ቫቲካን ሙስናን ለመከላከል የሚያግዝ የኢ-ሜይል አድራሻን ይፋ አደረገ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ረቡዕ ጥር 15/2016 ዓ. ም. ቅድስት መንበር ይፋ ያደረገችው አዲሱ ደንብ ግልጽነት የሌላቸውን የፋይናንስ እና የንብረት አጠቃቀሞችን ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በማሳወቅ ተገቢ እርምጃን ለመውሰድ የሚያግዝ ነው ተብሏል። አሠራሩ በቅድስት መንበር እና በቫቲካን ከተማ አስተዳደር የሕግ አፈጻጸም ላይ ያለውን ዕውቀት ለማካፈል እና በጠቋሚዎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ የመብት ጥሰቶችን በመከላከል ተጠያቂነትን ለማሳደግ እንደሚያስችል ተገልጿል። ቅድስት መንበር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 ዓ. ም. የተቀበለችው የተባበሩት መንግሥታት የፀረ ሙስና ስምምነት ከሌሎች ስምምነቶች ጋር ሙስናን ለመዋጋት ከሚረዱ ውጤታማ ከሆኑ መሣሪያዎች አንዱ ነው።
የቫቲካን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት መተዳደሪያ ደንብ እና “ወንጌል ስበኩ” የሚለው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ደንብ በጋራ ዋናው የኦዲተር መሥሪያ ቤቱ የገንዘብ ወይም የንብረት አጠቃቀምን እና ድልድልን የሚመለከቱ ሪፖርቶችን መቀበል እንዲችል ከመደንገጉ በተጨማሪ፥ የሥራ ውሎች ወይም ግብይቶች ሲፈጸሙ ሊከሰቱ የሚችሉ ግልጽነት የሌላቸው የሙስና ድርጊቶችን ለመከላከል እንደሚያግዙ ተገልጿል።
ጥንቃቄን የሚያሳድግ የኢሜይል አድራሻ
አካሄዱ፥ segnalazionianomalie@urg.va በሚለው የኢሜይል አድራሻ አማካይነት ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርቶችን ወይም ምስጢራዊ መልዕክቶችን በጽሁፍ መላክ የሚቻል መሆኑን ይገልጻል። ሪፖርት ሊያደርግ ያሰበው ሰው በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት የድምጽ ሪፖርትም ሊቅረብ እንደሚቻል እና ይህም ከዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ጋር በቀጥታ በመገናኘት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ሊከናወን እንደሚችል ተገልጿል። የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ በበኩሉ ምስጢራዊነትን እና ታማኝነትን በማክበር፥ የጠቋሚውን ደኅንነት በመጠበቅ ሪፖርቱን ለፍትህ ባለስልጣን ግልጽ የሚያደርገው ለምርመራ ወይም ለዳኝነት ተግባር ብቻ ነው ሲል አስታውቋል።
የጠቋሚውን ማንነት መጠበቅ
አሠራሩ በግልጽ እንደሚያሳየው፥ የጠቋሚውን ማንነት ወይም ስም በምስጢር መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሪፖርቱ ይዘት በተዘዋዋሪ ቢሆንም ከዚህም ጋር የተያያዘ ሠነድ ለማንም ይፋ ማድረግን የሚከለክል እንደሆነ ያመለክታል። መመሪያው በተጨማሪም በቅን ልቦና የተደረጉ ያልተለመዱ ተግባራትን ለዋና ኦዲተር ማቅረቡ ምስጢራዊነትን በመጣስ ወይም በሕግ፣ በአስተዳደራዊ እና በውል የተደነገጉ ደንቦችን ይፋ የማድረግ ገደብ በተመለከተ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት እንደማይፈጥር ይገልጻል።
ተገቢ ባልሆነ ተግባር ላይ ጥንቃቄን ማድረግ
ይፋ የሆነው የቅድስት መንበር ደንብ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሚቀርቡ ሪፖርቶች በጋራ ጥቅም ላይ ስጋትን ወይም ጎዳትን ሊያስከትሉ በሚችሉ ተገቢ ያልሆኑ ባህሪያትን እንደሚያሳስቡ ያብራራል። በሌላ በኩል ሪፖርቱ የጠቋሚውን ግላዊ ቅሬታዎችን የሚያንጸባርቅ ሳይሆን ነገር ግን በሥራ መደብ ላይ ያለውን ዲሲፕሊን እና የአሠራር ሂደቶችን የሚጠቅስ እና በተዋረድ ከሚገኙ ከፍተኛ የሥራ ባልደረቦች ጋር ያለውን ግንኙነት መመልከት እንደሌለበት ያሳስባል።
ደንቡ፥ ምንጫቸው የማይታወቁ ሪፖርቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው አፅንዖት የሰጠ ሲሆን፥ "የአሠራር ሂደቱ ቀደም ባሉት ዓመታት በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በኩል የተቀበሏቸው ሪፖርቶች የበለጠ አበረታች እንደሆኑ እና በተለይም በኤሌክትሮኒክ ቻናል በኩል ለመላክ ቀላል ያደርገዋል" ሲሉ የቫቲካን ዋና ኦዲተር አቶ አሌሳንድሮ ካሲኒስ ሪጊኒ ተናግረው፥ "አሠራሩ ተቀባይነት ያለው እና ያልተካተቱ ሪፖርቶች ስፋት እንዲሁም ከቅድስት መንበር እና ከቫቲካን ከተማ አስተዳደር ጋር በሕጋዊ መንገድ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት የሚያደርጉ አካላትም በሕጋዊ ርዕሠ ጉዳዮች እንደሚካተቱ ግልጽ አድርጓል" ብለዋል።
አቶ አሌሳንድሮ ካሲኒስ ቀጥለውም፥ በየጊዜው ግልጽ እየሆኑ የመጡት ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች በቅርቡ ከተሻሻሉት የኮንትራት ደንቦች ጀምሮ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከሌሎች የቅድስት መንበር አካላት እና ከመንግሥት የፀረ-ሙስና ባለስልጣን ጋር በመሆን የተቆጣጣሪነት ሚናውን በትክክል እየተወጣ ይገኛል" ሲሉ አስረድተዋል።