የቫቲካን ተከሳሾች በጠቅላላው የ37 ዓመታት እስራት የተፈረደባቸው መሆኑ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቫቲካን ፍርድ ቤት ችሎት ማጠቃለያ ላይ ከቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የገንዘብ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ በብፁዕ ካርዲናል ጆቫኒ አንጀሎ ቤቹ ላይ የበየነው ፍርድ ለንደን በሚገኘው ሕንፃ ግዢ እና ሽያጭ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ታውቋል። ቅዳሜ ታኅሳስ 6/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተላለፈው የቅጣት ውሳኔ መሠረት ብፁዕ ካርዲናል አንጀሎ ቤቹ በሦስት ክሶች ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል። በቀድሞው የቫቲካን ቁጥጥር እና ፋይናንስ መረጃ ባለስልጣን ፕሬዝደንት እና ዳይሬክተር በሆኑት አቶ ሬኔ ብሩልሃርት እና አቶ ቶማሶ ዲ ሩዛ ላይ የ1,750 ዩሮ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ፥ የቅድስት መንበር የፋይናንስ አማካሪ በነበሩት በአቶ ኤንሪኮ ክራሶ ላይ የሰባት ዓመት እስራት እና የአሥር ሺህ ዩሮ የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ በማስተላለፍ ከሥራ ገበታቸው እንዲነሱ ወስኗል። የገንዘብ ሃላፊ በነበሩት በአቶ ሩፋኤል ሚንቾኔ ላይ የአምስት ዓመት ከስድስት ወር እስራት፣ የስምንት ሺህ ዩሮ የገነዘብ ቅጣት በይኖ ከሥራ ገበታቸው አንስቶአቸዋል። ፍርድ ቤቱ በቅድስት መንበር የአስተዳደር ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ሠራተኛ በሆኑት በአቶ ፋብሪዚዮ ቲራባሲ የቅጣት ውሳኔ የሰባት ዓመት እስራት፣ አሥር ሺህ ዩሮ ቅጣት በመወሰን እና ከመሥሪያ ቤቱ አባልነት አግዶአቸዋል።
ጠበቃ አቶ ኒኮላ ስኩላስ በመሥሪያ ቤቱ ላይ ካደረሱት ጉዳት ጋር በተያያዘ፣ የአንድ ዓመት ከአሥር ወር እስራት እና ለአምስት ዓመት ከሥራ እንዲታገዱ ወስኗል። ፍርድ ቤቱ በማከልም፥ አሻሻጭ በነበሩት በአቶ ጃንሉዊጂ ቶርዚ ላይ የስድስት ዓመት እና የስድስት ሺህ ዩሮ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎ፥ ከሥራው ገበታቸው እንዲነሱ እና በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 412 መሠረት ለአንድ ዓመት በልዩ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ውሳኔ አስተላልፏል። የሥራ አስኪያጅ በነበሩት በወ/ሮ ቼቺሊያ ማሮኛ ላይ ሦስት ዓመት ከዘጠኝ ወር የእስር ቅጣት ከማስተላለፉ በተጨማሪም በሥራቸው ላይ ጊዜያዊ እገዳ በመጣል ድርጅታቸው ላይ የ40,000 ዩሮ ቅጣት ወስኖባቸዋል።
ታህሳስ 6/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ የተሰጠው ብይን ከ86 ችሎቶች በኋላ እንደሆነ ታውቋል። የቫቲካን ፍርድ ቤት ለንደን ውስጥ ስሎኔ ጎዳና ቁ. 60 በሚገኘው ሕንጻ ግዢ እና ሽያጭ ላይ በተመለከተ በዋነኛነት በብዙ ጉዳዮች በሚታወቁት አሥር ተከሳሾች እና አራት ኩባንያዎች ላይ የመጀመርያ ደረጃ ብይን ሰጥቷል።ፍርድ ቤቱ 200 ሚሊዮን ዶላር እና 500,000 የአሜሪካ ዶላር በሕገ ወጥ መንገድ ጥቅም ላይ መዋሉን ያረጋገጠ ሲሆን ይህም ቅድስት መንበር በጊዜው ከነበራት 1/3 ያህል መሆኑንም አረጋግጧል። የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ በዚህ መጠን በሕገ ወጥ መንገደ ክፍያ የተፈጸመው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2013 እና 2014 መካከል እንደ ነበር ታውቋል።
በጊዜው የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ምትክ የነበሩት ሊቀ ጳጳስ ጆቫኒ አንጄሎ ቤቹ፥ የአቴና ካፒታል ምርቶች በአክሲዮን ለመግዛት በአቶ ራፋኤሌ ሚንቾኔ ስም ያወጡት ገንዘብ ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንደ ነበር እና ለቁጥጥር ዕድል በማይሰጥ መንገድ መከናወኑ በባለ ሀብቱ ላይ ከፍተኛ አደጋን የሚፈጥር እንደ ነበር ታውቋል። በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ገንዘቡን ለመክፈል ከቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ሲያደርጉ የነበሩት ብፁዕ ካርዲናል አንጀሎ ቤቹ እና አቶ ራፋኤሌ ሚንቾኔ ከጽሕፈት ቤቱ ጋር ምንም እንኳን ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ በመተባበራቸው ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጧል። በሌላ በኩል የቫቲካን ዳኞች በፍትህ ሥርዓቱ በኩል ክስ የተመሠረተባቸውን ሌሎች የካርዲናል አንጀሎ ቤቹ፣ የክራሶ ኤንሪኮ እና የቲራባሲ ፋብሪዚዮ የማጭበርበር ወንጀሎችን ውድቅ አድርጓል።
የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2018-2019 ዓ. ም. መልሶ ግዥ ያካሄደባቸውን ንብረቶች በተመለከተ ከላይ የተጠቀሰውን ሕንፃ ለመግዛት ውስብስብ የፋይናንስ አሠራርን በመከተላቸው ፍርድ ቤቱ አቶ ጃን ሉዊጂ ቶርዚን እና አቶ ኒኮላ ስኩላስን በተባባሰ የማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ብሏል። እንዲሁም አቶ ቶርዚ፣ አቶ ቲራባሲ፣ አቶ ክራሶ እና ሚንቾኔ ከሽያጩ ጋር በተገናኘ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ተጨባጭ ጥፋት ያልተገኘባቸው በመሆኑ ነፃ አድርጓቸዋል።
አቶ ቲራባሲ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2004 እስከ 2009 ዓ. ም. ድረስ በዩቢኤስ ባንክ የተከፈለውን ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር ይዘው እራስን ለማሸሽ ባደረጉት ወንጀለኛ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል። ፍርድ ቤቱ ይህን ድምር ተከሳሹ በመቀበላቸው የሙስና ወንጀል እንደሆነ አረጋግቷል። አቶ ቶማሶ ዲ ሩዛ እና አቶ ሬኔ ብሩልሃርት በቅደም ተከተላቸው በጊዜው የቫቲካን ፋይናንስ ዋና ዳይሬክተር እና የቫቲካን የቁጥጥር እና የፋይናንስ መረጃ ባለ ስልጣን ፕሬዝዳንት ሆነው በሠሩበት ወቅት ለንደን ውስጥ በስሎን ጎዳና የሚገኘውን ሕንፃ ለመግዛት በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ጣልቃ በመግባታቸው ሁለቱንም ከወንጀል ነጻ አድርጓቸዋል።
በመጨረሻም ሌሎች ሁለት የምርመራ ዘርፎችን በሚመለከት፥ ብፁዕ ካርዲናል አንጀሎ ቤቹ እና ወ/ሮ ቼቺሊያ ማሮኛ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙበት የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት በድምሩ ከ570,000 ዩሮ በላይ በወ/ሮ ቼቺሊያን ስም ለኩባንያው እንዲከፈል መደረጉ እውነት የሌለው መሆኑን እና ነገር ግን ገንዘቡ አፍሪካ ውስጥ የታገቱ አንዲት ገዳማዊ እህት ነፃ የሚወጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የተከፈለ እንደ ነበር ገልጿል።
ብፁዕ ካርዲናል አንጀሎ ቤቹ 125 ሺህ ዩሮ ጠቅላላ ድምር በጣሊያን ኦዚዬሪ ሀገረ ስብከት ውስጥ ወንድማቸው ፕሬዝደንት ሆነው በሠሩበት የዕርዳታ ድርጅት ስም ሁለት ጊዜ ገንዘብ በማውጣታቸው ምክንያት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል። ምንም እንኳን ገንዘቡ ወጪ የተደረገበት ዓላማ ሕጋዊ ቢሆንም ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ በመዋሉ የሙስና ወንጀል መሆኑ ተገልጿል።
በአንፃሩ ተከሳሾቹ አቶ ሚንቾኔ፣ አቶ ቶርዚ፣ አቶ ቲራባሲ፣ ብጹዕ ካርዲናል አንጀሎ ቤቹ፣ አቶ ስኩሌስ፣ አቶ ክራሶ፣ አቶ ዲ ሩዛ እና አቶ ብሩልሃርት የተከሰሱባቸው ሌሎች ወንጀሎች በሙሉ ክሳቸው ተቋርጧል። ሞንሲኞር ማውሮ ካርሊኖም ከተከሰሱት ወንጀሎች ነፃ የተለቀቁ ሲሆን፥ በችሎቱ ላይ የተገኙት በርካታ ተከላካይ ጠበቆች ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።