በቻይና ለተቋቋመው አዲስ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ጳጳስ መሰየሙ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቻይና አዲሱ የዌይፋንግ ሀገረ ስብከት በቅርቡ የተቋቋመ ሲሆን፥ አባ አንቶኒ ሳን ቬንጁን የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ሆነው የተሰየሙትም ሰኞ ጥር 20/2016 ዓ. ም. እንደ ነበር ታውቋል። ሁለቱም ውሳኔዎች ማለትም አዲሱን ሀገረ ስብከት ማቋቋም እና አባ አንቶኒ ሳን ቬንጁን የሀገረ ስብከቱ የመጀመሪያ ጳጳስ ሆነው የተሰየሙት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር 2015 ዓ. ም. ቢሆንም ለምዕመናኑ ይፋ የሆነው ሥነ-ሥርዓቱ በተካሄደበት ዕለት እንደ ሆነ ታውቋል። ሹመቱ የተካሄደው በቅድስት መንበር እና በቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መካከል ባለው ጊዜያዊ ስምምነት እንደሆነ ተገልጿል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ዓመት ሚያዝያ 12/2015 ዓ. ም. ለሀገረ ስብከቱ አዲስ ጳጳስ የሾሙት ለእግዚአብሔር መንጋ የሚቀርበውን የሐዋርያዊ አገልግሎት እንክብካቤን ለማሳደግ እና መንፈሳዊ ደኅንነቱ በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ ካለው ፍላጎት መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት አስታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ለማድረግ የወሰኑት፥ ቻይና ውስጥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 16/1931 ዓ. ም. ያቋቋሙትን የይዱክሲያን ሐዋርያዊ አስተዳደርን ወደ ሀገረ ስብከት ለማሳደግ ባደረጉት ውሳኔ መሠረት ሲሆን፥ የዋይፋንግ ግዛት አዲስ ሀገረ ስብከት እንዲሆን የተደረገው የጳጳስ መቀመጫ የሆነ የክርስቶስ ንጉሥ ካቴድራል በግዛቱ በሚገኘው በኪንግዡ ከተማ ውስጥ ስለሆነ ነው በማለት መግለጫው ገልጿል። መግለጫው በመቀጠልም፥ የአዲሱ ሀገረ ስብከት ድንበሮች የዊቸንግ፣ የሃንቲንግ፣ የፋንግዚ እና አራቱን የጋራ የልማት ዞኖችን የሚያካትት የኩዌን አካባቢ፣ የሊኑ እና ቻንግል አውራጃዎች፣ የቺንቹዎ፣ ዚቻንግ፣ ሾጓ፣ አንጁ ጎሚ እና ቼንጂ ከተሞችን እንደሚያካትት መግለጫው ገልጿል።
በዚህም መሠረት የዌይፋንግ ሀገረ ስብከት ከዋናው ከተማ ዌይፋንግ ጋር በመሆን በድምሩ 16,167.23 ኪ.ሜ. ስፋት ያለው እና በአጠቃላይ 9,386,705 ሕዝብ የሚገኝበት፥ ከእነዚህም ውስጥ በአሥር ካኅናት እና ስድስት ደናግል መንፈሳዊ አገልግሎቶችን የሚያገኙ ወደ 6000 የሚጠጉ ካቶሊካዊ ምዕመናን የሚገኙበት ሀገረ ስብከት እንደሆነ መግለጫው አክሎ አስታውቋል።
የቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት የአዲሱን ጳጳስ አጭር የሕይወት ተሞክሮን በማስመልከት ይፋ እንዳደረገው፥ አባ አንቶኒ ሱን ዌንጁን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ህዳር ወር 1970 ዓ. ም. ተወልደው፥ ከ1989 እስከ 1994 ድረስ ሻንጋይ ውስጥ በሚገኝ የሼሻን ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት መንፈሳዊ ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1995 ቤጂንግ ውስጥ በሺሺኩ ካቶሊክ ቁምስና ውስጥ ማዕረገ ክህነትን መቀበላቸው አስታውቆ፥ ቀጥለውም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2005 እስከ 2007 ዓ. ም. በሻንዶንግ ቁምስና ተከታታይ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2007 እስከ 2008 ዓ. ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ለክኅነት ማዕረግ የሚዘጋጁትን ተማሪዎች ለመከታተል የሚያግዝ ትምህርት በአየርላንድ ከቀሰሙ በኋላ ወደ ዌይፋንግ ተመልሰ አገልግሎት መስጠት መቀጠላቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።