ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም የሚገኘውን ባምቢኖ ጄሱ ሆስፒታልን በጎበኙበት ወቅት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም የሚገኘውን ባምቢኖ ጄሱ ሆስፒታልን በጎበኙበት ወቅት 

ጦርነትን ለሸሹ የዩክሬን ሕጻናት ለሁለት ዓመታት እንክብካቤ ሲደረግላቸው መቆየቱ ተገለጸ

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ካካሄደችበት ከሁለት ዓመት ወዲህ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ወደ 2,500 የሚጠጉ አዳጊ ሕጻናት ሮም ውስጥ በሚገኝ “ባምቢኖ ጄሱ” ካቶሊክ ሆስፒታል ውስጥ ሕክምናን ለማግኘት መግባታቸው ታውቋል። ከእነዚህ አዳጊ ሕጻናት መካከል የመጀመሪያው ሰለባ በሮም አቅራቢያ ወደሚገኝ ዋና ማዕከል የካቲት 22/2014 ዓ. ም. መድረሱ ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የመጀመሪያው የቦምብ ጥቃት በኪዬቭ ከተማ ከደረሰ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ “ባምቢኖ ጄሱ” የሕጻናት ሆስፒታል የጦርነቱ ሰለባ ሕጻናትን ተቀብሎ የሕክምና ዕርዳታ ማቅረብ መጀመሩን እንዳስታወቀ ይታወሳል። ሆስፒታሉን በባለቤትነት ለአንድ መቶ ዓመታት ይዛው የቆየችው ቅድስት መንበር ከዚህ የመጀመሪያው ሕጻን ጀምሮ ከ 2,500 በላይ የሚሆኑ የዩክሬን አዳጊ ሕጻናት የሕክምና ዕርዳታ ተደርጎላቸዋል።

ለሁለት ዓመታት ያህል የተሰጠው የቀዶ ጥገና እና ልዩ ሕክምና አገልግሎት

በዩክሬን በተካሄደው የሁለት ዓመት ጦርነት ለተጎዱት ሕጻናት ለ730 ቀናት ያህል የተካሄዱ ልዩ ልዩ የቀዶ ጥገና ሕክምናዎች፣ የድንገተኛ አደጋ ዕርዳታዎች፣ የነርቭ ወይም የካርዲዮሎጂ ሕክምናዎች እና የሕዋስ ቴራፒ የመሳሰሉ ሕክምናዎች በሕጻናቱ ላይ የሚታዩትን ሕመሞች ለመፈወስ ችለዋል። በጡንቻ ሕመም ይሰቃይ የነበረው የ 12 ዓመቱ ዩክሬናዊ ሕጻን ጣሊያን ውስጥ ዕርዳታን ካገኙት የመጀመሪያዎቹ ታካሚዎች መካከል አንዱ ነው።

ከምግብ እና ከመድኃኒት አቅርቦት መካከል አንዱን እንዲመርጥ የተገደደው የዩክሬን ሕዝብ፥ እነዚህን የተለያዩ ሕክምናዎችን በሀገር ውስጥ ማግኘት እንደማይችል እና አስቸጋሪ እንደ ነበር ይታወቃል። የ “ባምቢኖ ጄሱ” ካቶሊካዊ የሕጻናት ሆስፒታል በአውሮፓ ውስጥ የጀመረውን የአውታረ መረብ ተልዕኮን በርቀትም ቢሆን ከባድ እና አዳዲስ በሽታ ላለባቸው ሕፃናት የምርመራ እና የሕክምና ዕርዳታን እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥሪ ፈጣን ምላሽ መስጠቱ ታውቋል። ሆስፒታሉ በአውሮፓ ውስጥ በሂደት የተዘገቡትን እና በዩክሬን ሕጻናት ላይ ይታዩ የነበሩ አዳዲስ ሕመሞችን ለማከም ዘወትር ቦታን አዘጋጅቶ ይጠብቃል።

"ባምቢኖ ጄሱ" የሕጻናት ሆስፒታል
"ባምቢኖ ጄሱ" የሕጻናት ሆስፒታል

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የመጋቢ ወር 2014 ጉብኝት

ከመጋቢት 10/2014 ዓ. ም. ጀምሮ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሆስፒታሉ እንክብካቤ የሚደረግላቸው 50 ሕፃናት እንደ ነበሩ ሲታወስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጦር ግንባር ወይም በመንግሥተ ሰማያት የነበሩ ወላጆች ልጆች ለሆኑት ሕሙማን ሕጻናት በሙሉ አባትና አያት በመሆን "የአባቶችን ቀን" ለማክበር መወሰናቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ከሰዓት በኋላ በሮም ከተማ ውስጥ ወደሚገኘ የሕጻናት ሕክምና መስጫ ዋና ማዕከል በመሄድ በጊዜው የማዕከሉ ፕሬዝደንት በነበሩ ወ/ሮ ማሪኤላ ሄኖክ ታጅበው ጦርነቱን ሸሽተው ለመጡት አሥራ ሁለት የዩክሬን ሕጻናት ሰላምታ ማቅረባቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በተለያዩ ሕመሞች ለሚሰቃዩ ሕጻናት ቡራኬአቸውን፣ ስጦታቸውን እና የአባትነት ፍቅራቸውን በመግለጽ ጦርነቱ የወሰደባቸው ፈገግታ እንዲመለስ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ከዩክሬን ቀዳማዊት እመቤት የተለከ መልዕክት

ለ “ባምቢኖ ጄሱ” የሕጻናት ሆስፒታል የሚሰጠው የማገገሚያ አገልግሎት አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ እና ስነ ልቦናዊ እንደሆነ፥ የዩክሬን ቀዳማዊት እመቤት ኦሌና ዘለንስካ ለሆስፒታሉ ፕሬዝደንት ማሪዬላ ሄኖክ በፃፉት መልዕክት ገልጸው፥ የጤና እንክብካቤው ለህፃናት ብቻ ሳይሆን ለእናቶቻቸው እና ለአያቶቻቸውም ጭምር እንደሆነ፥ ሕጻንን ከበሽታ ማዳን ከባድ እንደሆነ እና በጦርነት ወቅት ይህን ማድረግ የበለጠ አድካሚ እንደሆነ ገልጸው፥ ሕክምና ላይ የቆዩ ሴት ሕጻናት እንደገና ወደ ፈገግታቸው እንደሚመለሱ እርግጠኛ በመሆን፥ የፕሬዝደንት ማርዬላ ሄኖክ ጥረትም ይህ እንደሆነ ያላቸውን እምነት በመልዕክታቸው ገልጸውላቸዋል። 

የእናት አይሪን ዘፈን

ከእነዚህ የሕጻናቱ እናቶች እና አያቶች መካከል ፈገግታቸውን መልሰው ካገኙት መካከል አይሪን አንዷ ሲሆኑ፥ በዩክሬን በሚገኝ የመዋለ ህፃናት ማዕከል ውስጥ ከልጆች ጋር ትሠራ የነበረች ዘፋኝ እና የፒያኖ መምህርት አይሪን፥ ጣሊያን ውስጥ ወደ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል የመጡት ሕጻናት ደኅንነት የተጠበቀ መሆኑን በመግለጽ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ባህላዊ የዩክሬን ዘፈኖችን በኮንሰርት መልክ ለማዘጋጀት መፈለጓን ገልጻለች።

ልብን መክፈት

"ለሚሰቃዩት ዘወትር ቅርብ ነው" የሚለው መፈክር በ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል ሠራተኞች በኩል የተነገር ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በተጨባጭ የተገለጸ እንደሆነ ተመልክቷል። ይህ ተጨባጭ የሕክምና አገልግሎታቸው በጥር ወር 2015 ዓ. ም. ሆፒታሉን በጎበኙት የአብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ልዑካን አድናቆት ተሰጥቶታል።  

በዩክሬን የሚገኙ ዋና ዋና የእምነት ቤቶች ተወካዮች ለወገኖቻቸው የተደረገላቸውን እንክብካቤ ከተመለከቱ በኋላ የልዑካን ቡድኑ መሪ እና በዩክሬን የአርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሀገረ ስብከት ጳጳስ ማርኮስ በንግግራቸው፥ “የጤና ባለሞያዎቹ የሆስፒታሉን በር ብቻ ሳይሆን ልቡንም ጭምር ከፍተዋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

"ባምቢኖ ጄሱ" የሕጻናት ሆስፒታል
"ባምቢኖ ጄሱ" የሕጻናት ሆስፒታል

 

 

 

 

 

26 February 2024, 16:19