የካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ “በችግር እና በለውጥ መካከል በሚገኝ ዓለማችን ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ” በሚል ርዕሥ አዳዲስ ስልጠናዎችን ማዘጋጀቱን አስታውቋል።ስልጠናው የሚቆየው ከጥር 11 እስከ መጋቢት 14/2016 ዓ. ም. ድረስ ሲሆን፥ የሚሰጠውም በክፍል ውስጥ እና በመስመር ላይ እንደሆነ፥ ስልጠናውንም የሚመሩት ሞንሲኞር ጋይ-ሪያል ቲቪየር እንደሆኑ ተገልጿል።
ከጥር 11 እስከ መጋቢት 14/2016 ዓ. ም. ድረስ የሚቆየው ይህ ስልጠናው የሚጀመረው ሮም ውስጥ በሚገኝ “ካሳ ቦነስ ፓስተር” ማዕከል ሲሆን፥ ስልጠናውን መርቀው የሚያስጀምሩትም የፋውንዴሽኑ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ሐና ታራንቶላ እንደሚሆኑን ተነግሯል። በጎርጎሮሳውያኑ አዲሱ ዓመት 2024 ዓ. ም. የሚሰጠው ይህ ከፍተኛው ሥልጠና፥ የካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮ ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶችን የበለጠ ለማስከበር እና የሰላም መንገዶችን ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን በጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ ድረ ገጽ ላይ የታተመ የሞንሲኞር ጋይ-ሪያል ቲቪየር መልዕክት ያስረዳልል።
የሚሰጡ ትምህርቶች እና ዋና ተካፋዮቹ
ሦስት ደረጃዎች እንዳሉት የስልጠናው መርሃ ግብር ገልጾ፥ እነርሱም ጥልቅ፣ አስተዋይ እና የማኅበረሰብን ጥበብ መሠረት ያደረጉ እንደሆነ ታውቋል። እነዚህ ስልጠናዎች ላለፉት በርካታ ዓመታት ወደ ሥራው ዓለም ለመግባት የሚዘጋጁ የመንግሥት እና የግል ተወካዮችን፣ ባለሙያዎችን፣ ምሁራንን፣ ሥራ ፈጣሪዎችን፣ የይማኖት አባቶችን እና ወጣት ተማሪዎች በማሰልጠን ላይ ያተኮሩ እንደ ነበር ተነግሯል።
የስልጠናው ዋና ዓላማ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መርሆች እና ልምዶችን ማስተማር ሲሆን፥ በስልጠናዎቹ አማካይነት ፋውንዴሽኑ፥ በዓለማችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እውነታዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አሳቢ እና የተቀናጁ ማኅበረሰቦችን ለመገንባት እንደሚፈልግ ታውቋል።
የስልጠናው አወቃቀር
ሦስት የክፍል ውስጥ እና አራቱ የመስመር ላይ የስልጠና ክፍለ-ጊዜያት ያሏቸው ሰባቱ ሞዴሎች፥ በሰው ልጅ ጠቅላላ ዕድገት፣ ማኅበራዊ ወዳጅነት እና ትብብር ላይ እንደሚያተኩሩ ታውቋል። በክፍል ውስጥ የሚሰጡ ስልጠናዎች ሮም ውስጥ በሚገኝ “ካሳ ፓስተር ቦነስ” በተባለ ማዕከል ውስጥ ሲሆን፥ መስመር ላይ የሚሰጥ ስልጠና በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከ6፡30 pm እስከ 8፡30 pm (GMT+1) እንደሚካሄድ ተገልጿል።
እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ በተለያዩ የካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮዎች እና በኢኮኖሚ፣ በገንዘብ እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ንግግር በሚያደርጉ ባለሞያዎች የተዋቀረ እንደሆነ ታውቋል። በስልጠናው ወቅት ነጻ የንግግር እና የውይይት ጊዜን እና የቡድን ሥራን የሚያካትት እንደሚሆን ተገልጿል።
ለገዳማውያን እና ገዳማዊያት ስልጠናው በነፃ የሚሰጥ ሲሆን፥ ወጣት ተሳታፊዎች ቀደም ብለው ጥያቄያቸውን ለፋውንዴሽኑ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ካቀረቡ በክፍያው ቅናሽ ሊደረግላቸው እንደሚችል ተገልጿል።
የስልጠናዎቹ ርዕሦች
የስልጠናዎቹ ርዕሦች፥ መግቢያን፣ የሥራ ዘዴን እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሠረቶችን የሚያካትቱ ሲሆን፥ ሁለተኛው ክፍለ ጊዜ በባሕል እና ማኅበረሰብ ላይ እንደሚያተኩር፥ ሦስተኛው ክፍለ ጊዜ በፖለቲካ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር፥ አራተኛው ክፍለ ጊዜ አዳዲስ ተግዳሮቶችን እና መንገዶችን በሚመለከቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሃላፊነቶች ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል።
አምስተኛው ክፍለ ጊዜ፥ መገናኛን እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የሚዳሥ ሲሆን፥ ስድስተኛው ክፍለ ጊዜ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን፣ ሰባተኛው ክፍለ ጊዜ ማኅበራዊ ለውጦችን እና ትምህርትን እንደሚመለከት ታውቋል።