ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ  

በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ተባለ

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል የበለጠ ውጤታማ ዓለም አቀፍ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመንግሥታቱ ድርጅት 78ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ በድጋሚ አሳስበዋል።

የቅድስት መንበር እንደራሴው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በማከልም፥ በዓለም አቀፍ ሕግ ውስጥ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንደ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች መቆጠራቸውን አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ “የዓለም አቀፍ ሕግ ኮሚሽን (አይኤልሲ) እነዚህን ወንጀሎች መከላከል በእርግጥ የማይለወጥ እና የማይጣስ ደንብ ነው” በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል።

ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቅጣት የሚደረግ ዓለም አቀፍ ትብብር

እነዚህን አስከፊ ድርጊቶች ለመከላከል እና ለመቅጣት የሚያግዝ ዓለም አቀፍ ትብብር ሊበረታታ እንደሚገባ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ ከዚህ በፊት የነበረውን ሕግ የሚያስተካክል ዓለም አቀፋዊ፣ ባለ ብዙ ወገን እና ሁሉን የሚያስተዳድር ሕጋዊ መንገድ መኖር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በንግግራቸው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በማስታወስ የሌሎች ክብር በማንኛውም ሁኔታ መከበር እንዳለበት አሳስበው፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመፍታት የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ መሠረት ለሆነው የሰብዓዊ ክብር ወሳኝ ሚና አጽንዖት ሰጥተዋል።

ውጤታማነትን ማጠናከር

ሕገ ረቂቁን በማስመልከት የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ ውጤታማነቱንም ለማጠናከር የማሻሻያ ሐሳቦችን አቅርበዋል። “የአዲሱ ሕገ ረቂቅ ድርብ ዓላማ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቅጣት ቢሆንም የቀድሞውን ዓላማ ግልፅ ማጣቀሻ ያልያዘ በመሆኑ፥ በአንቀጽ ዘጠኝ ላይ የሰብዓዊ ክብር ማጣቀሻን ማካተት እንደሚገባ ጠቁመው፥ እነዚህ የማሟያ ሃሳቦች ለአንቀጾች ይበልጥ ጠንካራ የሆኑ የትርጓሜ ማዕቀፎችን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የወንጀል መከላከል አስፈላጊነትን በግልፅ መቀበል እንደሚገባ አሳስበው፥ “በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል የማይለወጥ የማይጣስ ሕግ ስለሆነ የነዚህ ድርጊቶች ፍቺም ከልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የተያያዘ መሆን እንዳለበት ተናግረው፥ እነዚህን በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ሲገልፅ አሁን ካለው ልማዳዊ ደንቦች መራቅ የለበትም ሲሉ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ አሳስበዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ የሉዓላዊ ፍላጎቶች በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በፍፁም ሊያረጋግጡ የማይችሉ መሆናቸውን አሳስበዋል።

 

03 April 2024, 14:20