ኮንቴይነር የጫነ መርከብ ቀይ ባህርን ለመሻገር  የስዊዝ ካናል ከመግባቱ በፊት የስዊዝ ባሕረ ሰላጤን  ያቋርጣል ኮንቴይነር የጫነ መርከብ ቀይ ባህርን ለመሻገር የስዊዝ ካናል ከመግባቱ በፊት የስዊዝ ባሕረ ሰላጤን ያቋርጣል 

ብጹእ ካርዲናል ቼርኒ የባህር ተጓዦች ‘ኢፍትሃዊነት፣ ብዝበዛ እና መድልዎን’ እየተጋፈጡ ይገኛሉ አሉ

ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ ‘ሲ ሰንዴይ’ ተብሎ ለሚከበረው ቀን ባስተላለፉት የጽሁፍ መልእክት፥ መርከበኞች የባሕሮችን “ወሰን የለሽ ውበት” እንዲሁም የራሳቸውን “አካላዊ፣ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ጉለት” እንደሚያገኙበት ጽፈዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሲ ሰንዴይ ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያናት ውስጥ በአንድነት ተሰብስበው ለመርከበኞች፣ ለባህር ላይ ተጓዦች እና አሳ አጥማጆች የሚጸልዩበት እና በህይወት ዘመናቸው የሰው ልጆችን ለማገልገል ለሚጫወቱት ወሳኝ ሚና የሚያመሰግኑበት ቀን ነው። ሲ ሰንዴይ በተለምዶ ሃምሌ በገባ በሁለትኛው እሁድ ላይ የሚከበር ሲሆን፥ ነገር ግን ሁሉም ሰው በሚስማማው በማንኛውም የዓመቱ ቀን መርከበኞችን እና አሳ አጥማጆችን ለማክበር መምረጥ ይችላሉ።

የዘንድሮው ክብረ በዓል ከመከበሩ አስቀድመው የቫቲካን የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ቸርኒ የተረሱትን የባህር ላይ ሠራተኞች በማስመልከት መልእክት አስተላልፈዋል።

ኢፍትሃዊነት፣ ብዝበዛ እና መድልዎ

ብጹእ ካርዲናል ቼርኒ በመርከብ ኢንደስትሪ ውስጥ የተሳተፉትን ሁሉ - ከመርከብ ሰራተኞች እስከ ወደብ ሰራተኞች፣ የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች እስከ ጉምሩክ ወኪሎች በአጠቃላይ በብዙ ሚሊዮኖች እንደሚቆጠሩ በመግለጽ ነበር ጽሁፋቸውን የጀመሩት።

ብዙ የዕለት ተዕለት ፍላጎቶቻችን ባለንበት ቦታ የሚደርሱን በእነዚህ ሰራተኞች “ስውር ጥረት” ነው ሲሉ ብጹእ ካርዲናል ቼርኒ ጽፈዋል።

ነገር ግን፣ “ዛሬም ሆነ ድሮ፣ የባህር ላይ ጉዞ ከቤት እና ከመሬት፣ ለወራት አልፎ ተርፎም ለዓመታት መቅረትን ሊያስከትል ይችላል። ሁለቱም የባህር ተጓዦች እና ቤተሰቦቻቸው እርስ በእርስ ሊኖራቸው እና ሊያሳልፏቸው የሚገቡ ውድ ጊዜያትን በሥራው ምክንያት ያጣሉ” ብለዋል።

በተጨማሪም ብጹእ ካርዲናል ቼርኒ እንዳሉት በርካታ መርከበኞች እና የባህር ተጓዦች “በፍትህ መጓደል፣ ብዝበዛና እኩልነት ማጣት” ስጋት ላይ ናቸው በማለት ገልጸዋል።

ስቴላ ማሪስ

ብጹእ ካርዲናሉ መልዕክታቸውን በመቀጠል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በበጎ ፈቃደኞች እና ካህናት በኩል በመርከብ ኢንዱስትሪ ውስጥ ላሉት ሰዎች የምታደርገውን የባህር ላይ ሃዋሪያዊ አገልግሎት እና ለመብቶታቸው መከበር የምታደርገውን የጥብቅና አገልግሎትን በማንሳት አበክረው ገልጸዋው።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የባህር ላይ የምትሰጠው ይህ ሐዋርያዊ አገልግሎት 'ስቴላ ማሪስ' ወይም 'የባህር ኮከብ' በመባል የሚታወቀው የጥንት ‘የማሪያን’ ወይም በቅድስት ድንግል ማሪያም የተሰየመ ስያሜ ሲሆን፥ ይህ አገልግሎት በዓለም ዙሪያ ባሉ በመቶዎች በሚቆጠሩ ወደቦች ላይ ይገኛል።

ብጹእ ካርዲናሉ እንደጻፉት፥ ይህ “የባሕር አገልግሎት” ዋና ዓላማው የባህርን ዳርቻ በተለያዩ መንገዶች ማለትም በባህር ላይ የሚሰሩትን ሰዎች በአካል በማግኘት ወይም በጸሎት በመታገዝ የሰራተኞቹን ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሁኔታዎች ማሻሻል፣ ለሠራተኞቹ ክብር እና መብት መሟገት እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን እና ፖሊሲዎችን በማጠናከር ወደ መሃል ለማቅረብ የሚተጋ አገልግሎት ነው።

ባሕር በክርስቲያን ታሪክ ውስጥ

ብጹእ ካርዲናል ቼርኒ በመልዕክታቸው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ፣ በቤተክርስቲያኗ ታሪክ ውስጥ ከባህር ጋር ጥልቅ ትስስር የነበራቸውን ሁለት ክፍሎችን ለማሳየት ሞክረዋል።

በመጀመሪያ፣ ብዙ ጊዜውን በባህር በመጓዝ፣ የወደብ ከተማ ለሆነችው ቆሮንቶስ የቤተክርስቲያንን መልእክት በማሰራጨት ያሳለፈውን የቅዱስ ጳውሎስን ጉዞ አንስተዋል። ብጹእነታቸው እንዳሉት ሃዋሪያው ጳውሎስ እዚያ ብዙ ተከታዮችን ያገኘ ቢሆንም፥ እነዚህ አዳዲስ ክርስቲያኖች ብዙም ሳይቆይ እርስ በርሳቸው ተከፋፍለዋል።

ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ይህንን ክፍል የሚመለከት ሲሆን፣ ብፁእ ካርዲናል እንደጻፉት፣ “ቤተ ክርስቲያን ዛሬ እርስ በርስ በሚለያዩ ሰዎች መካከል ብቻ ሳይሆን፣ መከፋፈል እና የእርስ በርስ ግጭት በሚያጋጥማቸው ሰዎች መካከል ለበለጠ አንድነት እንድትሠራ ማበረታቻ ነው” ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናል ቼርኒ በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጡት፣ ክርስትና በመላው ዓለም የተንሰራፋው ብዙውን ጊዜ በባህር በኩል የመሆኑን እውነታ አስምረውበታል።

ብጹእ ካርዲናል ቼርኒ “ቤተክርስቲያናችን ዛሬ የክርስቶስን ፍጹም አዲስ መልዕክት ከባህር ላይ ሐዋርያት እና ከሌሎች ሚስዮናውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰሙ የባህር ዳርቻ ማህበረሰብ ከሆኑት ነዋሪዎች መነሳሳትን ማግኘት ትችላለች” ካሉ በኋላ በመጨረሻም “የምናውቀውንው ምቾት ከመረጥን ለህይወት አማራጮች ክፍት መሆን አንችልም” ሲሉ ደምድመዋል።
 

25 June 2024, 16:11