ከአከባቢያቸው የተፈናቀሉ ሴቶች ኢትዮጵያ፣ አፋር ክልል ውስጥ በምትገኘው፣ የኢሬብቲ ጊዜያዊ መጠልያ ካምፕ ውስጥ ጀሪካን ይዘው ከአከባቢያቸው የተፈናቀሉ ሴቶች ኢትዮጵያ፣ አፋር ክልል ውስጥ በምትገኘው፣ የኢሬብቲ ጊዜያዊ መጠልያ ካምፕ ውስጥ ጀሪካን ይዘው  (AFP or licensors)

ቅድስት መንበር ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ በጋራ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበች

ቅድስት መንበር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመመከት በመተባበር አስቸኳይ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ገልፃ፥ ከ4.4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ከአስከፊ ድርቅ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጦት እና የኢኮኖሚ ችግሮች ጋር ተዳምረው ያለውን ሁኔታ አስከፊ አድርጎታል በማለት አሳስባለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጄኔቫ በተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ተወካይ የሆኑት ብጹእ አቡነ ኤቶር ባሌስትሬሮ ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት ገልጸው ከ4.4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስለሚሆኑ ስደተኞች በማንሳት ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ አመላክተዋል።

ሚያዚያ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ስለሚገኘው የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ ላይ ለመምከር በጄኔቫ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ብጸእ አቡነ ባሌስትሬሮ ቅድስት መንበርን ወክለው እንደተናገሩት ስብሰባው አስቸጋሪ በሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ለምትገኝ አገር ያለውን አጋርነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሊቀ ጳጳሱ የተልእኮውን አጣዳፊነት እና ስፋት አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ “የችግሩ ሁኔታ ሁላችንም በመተባበር እና በመደጋገፍ እንድንንቀሳቀስ ያስገድደናል” ብለዋል።

በሃገሪቷ ውስጥ ያሉ ችግሮች

ኢትዮጵያ ተከታታይ የሆኑ ግጭቶችን፣ የበሽታዎች መቀስቀስ እና ለአምስት ዓመታት በበልግ ወቅት ያልዘነበው ዝናብ ያስከተለውን ድርቅ እያስተናገደች ያለች ሃገር ስትሆን፥ በዚህም የተነሳ ባለፉት አሥርት ዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ አከባቢዎች እጅግ የከፋ የድርቅ ሁኔታ መከሰቱን አስረድተዋል። በማስከተልም “እነዚህ አስከፊ ክስተቶች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፣ በተለይም አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናትን እና በርካታ ሴቶችን ለችግር አጋልጧል” ብለዋል።

የአገሪቱን ሁኔታ ከሚያባብሱት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግሮች ውስጥ የዋጋ ንረት እና የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ተጠቃሽ እንደሆኑም ተገልጿል። ከእነዚህ ችግሮች አንጻር ይላሉ ሊቀ ጳጳሱ “የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ አጋሮች በሚያስደንቅ ቁርጠኝነት እና ትጋት ለችግሮቹ ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ” ካሉ በኋላ፥ ሆኖም ግን አሁንም ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳለ ገልፀዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ድጋፍ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሰብአዊ ቀውሱን አስከፊነት በመረዳት ከተጎጂው ሕዝብ ጋር በመሆን በአብሮነት የማገዝን አስፈላጊነት በማጉላት ሲገልጹ እንደነበር ይታወቃል። ብፁዕ አቡነ ባሌስትሬሮ ከዚህ ጋር አያይዘው የተሰማቸውን ጥልቅ አሳቢነት በመግለጽ “የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ አፋጣኝ ዕርምጃ እና ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደረግ ያቀረቡትን ጥሪ ቅድስት መንበር ትደግፋለች" ካሉ በኋላ፥ "ይህ የከፍተኛ ደረጃ የቃል ኪዳን ዝግጅት መደረጉን በእጅጉ ታደንቃለች” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የምትገኘው ቤተክርስቲያን

በኢትዮጵያ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምንም እንኳን አናሳ ብትሆንም በምግብ እጦት ለተጎዱ እና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ሰለባ ለሆኑ ህዝቦች እርዳታ በማቅረብ እና በማከፋፈል ረገድ ትልቅ ሚና ትጫወታለች።

ብጹእ አቡነ ባሌስትሬሮ ይሄን አስመልክተው እንደተናገሩት በ2015 ዓ.ም. በአከባቢው የሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት እንቅስቃሴ በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ አሥራ ሁለት ክልሎች በዘጠኙ ውስጥ ለሚኖሩ ዘር፣ ሃይማኖት እና ብሄር ሳይለይ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቶቹ በዋናነት በሰብአዊ ዕርዳታ እና በምግብ ዋስትና ላይ ያተኮሩ ነበሩ። “እነዚህ አሃዞች በሌሎች ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ኤጀንሲዎች የሚሰጠውን ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አያካትቱም” ሲሉ ሥራው የተሰራው በሃገር ውስጥ በምትገኘዋ ቤተክርስቲያን ብቻ መሆኑን አመላክተዋል።

ብጹእ አቡነ ኤቶር ባሌስትሬሮ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ “ዛሬ ቅድስት መንበር ቃል ኪዳኗን እያደሰች ነው” ካሉ በኋላ “ይህንን ማድረግ ግዴታችን ነው፥ ጥልቅ ከሆነ የጋራ ሰብአዊነት ስሜት የመነጨ፣ ሃይማኖታዊ እና ሞራላዊ ግዴታ ነው” ብለዋል።
“ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ ፍላጎቶች በጋራ በምናደርገው ምላሽ ደህንነትን፣ መረጋጋትን እና ሰላምን ለማምጣት የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት እናደርግ ዘንድ የማያወላውል ድጋፍ እናድርግ” ሲሉም መለዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
 

18 April 2024, 16:17