በሮም የሚገኘው የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል የሕክምና ክፍል የቆየ ምስል በሮም የሚገኘው የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል የሕክምና ክፍል የቆየ ምስል  

በሮም የሚገኘው የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሆነበት አንድ መቶኛ ዓመት ተከበረ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የህፃናት የሕክምና ማዕከል እንደሆነ የሚነገርለት “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል ከ100 ዓመት በፊት ለቅድስት መንበር የተበረከተ እንደሆነ ይታወቃል። በሮም የሚገኝ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆስፒታል ተብሎ የሚጠራውን የዚህ ሆስፒታል ታሪክ ወደ ኋላ ተመልሰን በማጤን ቅዱስነታቸው ከሆስፒታሉ ጋር ያላቸውን የአባትነት ግንኙነት እንመለከታለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ጎሮግሮሳውያኑ በ 1869 ዓ. ም. በሮም የሚገኙ የሺፒዮኔ መሳፍንት ቤተሰብ “ባምቢኖ ጄሱ” የሕፃናት ሕክምና ሆስፒታልን መሠረቱ። በሮም ከተማ መሃል የሚገኘው የመሳፍንት ቤተሰብ መኖሪያ ቤት በውስጡ 12 አልጋዎችን በመያዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የህፃናት ሆስፒታል ሆነ።

ከዚያም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 12/1916 ዓ. ም. ሆስፒታሉ ለቅድስት መንበር የተበረከተ ሲሆን ይህም “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆስፒታል” እንዲሆን እና በሮም እና በዓለም ዙሪያ ላሉ የታመሙ ሕፃናት ተጠቃሽ የኅክምና ማዕከል ሆነ። ይህ ከሆነ እነሆ በትክክል አንድ መቶ ዓመታት አልፈዋል።

በዚህ ወቅት ሆስፒታሉ ሮም ከተማ ውስጥ ጃኒኩለም ተብሎ በሚጠራ ኮረብታማ ቦታ ላይ ወደሚገኝ ጥንታዊ የቅዱስ ኦኖፍሪዮ ገዳም ወዳለበት ቦታ ተዛወረ። ይህ ሆስፒታሉ ከተመሠረተ አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1887 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ ሥፍራ የሚገኝ ቢሆንም፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2030 ዓ. ም. እንደገና “ፎርላኒኒ” ሆስፒታል ወደሚገኝበት ሥፍራ ይዛወራል ተብሎ ይጠበቃል።

የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታሉ ታሪክ

ሮም ከተማ ውስጥ የሚገኘው የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል ለቅድስት መንበር ከመለገሱ በፊት 33,000 ሕጻናት የሕክምና ዕርዳታ አግኝተው ነበር። ሆስፒታሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1915 ዓ. ም. በአቬዛኖ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዱ 420 ህጻናትን እና በታላቁ ጦርነት ወቅት ማለትም እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ1918 ዓ. ም. በገባው የጉንፋን ወረርሽኝ የተያዙ 300 ሕጻናትን ጨምሮ በቁጥር በርካታ ለሆኑ የድንገተኛ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሕጻናት አገልግሎት አበርክቷል።

የሆስፒታሉ የላቀ ችሎታ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1858 ዓ. ም. በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታልን የጎበኙት የመጀመርያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ሲሆኑ፥ ቀጥሎም በ1968 (እ.አ.አ.) ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ በ1979 (እ.አ.አ.) ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በ2005 (እ.አ.አ.) ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እና በ2017 (እ.አ.አ.) ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጎበኙት ሲሆን፥ ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት ትልቁ የሕፃናት ሕክምና ማዕከል እና የምርምር ተቋም ከመሆኑ በላይ በአውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ ዋና ዋና ዓለም አቀፍ የምርምር ማዕከላት ጋር በቆራኘት የሚሠራ እንደሆነ ታውቋል።

ሆስፒታሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ብቻ ከ 95,000 በላይ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትን፣ ከ 29,000 አልጋ ይዘው የሚታከሙትን፣ ከ 32,000 በላይ የቀዶ ጥገና ዕርዳታን እና ከ 2,500,000 በላይ ተመላላሽ ታካሚ ሕጻናት መዝግቦ አገልግሎት መስጠቱ ታውቋል። በሆስፒታሉ ከሚታከሙ ሕጻናት መካከል 30% በላይ የሚሆኑት ከክልሉ ውጭ የመጡትን የሚያካትት ሲሆን 14% የሚሆኑት የውጭ አገር ዜጎች እንደሆኑ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 ሕክምና እና እንክብካቤ የተደረገላቸው 8,000 ሕጻናት በብዛት የማያጋጥም በሽታ ያለባቸው እንደነበሩ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎርሳውያኑ በ 2017 በሮም ከተማ በሚገኝ የ “ባምቢኖ ጄሱ” ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ የሕክምና ባለሞያዎችን እና ሕጻናትን አግኝተው ባነጋገሯቸው ወቅት እንደገለጹት፥ "ሆስፒታሉ ከሆስፒታልነት በላይ የቤተሰብ መንፈስ የሚታይበት እንደሆነ ተረድቻለሁ" ብለው፥ በዚህ ጉብኝታቸው እርሳቸውም የዚህ ቤተሰብ አካል መሆናቸውን አስመስክረዋል። ቅዱስነታቸው በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉትን ህፃናትን ከጎበኟቸው ሕጻናቱም በተራቸው ለቅዱስነታቸው መልዕክት እና ስዕሎቻቸውን ልከውላቸዋል።

“ባምቢኖ ጄሱ” የሕፃናት ሕክምና ሆስፒታል “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሆስፒታል” የተባለበት ምክንያት የቅድስት መንበር በመሆኑ ሳይሆን ነገር ግን ቅዱስነታቸው በግልጽ እና በእውነት ለሆስፒታሉ ባላቸው ፍቅርና እንክብካቤ መሆኑን ሕጻናቱም ጭምር በሚገባ ያውቁታል።

21 February 2024, 16:30