ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ፥ የጋዛ ክርስቲያኖች በከፍተኛ ችግር እንደሚንገላቱ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሰኞ ጥር 6/2016 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተው የተወያዩት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ፥ የጋዛ ክርስቲያኖች መኖሪያ ቤታቸው ስለወደመባቸው፣ ውሃ እና መብራት ስለሌላቸው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀዋል ብለዋል።
ከቅዱስነታቸው ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም፥ በጋዛ እና በቅድስት አገር ስለሚገኝ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ሁኔታ፣ በክልሉ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የጋራ ውይይት እና የሰላም ተስፋዎችን በማስመልከት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
የጋዛ ክርስቲያኖች የሚገኙበት ሁኔታ
ብጹዕ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ከጋዜጠኞች ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፥ የጋዛ ክርስቲያኖች እንደሌላው ሕዝብ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረው፥ ከሌላው የአካባቢው ሕዝቦች የተለዩ ባለመሆናቸው ምንም እንኳን በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም ያጋጠማቸው ችግር መላውን የአካባቢው ሕዝብ እያጋጠመው ያለው ችግር አካል ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ብጹዕ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ አክለውም ከጋዛ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር በመደበኛነት እየተገናኙ መሆናቸው ገልጸው፥ በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል ያነሰ ውጊያ መኖሩን አስረድተዋል። ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በደቡብ የጋዛ አካባቢዎች መኖራቸውን ፓትርያርኩ ገልጸው፥ ነገር ግን አካባቢው ምንም ነገር የሌለበት፣ በእስራኤል ጥቃት ቤቶች የወደሙበት፣ ተቋማት የፈረሱበት፣ ውሃም ሆነ መብራት የሌለበት እና እጅግ የከፋ ድህነት የሚታይበት አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።
ዮርዳኖስ ለሰብዓዊ ተልዕኮ መሠረት ናት
ባለፈው ሳምንት ከቆዩበት ከዮርዳኖስ ወደ ጣሊያን የመጡት ብጹዕ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ፥ "በዮርዳኖስ ያለው ሁኔታ ውስብስብ ቢሆንም ነገር ግን ከፖለቲካዊ እና ሰብዓዊ ሁኔታ አንፃር ዮርዳኖስ የተረጋጋች ብቸኛዋ አገር ናት” ብለው፥ "ለጋዛ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ መጠየቅ ስንፈልግ መሄጃችን የዮርዳኖስ ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ነው" በማለት ተናግረዋል።
ከዮርዳኖስ ንጉሥ አብደላህ ጋር፣ ከዮርዳኖስ መንግሥት እና ከተለያዩ ተቋማት ተወካዮች ጋር መነጋገራቸውን የገለጹት ብጹዕ ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ፥ ጋዛ ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ባለሥልጣናት ጋር የመገናኛ መስመሮች መቆየት ወይም አለመቆየት እናያለን" ብለዋል። ዮርዳኖስ በአሁኑ ወቅት ለቤተ ክርስቲያናቸው ተያዥ እንደሆነች እና ከሰብዓዊ ድርጅቶች እና ከግብፅ ጋር መጠነኛ ትብብር መኖሩን አስረድተዋል።
የጋራ ውይይት መቀጠል አለበት
በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ቀላል አለመሆኑን፣ ለችግሩ ፈጣን መፍትሄ ማግኘት እንደማይቻል እና በየደረጃው ማሰብ እንደሚገባ፥ አሁን አስፈላጊው ነገር በሁለቱ ወገኖች ማለትም በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የግንኙነት መስመሮችን መፈለግ እንደሚገባ፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም ለዚህ ግብ በርትታ መሥራቷን እንደምትቀጥ በኢየሩሳሌም የላቲን የአምልኮ ሥርዓት የምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ በሮም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል።