በካህናት የወንጌል አገልግሎት ዝግጅት ላይ የሚወያይ ጉባኤ በቫቲካን ተጀመረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
"በውስጣችሁ ያለውን የእግዚአብሔር ስጦታ አንቁ" በሚል መሪ ርዕሥ ከማክሰኞ ጥር 28 እስከ የካቲት 2/2016 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን የሚካሄደውን ጉባኤ ከዓለም ዙሪያ ከስልሳ አገራት የተወጣጡ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ካህናት የሚካፈሉት ሲሆን፥ በኅብረት ሆነው ያዘጋጁትም በቅድስት መንበር የቤተ ክኅነት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ናቸው።
ቀሳውስትን የመንከባከብ ተልዕኮ
ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ላዛሩስ ዩ ሄንግ-ሲክ ስሆኑ፣ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ባሰሙት ንግግር፥ በርካታ ካህናት በዛሬው ኅብረተሰብ ውስጥ በሚያጋጥሟቸው ችግሮችና በሚሸከሙት ሸክም በመድከም ተስፋ መቁረጣቸውን ተናግረው፥ ስለዚህም “ለካህናት አስፈላጊውን ድጋፍ የማድረግ እና ቀጣይነት ያለውን ስልጠና የመስጠት አስፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል” ብለዋል።
የጉባኤው የሲኖዶሳዊነት ድባብ
ብጹዕ ካርዲናል ሄንግ-ሲክ ለጉባኤው ተሳታፊዎች እንደተናገሩት፥ ካኅናቱ በጉባኤው ላይ የተገኙት ለመማር ብቻ ሳይሆን ዋና ተዋናዮች መሆናቸውን ከጉባኤ ዝግጅት መጀመሪያ አንስቶ ሲናገሩ እንደ ነበር ገልጸው፥ እያንዳንዱ ካኅን ወደ ጉባኤው ሲመጣ ጥበቡን እና ልምዱን ይዞ እንደመጣ ገልጸዋል።
በጣሊያን የምዕመናን ማኅበረሰብ አንቂ ካኅን አባ ኦሬስቴ ቤንዚ በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ከሌሎች ምንም የማይቀበል ሀብታም ወይም ለሌሎች ምንም መስጠት የማይችል ድሃ የለም” ማለታቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሄንግ-ሲክ፥ ጉባኤው በተቻለ መጠን የአውደ ጥናት ዘይቤን በመከተል አሳታፊ እና ሲኖዶሳዊ አካሄድ እንዲኖረው አሳስበዋል።
ለባሕላዊ ዕውቀት ማዘጋጀት
ጉባኤው ካዘጋጁት የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች መካከል ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ ጉባኤው ከመጀመሩ በፊት ባሰሙት አጭር ንግግር፥ ከሁሉ አስቀድሞ ካኅናት የክኅነትን ምስጢር ከተቀበሉ በኋላ ዕውቀታቸውን ማሳደግ የሚያበቃ አድርገው እንዳያስቡ አሳስበው፥ “ይልቁንም በትክክል ለእግዚአብሔር እና ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተሾምን በመሆናቸን ያለማቋረጥ በዕውቀት ማደግ አለብን” ብለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ በማከልም፥ “በሁለተኛ ደረጃ ካህናት ባሕላቸውን ብቻ የማትኮር እና የማስከበር ዝንባሌን ለማሸነፍ ቀጣይነት ያለው ትምህርት ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል። ለክኅነት አገልግሎት የተሾሙት ካህናት ባሕላቸውን ለማድነቅ የባሕል ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል ብለው፥ ነገር ግን ባሕላቸው ውድቀት እንደሚያጋጥመው በማመን በሌሎች ባሕሎች ውስጥ ያሉትን መልካም ነገሮች ማወቅ አለባቸው ብለዋል ።
ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ በመጨረሻም፣ ብዙ ካኅናት በእጅጉ ለሚሰቃዩት ሰዎች ቅርብ እንደሆኑ ወይም ራሳቸውም ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸው፣ በቀላሉ ወደ በቀል፣ ወደ ቂመኝነት እና ወደ ጥላቻ ሊመሩ የሚችሉ ቁስሎችን እና ሕመሞችን የሚፈውስ የክኅነት ዝግጅት ሊኖር እንደሚገባ ጠይቀዋል።