ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በጨለማ በተሸፈነ ዓለም ውስጥ፣ የሰላም ፈጣሪዎች እንሁን አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የቫቲካን የመንግስታት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ዋና ፀሐፊ ብጹእ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በክሮኤሺያ ባደረጉት የሶስት ቀናት ጉብኝት ወቅት ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የዛግሬብ ጠባቂ የሆነችው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደረገውን ሥርዓተ ቅዳሴ መርተዋል።
ብጹእነታቸው በሥርዓተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ቃለ ምእዳን የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ፍጻሜ ሳያዩ አምነው ተስፋ እንዳደረጉት ቅድስት ድንግል ማርያም እና የአክስቷ ልጅ ኤልሳቤጥ ሁሉ፥ ምዕመናንም ምንም እንኳ ዛሬም በብዙ ችግሮች እና “ጥፋቶች” ውስጥ ቢኖሩም የእግዚአብሔርን ሥራ እንዲገነዘቡ ጋብዘዋል።
የተስፋ ምንጭ የሆነችው እመቤታችን
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በአከባቢው አጠራር ‘መግቢያ አለት’ የምትሰኘው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ምስሏ በሃገሪቷ በተነሳው የእሳት አደጋ በርካታ ህንፃዎች መውደማቸውን ተከትሎ ወደ ጥንታዊቷ የዛግሬብ ከተማ በሚያስገባው በምስራቃዊ መግቢያ ላይ ካለው የበሩ ፍርስራሽ ውስጥ ምንም አደጋ ሳይደርስበት መገኘቱን አስታውሰዋል።
“ለተጨነቁና ግራ ለተጋቡት” ነዋሪዎቿ ይህ የመደነቅ እና የተስፋ ምንጭ ነበር። ሊቀ ጳጳሱ እንዳሉት “ምንም እንኳን አንዳንዶቹ በተፈጥሮ ክስተቶች የተከሰቱ ቢሆኑም በአብዛኛው በሰው ልጅ ግድየለሽነት ምክንያት የሚደርሱ የአሰቃቂ ውድመት ትእይንት ባልጠፋባት በዛሬዋ ዓለማችን ውስጥ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለበርካታ ጊዜያት ሲገልጹት እንደነበረው ‘በከፊል ሲደረጉ የነበሩ የሶስተኛው የዓለም ጦርነት’ ወደ ‘ዓለም አቀፋዊ ግጭት’ ተቀይሯል” ያሉት ብጹእነታቸው፥ በመሆኑም ካለፈው ተምረን እራሳችንን እንደገና መመልከት አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል።
የእግዚአብሔር የህይወት ስጦታ
በማርያም እና በኤልሳቤጥ መካከል ስላለው ግንኙነት የሚናገረውን የመጽሃፍ ቅዱስ የዕለቱ ምንባብ ላይ አስተንትኖ የሰጡት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር፥ ሁለቱም እናቶች ባልተጠበቀ እና ባልተለመደ መልኩ የእናትነትን ክብር ያገኙ እንደሆኑ እና የደረሰባቸው መከራ የእናትነት እቅዳቸውን እንዴት እንዳስተጓጎለ ነገር ግን በደስታ እንደተቀበሉት ጠቁመዋል።
ይህንንም ሃሳብ ወደ ዛሬዎቹ እናቶች በማዞር ሲገልጹ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አዲስ የሕይወት ዘር በማኅፀናቸው የሚቀበሉ ሴቶችን ሁሉ፥ በድንገት የተከሰተ ቢሆንም፥ እሷ ታጅባቸው ዘንድ እንለምናለን” ካሉ በኋላ፥ የተሰጣቸው ሥጦታ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ እንዲያውቁ እንለምናለን” ብለዋል። ብጹእነታቸው በማከልም ይህ በህብረተሰባችን ውስጥ ሁሌም የሚከሰት አይደለም፥ ነገር ግን ለአማኞች ሁል ጊዜ ህይወትን ማበረታታት እና መከላከል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ወደፊት መጓዝ
ወንጌል ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም ሲናገር “ተነሥታ ፈጥና ሄደች” በማለት የአክስቷን ልጅ የሆነችውን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ እንደሄደች ይገልፃል። ለዚህም ነው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ማርያምን አሁን ላለችው ቤተ ክርስቲያን እንደ ተምሳሌት ያቀረቡት፥ ካሉ በኋላ “እንዲሁም ለእኛም ጭምር አርአያ እንድትሆነን እንጸልያለን” በማለት ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በድጋሚ ገልጸዋል።
“በክፉ ዕድል ወይም በሰው ክፋት የሚሰቃዩትን ሰዎች ለመርዳት እንድንነሣ፣ እንድንወጣ እና እንድናገናኛቸው ጌታ ኃይልን ይስጠን፥ ። በፍጥነት እንነሣ፣ ብቻችንን ተለይተን መቆየት አንችልም፥ የተጎዱትን ማጽናናት፣ ተስፋ የቆረጡትን ማበረታታት፣ እንዲሁም ሰላም ፈጣሪዎች መሆን ያስፈልጋል” ብለዋል።
የፋሲካው ተስፋ
ኤልሳቤጥ እና ባለቤቷ ዘካርያስ አምላክ ልጅ እንዲሰጣቸው ለዓመታት ሲጠባበቁ ነበር፥ “ምናልባት ተስፋ ቆርጠው ነበር” ፥ ነገር ግን ጌታ ጸሎታቸውን በሰማ ጊዜ ተስፋቸውን ፈፀመላቸው።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይፈፀም ዘንድ “ይሁን” ብላ በመታዘዟ እና ኤልሳቤጥ ማሪያምን ባየቻት ጊዜ በደስታ መሞላት የትንሳኤን አመክንዮ ያመለክታል ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፣ “የፈጣሪ ፈቃድ ይፈፀም ዘንድ የራሳችንን እቅዶች እንዴት መተው እንዳለብን ካወቅን፥ ደስተኛም ሆንክ ሃዘንተኛ፣ በውስጣችን የሚሠራውና በሙሉ ኃይሉ የሚገለጠው የፋሲካ ምሥጢር ነው” ሲሉ ሊቀ ጳጳሱ አጽንኦት ሰጥተው ቃለ ምእዳ አሰምተዋል።
አንድነት
ማርያም እና ኤልሳቤጥ ጌታን የሚያመሰግኑት ሁሉም ነገር እንደፍላጎታቸው ሲሆን ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር የገባውን ቃል እንደሚፈጽም በማመንም ጭምር ነው። ይህ ለእኛ ትልቅ መልዕክት አለው፥ “በጽንስ ውስጥ ሆኖም እንኳን፣ የእግዚአብሔርን ሥራ በዓለም ላይ እንድናይ ነው” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር አማኞች በእያንዳንዱ አሳዛኝ ሁኔታ ወይም “የሰው ልጅ ጭካኔ” በተጋረጠ ጊዜ በአንድነት ወይም በህብረት ለመቆም ዓይኖቻቸው እንዲከፍቱ መክረዋል።
ብጹእነታቸው በመቀጠልም “የሚወድቁትን ቦምቦች እና የሚያደርሱትን ውድመት ብቻ አንመልከት” ብለዋል። “ጌታ የአለት በር የሆነችውን እመቤታችንን እንደጠበቀው ሁሉ፥ ሁል ጊዜ መልካም የሆነውን፣ ይሄንን አንዳንድ ጊዜ ትልቅ የሚሆነውን አነስተኛ የምዕመናን መንጋ ያድናል። ይህም የተጎጂዎችን ህመም ለማስታገስ ወይም አዲስ አደጋ እንዳይደርስ ለመከላከል ሕይወቱን አደጋ ላይ እንደሚጥል ሰራዊት ነው” በማለት አስተንትነዋል።
የሰላም ፈጣሪዎች
“ክፋት በተሞላባት ዓለማች ውስጥ” የእግዚአብሔርን ሥራ አስቀድሞ ለማየት፣ በዛሬው የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ውስጥ ዋና ተዋናዮች የሆኑትን የሁለቱን ሰዎች እይታ እንዲኖረን ያስፈልገናል” ያሉት ሊቀ ጳጳሱ፥ “ቅዱስ ዮሓንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከ30 ዓመታት በፊት ሃገሪቷን በጎበኙበት ወቅት እንዳስታውሱት በክሮኤሺያ “የተሻለች ዓለም መነሻ” ተብላ የተጠራችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ለሁሉም ሰው የታጋሽነት ሥጦታ እንድትሰጥ እጸልያለሁ” ብለዋል።
ብጹእ አቡነ ጋላገር በመጨረሻም “በአደጋ ጊዜ የተስፋ ምልክት እንደሆነች ራሷን እንደገለጠች ሁሉ፥እኛንም የትንሣኤው ምስክሮች ታደርገን ዘንድ እጸልያለሁ፣ በሕይወታችን እግዚአብሔርን ለማመስገን እና ምንም ነገር እንኳን ቢሆን፣ በጨለማ በተሸፈነ ዓለም ውስጥ የብርሃን መብራቶች እና የሰላም ፈጣሪዎች እንድንሆን ትርዳን” በማለት አጠቃለዋል።