የቅድስት መንበር ልኡካን ዓለም አቀፍ የሰላም ቀንን በጸሎት ለማክበር ጄኔቭ ላይ መሰብሰቡ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ዘንድሮ በተከበረው 57ኛው የዓለም የሰላም ቀን ላይ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባስተላለፉት የዘንድሮ መልዕክት ላይ በማሰላሰል፥ የቴክኖሎጂ ግስጋሴ በሥነ ምግባራዊ ማዕቀፍ በመታገዝ ለሰላም ባህል ማበብ እና የተሻለ ዓለምን ለመገንባት አስተዋጽዖን ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል።
በየዓመቱ የሚካሄደው ይህ የጸሎት ጉባኤ ዘንድሮ አሥራ አምስተኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን፥ በጄኔቭ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ተልእኮ አዘጋጅነት የተካሄደ ሲሆን በርካታ አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎችን እና የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች መካፈላቸው ታውቋል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት እንግዶች በጄኔቭ ከሚገኙት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦች ተወካዮች፣ ከአይሁድ፣ ከቡዳ፣ ከሱፊ ሙስሊሞች፣ ከፕሮቴስታንት እምነቶች እና ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመጡ እንግዶች በዕለቱ የቀረቡትን አጫጭር አስተንትኖዎችን አድምጠዋል።
የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽሕፈት ቤት እንዳመለከተው፥ ዝግጅቱ በተካሄደበት በቅዱስ ዮሐንስ 12ኛ ቁምስና ውስጥ የፊሊፒን እና የአፍሪካ መዘምራን ዜማቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ በአረብኛ፣ በቻይንኛ፣ በፈረንሣይኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በሩሲያ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች ጸሎት ቀርቧል።
ጋዜጣዊ መግለጫው አክሎም፥ በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የልዩ ልዩ እምነቶች ተከታዮች ሰላምን የሚገልጹ የወይራ ቅርንጫፎች ለእያንዳንዱ ተወካይ እንደተሰጠው እና ይህም ለበዓሉ ማስታወሻ እንዲሆን እና ለሰላም የሚደረገውን የጋራ ጥረት የሚገልጽ እንደሆነ አስታውቋል።
ዝግጅቱ ከመጠቃለሉ አስቀድሞ የላውዛን፣ ፍሪቦርግ እና ጄኔቭ ከተሞች ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሻርል ሞሬሮድ የመጨረሻ ጸሎት ካደረሱ በኋላ ተሳታፊዎቹ በቁምስናው አዳራሽ ውስጥ የተዘጋጀላቸውን ጽበል ጸዲቅ ቀምስዋል።