ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተገኙበት የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተገኙበት የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ   (Vatican Media)

የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ በቫቲካን መጀመሩ ተነገረ

የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተገኙበት ሰኞ ሚያዝያ 7/2016 ዓ. ም. በቫቲካን መጀመሩን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ምክር ቤቱ የመጨረሻ ስብሰባውን የካሄደው ዘንድሮ ከታኅሳስ 26-28/2016 ዓ. ም. ሲሆን፥ ይህን ስብሰባ  ሦስት ሴቶች ተካፍለውታል። ምክር ቤቱ በወቅቱ “ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸው ሚና” በሚለው ርዕሥ ላይ መወያየቱ ሲታወስ፥ በርዕሡ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ያበረከቱት እህት ሊንዳ ፖቸር፥ የሳሌዥያን ደናግል ማኅበር አባል እና በሮም በሚገኘው ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ትምህርት ጥናት ዘርፍ የ “ክርስቶሎጂ” እና “ማሪዮሎጂ” መምህር፣ እህት ጁሊቫ ዲ ቤራዲኖ፣ በጣሊያን ቬሮና ሀገረ ስብከት ውስጥ የመንፈሳዊነት ትምህርት ልምምዶች መምህርት እና የዘርፉ ሃላፊ፣ እህት ጆ ቤይሊ ዌልስ፥ በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የአንግሊካን ኅብረት ጳጳስ እና ምክትል ዋና ጸሐፊ እንደ ነበሩ ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ የተገኙበት የታኅሳስ ወሩ የካርዲናሎች ስብሰባ ሌላው ርዕሥ፥ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው ሲኖዶሳዊ ሂደት እና በስብከተ ወንጌል መሪ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ ለዚህ ርዕሥ አስተዋጽዖአቸውን የበረከቱት፥ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግል እና በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ፣ ሊቀ ጳጳስ ሪኖ ፊዚኬላ እንደ ነበሩ ይታወሳል።

አዲሱ የካርዲናሎች ምክር ቤት “C9” አባላት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካርዲናሎች ምክር ቤትን የካቲት 28/2015 ዓ. ም. በአዲስ መልክ ማቋቋማቸው የሚታወስ ሲሆን፥ አባላቱም የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ የቫቲካን ከተማ ጳጳሳዊ ኮሚሽን ፕሬዝደንት እና የቫቲካን ከተማ አስተዳደር ርዕሠ መስተዳድር ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ቬርጌዝ አልዛጋ፣ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የኪንሻሳ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በሕንድ የቦምቤይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ኦስዋልድ ግራሲያስ፣ በሰሜን አሜሪካ የቦስተን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሴያን ፓትሪክ ኦማሌይ፣ በስፔን የባርሴሎና ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሁዋን ሆሴ ኦሜላ ኦሜላ፣ በካናዳ የኪቤክ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጄራልድ ላክሮክስ፣ በአውሮፓ የሉክሰምበርግ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክላውድ ሆሌሪች፣ በብራዚል የሳን ሳልቫዶር ደ ባሂያ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮካ እንደሆኑ እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ በጣሊያን የክሬሲማ ጳጳስ ሞንሲኞር ማርኮ ሜሊኖ እንደሆኑ ይታወቃል። ይህ አዲሱ ምክር ቤት “C9” የመጀመሪያ ስብሰባውን ሰኞ ሚያዝያ 16/2015 ዓ. ም. ማካሄዱ ይታወሳል።

የአዲሱ የካርዲናሎች ምክር ቤት ምሥረታ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዳሜ መስከረም 18/2006 ዓ. ም. በዓለማቀፉ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ እንዲያግዟቸው እና በሮም ቤተ ክርስቲያን የሚገኙትን የከፍተኛ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶችን ለማሻሻል የሚያስችሉ ጥናቶችን በማካሄድ ምክር ቤቱን ማቋቋማቸው ሲታወስ፥ በኋላም “ወንጌልን ስበኩ” በሚል ርዕሥ በመጋቢት 10/2014 ዓ. ም. የታተመውን አዲሱን ሐዋርያዊ ደንብ መመሪያው በማድረግ የመጀመሪያውን የካርዲናሎች ምክር ቤት “C9” ስብሰባን መስከረም 21/2006 ዓ. ም. ማካሄዱ ይታወሳል።

 

 

 

 

16 April 2024, 17:25