የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን የዓብይ ጾም መልዕክት መሠረት ያደረገ አዲስ የሥነ ጥብበ ሥራ ይፋ ሆነ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
"ወንድማማችነት" የሚለውን ጭብጥ ለማጉላት የተዘጋጀው እና በቫቲካን አካባቢ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ምስሎች በማዘጋጀት የሚታወቀውን የእውቁ ሠዓሊ ማውፓል፥ በዋና ስሙ ማውሮ ፓሎቲ በመባል የሚታወቀው ሠዓሊ አዲስ የጥበብ ሥራ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዘንድሮው የዓብይ ጾም ካዘጋጁት መልዕክት ጋር አብሮ እስከ ብርሃነ ትንሳኤው በዓል ድረስ በተከታታይ እንደሚወጣ ታውቋል።
የካቲት 18/2016 ዓ. ም. ይፋ የሆነው የሦስተኛ ዙር ሥዕል፥ “ወደ ሰማይ የደረሰው የዛሬዎቹ በርካታ ጭቁን ወንድሞች እና እህቶች ጩኸት ወደ እኛ ዘንድም ደርሶ ይቀሰቅሰናል ወይ?" ብለን እራሳችንን እንጠይቅ ከሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥቅስ ጋር የተያያዘ መሆኑ ተመልክቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዘንድሮው የዐብይ ጾም እንዲሆን ብለው በጥር 23/2016 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉት መልዕክት መሪ ቃል፥ “እግዚአብሔር በምድረ በዳ ወደ ነፃነት ይመራናል” የሚል እና በኦሪት ዘፀአት መጽሐፍ ውስጥ በምዕ. 20.1-17 ላይ፥ “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ ጌታ አምላክህ እኔ ነኝ” በሚለው ጥቅስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ታውቋል።
ነፃነት የሚለው የሁለተኛ ዙር የሠዓሊው ማውፓል ሥራ ዋና ጭብጥ ሲሆን፥ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ የዓብይ ጾም ወቅትን በማስመልከት ባስተላለፉት የጽሕፈት ቤታቸው መልዕክት፥ በዚህ ዙር ይፋ የሆነው ምስሉ ከባርነት ነፃ ለመውጣት ያግዘናል ሲሉ አስረድተዋል። “እግዚአብሔር ተስፋችን ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ፣ በቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ እና ግላዊ የለውጥ ጉዞ ላይ እርሱ ሊሰጠን ወደሚፈልገው ምድር ይመራናል" ሲሉ አስረድተዋል።