ለጸሎት ዓመት የተዘጋጀ መመሪያ ለጸሎት ዓመት የተዘጋጀ መመሪያ 

በቫቲካን የወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ለጸሎት ዓመት የሚሆን መመሪያን አዘጋጀ

በቫቲካን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፥ ቤተ ክርስቲያን የኢዮቤልዩ በዓልን ለማክበር በምትጋጅበት በዚህ ወቅት፥ "ጌታ ሆይ! መጸለይን አስተምረን" በሚል አርዕሥት የተዘጋጀ የጸሎት መመሪያን ይፋ አደረገ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያደርጉትን ግላዊ የጸሎት ውይይት እንዲያጠናክሩ እና በዛሬው ዓለም ውስጥ ባላቸው እምነት እና ቁርጠኝነት ላይ እንዲያሰላስሉበት ግብዓት የሚሆን አዲስ የመመሪያ መጽሔት ይፋ አድርጓል።

"ጌታ ሆይ! መጸለይን አስተምረን" በሚል ርዕሥ የታተመው አዲሱ መመሪያው፥ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. ለምታከብረው የኢዩቤልዩ ክብረ በዓል ዝግጅት እንዲሆን ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ከሚያቀርባቸው ተከታታይ ግብዓቶች ውስጥ የቅርቡ እንደ ሆነ ታውቋል። የርዕሡ ጥቅስ በሉቃ. ምዕ. 11 ላይ የተጻፈው እና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያቀረቡት ጥያቄ ሲሆን፥ ይህም ቤተ ክርስቲያን የኢዮቤልዩን በዓል ለማክበር ለምታደርገው ዝግጅት ዋና ማዕቀፍ እንደሚሆን ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ስለ ጸሎት ባቀረቡት ትምህርት ላይ የተመሠረተ ነው

በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አስተምህሮ ላይ የተመሠረተው እና "ጌታ ሆይ! መጸለይን አስተምረን" በሚል ርዕሥ የታተመው አዲሱ መመሪያው በቁምስና እና በቤተሰብ ውስጥ ለጸሎት የቀረቡ ምዕራፎችን ያቀፈ ሲሆን በተጨማሪም በመንፈሳዊ የወጣት ማኅበራት፣ በጸሎት ማኅበራት፣ በትምህርተ ክርስቶስ እና በመንፈሳዊ ሱባኤዎች ወቅት የሚቀርቡ ጸሎቶችን እና በመጨረሻም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. በሚከበረው የኢዮቤልዩ በዓል ላይ የሚቀርብ ጸሎት የያዘ እንደሆነ ታውቋል።

"ጌታ ሆይ! መጸለይን አስተምረን" በሚል ርዕሥ የታተመው ይህ አዲሱ መመሪያ፥ ምዕመና ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት አማካይነት የበለጠ ሙሉ ግንኙነት እንዲኖራቸው፥ ከሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነቶችም አቅጣጫዎችንና ምክሮችን ለመለገሥ ታስቦ የተዘጋጀ እንደ ሆነ መግለጫው አመላክቷል።

"ጌታ ሆይ! መጸለይን አስተምረን" በሚል ርዕሥ የታተመውን መመሪያ የጣሊያንኛ እትም በአሁኑ ወቅት ከጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ ድረ-ገጽ ላይ በነጻ ማውረድ እንደሚቻል እና የእንግሊዝኛ፣ የስፔን፣ የፖርቱጋል፣ የፈረንሳይኛ እና የፖላንድ ቋንቋዎች እትሞችም በቅርቡ በጽሕፈት ቤቱ ድረ-ገጽ ላይ እንደሚለጠፉ ታውቋል።

የጸሎትን አስፈላጊነት እንደገና ማወቅ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ጥር 12/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡት ወቅት፥ የጸሎት ዓመትን ከኢዮቤልዩ በዓል አስቀድመው ይፋ በማድረግ፥ ምዕመናኑ ይህን የጸጋ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ በመኖር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እና ጸሎታቸውን በማጠናከር የእግዚአብሔር ተስፋ ጥንካሬን እንዲለማመዱ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የጸሎት ዓመት ዋና ዓላማንም ሲገልጹ፥ “ዓመቱ በግል ሕይወት፣ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና በዓለም ውስጥ የጸሎትን ታላቅ ዋጋ እና ፍፁም አስፈላጊነት እንደገና ለማወቅ የተሰጠ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

 

22 February 2024, 12:46