“ፅንስ ማስወረድ በሕይወት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ነው" “ፅንስ ማስወረድ በሕይወት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ነው"  (©STEKLO_KRD - stock.adobe.com)

ማንም የሰውን ሕይወት የማጥፋት መብት ሊኖረው እንደማይችል ተገለጸ

በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ፥ በፈረንሳይ ፅንስ የማቋረጥ መብትን በሕገ-መንግሥቱ ለማካተት የሚደረገውን ጥረት የተቃወሙ የፈረንሳይ ብጹዓን ጳጳሳትን በመደገፍ መግለጫ አውጥቷል። ጳጳሳዊ የሥነ-ሕይወት አካዳሚው፥ ፈረንሳይ ፅንስን ማስወረድ ሕገ መንግሥታዊ መብት በማድረግ በቀዳሚነት ያስቀመጠችውን የማሻሻያ ሃሳብ በጽኑ ለተቃመችው የፈረንሳይ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ድጋፉን ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መንግሥት የቀረበው ረቂቅ ሕግ በብሔራዊ ምክር ቤት እና በሴኔት የፀደቀ ሲሆን፥ ሰኞ የካቲት 25/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተካሄደው በፓርላማው የጋራ ስብሰባ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ በሦስት አምስተኛ ድምጽ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በጠቅላላ የሰብዓዊ መብቶች ዘመን የሰውን ሕይወት የማጥፋት መብት ሊኖር አይችልም

በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ፥ ሰኞ የካቲት 25/2016 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፥ የፈረንሳይ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ “ፅንስ ማስወረድ በሕይወት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በመሆኑ ከሴቶች መብት አንፃር ተለይቶ ሊታይ አይችልም” የሚለውን ጽኑ አቋም በመደገፍ ከብጹዓን ጳጳሳቱ ጎን በመቆም፥ “ሃሳቡ ልጆቻቸውን በሕይወት ማቆየት ለሚፈልጉ ቤተሰቦች የድጋፍ እርምጃዎችን አይጠቅስም” በማለት ሐዘኑን ገልጿል።

የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው አክሎም፥ “በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ዘመን ማንም የሰውን ሕይወት የማጥፋት መብት ሊኖር አይችልም” በማለት አጥብቆ ተናግሯል። "ሁሉም መንግሥታት እና ሃይማኖታዊ ወጎች በዚህ የታሪክ ደረጃ ላይ ለሰላም እና ለማኅበራዊ ፍትህ የሚጠቅሙ ተጨባጭ እና ሁለንተናዊ ተደራሽነት ያላቸውን የሃብት፣ የትምህርት እና የጤና አጠባበቅ ውጤታማ እርምጃዎችን በመውሰድ ሕይወትን ከጉዳት መጠበቅ ፍጹም ቅድሚያ የሚሰጠው እንዲሆን የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው” ብሏል ጳጳሳዊ አካዳሚው።

ለጉዳት የተጋለጡትን መከላከል

"የዘመናችን ልዩ የሕይወት አስቸጋሪ እና አስገራሚ ሁኔታዎች፥ በመጀመሪያ ደረጃ አቅመ ደካማ እና ተጋላጭ የሆኑትን ከአደጋ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ጠንካራ ሕጋዊ መሣሪያዎች መቅረብ አለባቸው” ሲል የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው ተናግሯል።

“ሕይወትን ከአደጋ መጠበቅ የሰው ልጅ የመጀመሪያ ዓላማ መሆን አለበት” ያለው ጳጳሳዊ አካዳሚው፣ ግጭት በበዛበት በዚህ ዓለም ውስጥ ሕይወትን ከአደጋ መጠበቅ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በኢንዱስትሪ መስኮች በሙሉ የሰውን ልጅ እና ወንድማማችነትን የሚያገለግል እንደሆነ አስታውቋል።

ሕይወትን ከጥቃት መከላከያ ርዕዮተ ዓለም አይደለም

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት የጠቀስው የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው፥ ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን “ሕይወትን መከላከል ተጨባጭነት የሌለው ርዕዮተ ዓለም ሳይሆን ነገር ግን ሰብዓዊ እውነታ እንደሆነ በማስገንዘብ፥ ሁሉንም ክርስቲያኖች የሚያሳትፍበት ምክንያት፥ በእርግጥ ክርስቲያን እና ሰው በመሆናቸው ነው” ብሏል።

"የሕይወት ባሕል የክርስቲያኖች ቅርስ ብቻ እንዳልሆነ ጠንቅቆ በማወቅ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳት እና አንዱ ሌላውን በእንግድነት የመቀባበል አመለካከትን ለትውልድ ለማስተላለፍ፥ በባሕላዊ እና አስተማሪ ደረጃ መሥራት እንደሆነ የገለጸው ጳጳሳዊ አካዳሚው፥ “የወንድማማችነት ግንኙነቶች ለመገንባት የእያንዳንዱን ሰው እሴት ሌላው ቀርቶ የአቅመ ደካሞችን እና የስቃይተኞችንም ጭምር መገንዘብ ይገባል” ሲል መግለጫው ገልጿል።

05 March 2024, 16:37