉትን፣ የሚያራርቁትን፣ ሌሎችን የማይቀበሉትን እና በሮች እንዲዘጉ የሚያደርጉ ድርጊቶችን ይቃወማል። በሁሉም የወንጌል ገፆች ላይ የሕግ መምህራን የተቃውሞ ጥያቄዎች በማቅረብ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ጥግ ለማውጣት ሲሞክሩ እና ከዚያም ነፃነቱ በምሕረት በሚሞላበት ጊዜ በቁጣ ሲያጉረመርሙ፥ “ይህ ሰው ኃጢአተኞችን ይቀበላል፥ ከእነርሱ ጋርም ይበላል!” ሲሉ እንሰማለን።

ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አረማዊ ቤት በመግባት እራሱን ከሌሎች ጋር የሚያቀያይም መሆኑን ሳይፈራ በቅፍርናሆም የሚገኘውን የሚወደው አገልጋዩን ለመፈወስ ወደ መቶ አለቃው ቤት ሄደ። ኃጢያተኛዋ ሴት በእንግዶች ነቀፋ እና ንቀት መካከል እግሩን እንድታጥብለት ፈቀደላት። ለምን እንዳልከለካላት ሊገባው አልቻለም። በምሕረት ዓይኖቹ ከመመልከቱ በፊት ሕይወቱን እንዲለውጠው እና እንዲለወጥለት ሳይጠይቀው ከሾላው ቅርንጫፎች ላይ የተጠመጠመውን ቀራጩ ዘኬዎስን ተመልክቶት ጠራው። በሕጋቸው መሠረት በድንጋይ ተወግራ ልትሞት የነበረችውን አመንዝራይቱን ሴት አልኮነናትም። ነገር ግን ገዳዮቿን ትጥቅ በመፍታት እነሱም እንደ ማንኛው ሰው ኃጢአተኞች መሆናቸውን አስረዳቸው። ዘጠና ዘጠኙን በጎች ትቶ የጠፋውን አንድ በግ ሊፈልግ ከሄደው እረኛ ጋር ራሱን አነጻጸረ። ለታመሙት እንጂ ለጤነኞች አልመጣሁም አለ። ለምጻሙን በእጅ ለመንካት ከሚያስፈራ እና ከሰዎች ጋር እንዳይገናኝ ያደረገውን ደዌ በመንካት ፈወሰው። እነዚህ በሕዝቡ የተናቁት እና የተጣሉት በሙሉ በእርሱ ዕይታ የተወደዱ መሆናቸው ገባቸው። ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተሰጣቸውን ምሕረት ተቀበሉ። እንደተወደዱ እና ይቅርታ እንደተደረገላቸው አወቁ። ድሆች፣ ለማኞች፣ ኃጢአተኞች እና እንደ ማንኛውም ሰው መለወጥ የሚያስፈልጋቸው እንደ ነበሩ ተገነዘቡ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት ወር 2015 ዓ. ም. አዳዲስ ካርዲናሎችን በሾሙበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፡- “ኢየሱስ ክርስቶስ ሩቅ የሚገኙትን ማዳን፣ ቁስላቸውን መፈወስ፣ ሁሉንም ወደ እግዚአብሔር ቤት መመለስ ከሁሉ የሚበልጥ አገልግሎት ነበር። ይህን ማድረግ አንዳንድ ሰዎችን ያስፍራል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን የመሰለ ውርደት አይፈራም። በፈውስ ሥራው መካከል እንኳ ቢሆን ከየትኛውም ዓይነት ሃሳብ እና አስተሳሰብ ውጪ በሆነ ድርጊት፣ ለእነርሱ በሚገባቸው ማንኛውም የእንክብካቤ ወይም የርኅራኄ ምልክት የሚቆጡ እና የፈውስ ሥራውን የሚነቅፉ ዝግ አእምሮ ያላቸው ሰዎችን አይፈራም።

“ለዘመናት የዘለቀ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጋብቻ ትምህርት” በማለት አጽንኦትን የሰጠው ሠነዱ፥  በዚህ ቋሚ አስተምህሮ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አይደረግም፤ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል ባለው የጋብቻ አውድ ውስጥ ብቻ ተፈጥሯዊ የፆታ ግንኙነት ትክክለኛ እና ሙሉ ትርጉም ያገኛል” ሲል ገልጿል።

ስለዚህ ይህን ትክክለኛ የጋብቻ አስተምህሮን የሚቃረን አካሄድን ጋብቻ ብሎ ከመጥራት መቆጠብ ያስፈልጋል። ነገር ግን ከሐዋርያዊ እረኝነት እና ከወንጌል አገልግሎት አንጻር፥ መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች ሕይወትን የሚጋሩ ወይም መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ ቡራኬዎችን ለሚሹ ተመሳሳይ ጥንዶች መንፈሳዊ ድጋፎችን መስጠት የሚቻልበት መንገድ አልተዘጋም።

ክሎድ ሞንቴፊዮሬ የተባለ አንድ አይሁዳዊ ምሁር የክርስትናን እምነት ልዩነት እንዲህ በማለት ተናግሯል፥ “ሌሎች እምነቶች እግዚአብሔርን የሚፈልግ የሰው ልጅ በማለት ሲገልጹ፣ የክርስትና እምነት ግን የሰውን ልጅ የሚፈልግ አምላክ፥ ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢአተኛ ሰው ንስሐ እስኪገባ ድረስ እግዚአብሔር እንደማይጠብቀው እና ወደ ራሱ ሊጠራው እንደሚፈልግ አስተምሮአል” በማለት ገልጿል።

የተከፈተ የጸሎት በር እና መንፈሳዊ ድጋፍ ማድረግ፥ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሕይወትን የሚጋሩ ጥንዶችን ለማገዝ መልካም ጅማሬ ሊሆን ይችላል።

 

19 December 2023, 16:57