ሊቀ ጳጳስ ቪንቼንዞ ፓግሊያ በህንድ ኬረላ ግዛት ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ ሊቀ ጳጳስ ቪንቼንዞ ፓግሊያ በህንድ ኬረላ ግዛት ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ 

ሊቀ ጳጳስ ፓግሊያ ቤተክርስቲያን የቤተሰብን ሥነ-መለኮታዊ አኗኗር መመርመር አለባት አሉ

የጳጳሳዊ የሕይወት አካዳሚ ፕሬዝደንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ቪንቼንዞ ፓግሊያ የሕንድ ኬራላ ግዛትን ጎብኝተው፥ የቤተሰብ ሃዋሪያዊ እንክብካቤ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰጠውን ስልጠና አስጀምረዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሊቀ ጳጳስ ቪንቼንዞ ፓግሊያ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያለው ሥነ-መለኮታዊ ነጸብራቅ በቂ አለመሆኑን በመግለጽ የቤተሰቡ ወንጌል እንደገና እንዲታወጅ ጠይቀዋል።

ሐሙስ ዕለት በደቡባዊ የህንድ ክልል የምትገኘውን የኬራላ ግዛት ከተማ በሆነችው በቻንጋናሴሪ ከተማ ተገኝተው፥ የዮሃንስ ጳውሎስ ሁለተኛ የጋብቻ እና ቤተሰብ ጥናት ተቋም ባዘጋጀው የቤተሰብ ሃዋሪያዊ ሥራ ባለሙያዎች ኮርስ መክፈቻ ላይ ንግግር አድርገዋል።

ሊቀ ጳጳስ ፓግሊያ በንግግራቸው ወቅት እንዳሉት “ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አስተዳደር እና በአሁኑ ጊዜ ከተደረጉት ታላላቅ ለውጦች ጀምሮ፥ ሥነ-መለኮት የቤተሰብን ርዕሰ ጉዳይ በበቂ እና በአዲስ መልክ የመግለጽ አዲስ ፈተና ገጥሞታል” ብለዋል።

በባል እና ሚስት ህብረት እንዲሁም በእጮኛሞች ፍቅር ላይ በሕጋዊ-ቀኖናዊ አመለካከት ብዙ ጥናት ቢደረግም እንደ ግንኙነት አካል ተደርጎ የሚወሰደው አጠቃላይ የቤተሰብ ሥነ-መለኮት እስካሁን ሙሉ በሙሉ እንዳልተዳሰሰ ጠቁመዋል።

ቤተሰብ፡ ‘የጋብቻ ፍሬያማነት ቦታ’

አዲስ እየተሰጠ ያለው ኮርስ የጋብቻ ሥነ-መለኮትን በሰዎች ዘንድ ለማስረፅ እና የቤተሰብን አስፈላጊነትን የክርስቲያኖች ወደሆነው የቅዱስ ቁርባን ፍሬያማነት ቦታ ለመመለስ ይፈልጋል ተብሏል።

ሊቀ ጳጳስ ፓግሊያ እንዳሉት የዚህ ኮርስ ግብ ቤተሰብን እንደ ጋብቻ ውጤት ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ባለው እድገት እና መስፋፋት ልክ መመርመር ነው ብለዋል።

የጳጳሳዊ የሕይወት አካዳሚ ፕሬዝደንቱ አክለውም እንደተናገሩት “በወንድና በሴት መካከል ያለውን ልዩነት ለማስወገድ” እየተኬደ ያለውን ማኅበረሰባዊ አዝማሚያ በመተቸት፥ ውጤቱ “ለሁሉም ሰው ኪሳራ ነው” በማለት ገልጸዉታል።

ይሄንንም ሃሳብ ሲያጠናክሩት “የመጽሐፍ ቅዱሳዊው መልእክት ግልጽ ነው፡ ወንድና ሴት ከእግዚአብሔር የመጡ ናቸው፥ እናም አንድ ላይ የተጣመሩ ስለሆኑ እርስ በርሳቸው የማይነጣጠሉ ናቸው” ሲሉ ተናግሯል። በመቀጠልም “አንዱ ያለ ሌላው መኖር አይቻልም፥ በወንድ እና ሴት መካከል ያለው ተፈጥሮአዊ ልዩነት እንደ መፅሃፍ ቅዱሳዊ ሰብአዊነት እይታ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው” ብለዋል።

እንዲሁም ቤተክርስቲያን ከልጆቿ ጋር ያላትን የማይፈርስ ትስስር፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተክርስቲያን ጋር ካለው ትስስር ጋር በማመሳሰል፥ እግዚአብሔር ለኃጢአተኞች ያለውን የማያወላውል ፍቅር በማሳየት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ቤተክርስቲያን

የብጹእ አቡነ ፓግሊያ የህንድ ጉብኝት አርብ ዕለት በመቀጠል፥ በባንጋሎር ከተማ በሚካሄደው የህንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ምልአተ ጉባኤ ላይ እንደሚሳተፉም ተነግሯል።

በዚህ ጉባኤ ላይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም በአማሪኛ ትርጉሙ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፥ ለቤተክርስቲያን እና ለሰው ልጆች ስላለው አንድምታ ላይ ንግግር እንዲያደርጉም ቀጠሮ ተይዞላቸዋል ተብሏል።
 

02 February 2024, 12:22