የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ "መደራደር ሽንፈት ሳይሆን የፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ቅድመ ሁኔታ ነው።"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዩክሬን የሚካሄደውን ጦርነት በማስመልከት ከስዊዘርላን ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ተከትሎ፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን “ኮሪዬሬ ዴላ ሰራ” ከተሰኘ የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። በቃለ ምልልሳቸው የኒውክሌር ጦርነት መስፋፋት አደጋ እንዳለ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ዓመት የካቲት 18/2015 ዓ. ም. የተናገሩትን በመጥቀስ፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከስዊዘርላን ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ የቅዱስነታቸው ጥሪ “ፍትሃዊና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለማምጣት ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

እንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎችን ለመፈጠር ሃላፊነቱ በአንደኛው ወገን ላይ ብቻ ሳይሆን በሁለቱም ጫንቃ ላይ እንደሚወድቅ ግልጽ እንደሆነ ተናግረው፥ የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ጥቃቱ በትክክል እንዲቆም ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

አውዱ መዘንጋት የለበትም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በጉዳዩ ላይ ዋና አውዱ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀረበላቸው ጥያቄ እንደሆነ ተናግረው፥ ቅዱስነታቸው ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፥ “መደራደር እና ለመደራደርም ድፍረት ሊኖር እንደሚያስፈልግ፥ ለድርድር ፈቃደኛ መሆን እጅ መስጠት ወይም መሸነፍ አይደለም” ሲሉ መናገራቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል።

ቅድስት መንበር ይህንን መስመር እንደምትከተል እና የተኩስ አቁም ጥሪዋን ማቅረብ መቀጠሏን የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ቀድሞ ተኩስ ማቆም ያለበት አጥቂው ወገን መሆን እንዳለበት እና ከዚያም ድርድር መጀመር እንደሚገባ ገልጸው፥ መደራደር ድክመት ሳይሆን ጥንካሬ እና ድፍረት እንጂ እጅ መስጠት አለ መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማስረዳታቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አውሮፓ ውስጥ በጦርነቱ ለተሰውት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩት ሰዎች ሕይወት ትልቅ ግምት ሊኖረን እንደሚገባ መናገራቸውን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰው፥ ይህ ምክራቸው በዩክሬን እንዲሁም በቅድስት አገር እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች በሚፈጠሩ ግጭቶች ላይ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ማግኘት አሁንም ይቻላል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ውሳኔዎቹ በሰዎች ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ሁልጊዜ ዕድሉ አለ ሲሉ ተናግረዋል።

በዩክሬን ላይ የተከፈተው ጦርነት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የተፈጥሮ አደጋ ሳይሆን የሰው ልጅ የነፃነት ውጤት ብቻ እንደሆነ ገልጸው፥ ለደረሰው አደጋ ዋና ምክንያት የሆነው የሰው ልጅ ነፃ ፈቃድ፥ የሰው ልጅ የተፈጠረውን ችግር ለማስወገድ እርምጃዎችን የመውሰድ እና ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ መንገዱን የመክፈት ዕድል እና ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

“በሩስያ እና በዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት እየሰፋ የመሄዱ አደጋ ቅድስት መንበርን ያሳስባታል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የግጭቱ መባባስ፣ አዲስ የትጥቅ ግጭቶች መቀስቀስ እና የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም በዚህ ረገድ አሳሳቢ ምልክቶች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

የጦርነቱ መስፋፋት አዲስ መከራ፣ አዲስ ሐዘን፣ በሰው እና በንብረት ላይ አዲስ ጉዳት እና አዲስ ውድመት ማለት እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም የዩክሬን ሕዝብ በተለይም ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ሲቪሎች በገዛ እጃቸው የሚያጋጥማቸውን ችግር በመጨመር ከፍተኛ የኢ-ፍትሃዊ ጦርነት ዋጋ በመክፈል ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ተናገሩት፥ የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭትም ቢሆን የሁለቱን ወገኖች ኃላፊነት እንደሚጠይቅ፥ እነዚህ ሁለቱ ግጭቶች በጋራ ከየትኛውም ወገን ተቀባይነት የሌላቸው እና በአደገኛ ሁኔታ እየሰፉ መሄዳቸው እና መፍትሄን ማግኘት አለመቻሉ በተለያዩ አገሮች መዘዞችን የሚያስከትል በመሆኑ ያለ ጠንካራ ድርድር ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊገኝ እንደማይችል፣ እየፈጠሩ ያሉት ጥላቻዎች እንደሚያሳስባቸው እና የሚፈጠሩት ጥልቅ ቁስሎች የሚድኑበት ጊዜ እጅግ ረጅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

“ወደ ኒውክሌር ጦርነት የመሄዱ አደጋ ግልጽ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ አንዳንድ የመንግሥት ተወካዮች ወደዚህ ዓይነት ስጋት ውስጥ በመደበኛነት እንደሚገቡ ተናግረው፥ ይህም በእርግጥ ሊከሰት የሚቻል እና ማስጠንቀቂያ ሳይሆን ስልታዊ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ አስረድተዋል።

“ቅድስት መንበር ያደረባትን ፍርሃት በተመለከተ፥ በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ተዋናዮች ፍትሐዊ እና የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን የሚቻላቸውን ባለማድረጋቸው ይበልጥ ወደ ጥቅማቸው ሊገቡ እንደሚችሉ አምናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

 

12 March 2024, 15:54