የድርጅቱን 97ኛ ምልአተ ጉባኤን ምክንያት በማድረግ የቀረበ የመክፈቻ  መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የድርጅቱን 97ኛ ምልአተ ጉባኤን ምክንያት በማድረግ የቀረበ የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት   (Dicastero per le Chiese orientali)

ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሬቲ፣ በመጨረሻው የድህነት ደረጃ ላይ የሚገኙትን መርዳት እንደሚገባ አሳሰቡ

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሐላፊ እና ለአካባቢው የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሬቲ፣ በመጨረሻው የድህነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ማኅበረሰቦችን መርዳት እንደሚገባ አሳሰቡ። ካርዲናሉ ይህን የተናገሩት የድርጅቱን 97ኛ ምልአተ ጉባኤን ምክንያት በማድረግ በሮም በመካሄድ ላይ ያለው ስብሰባ የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ነው። ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሬቲ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ላይ ማሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ በትህትና እና በእምነት የተሞላ የበጎ አድራጎት ስልት ሊኖር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። እንዲሁም ለጥቅማቸው ሲሉ ድጋፍ በሚያደርጉ መንግሥታት እና ሕዝባዊ ተቋማት ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ክርስቲያናዊ ድጋፍ ወደ ሕይወት በሚወስደው ጠባብ በር በኩል መሆን አለበት” በማለት የተናገሩት፥ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሐላፊ እና የአካባቢው አገራት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ፕሬዝደንት ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሬቲ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለተገኙት ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካኅናት እና ምዕመናን ይህን ያስታወሱት ማክሰኞ ሰኔ 18/2016 ዓ. ም. ማለዳ በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ኤጀንሲዎችን በሚያስተባብር 97ኛው የምልአተ ጉባኤ የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው። ስብሰባው ሮም ውስጥ በሚገኝ የኢየሱሳውያን ማኅበር ጠቅላይ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን እስከ ሐሙስ ሰኔ 20/2016 ዓ. ም. ድረስ እንደሚቀጥ ከሥፍራው የደረሰን ዘገባ አስታውቋል።

ለሰላም የተደረገ ጸሎት
በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ በሕይወት ያሉትን ሆነ በሞት የተለዩ በጎ አድራጊዎችን በጸሎት ያስታወሷቸው ሲሆን በጦርነት የሚሰቃዩ አገራትን ለቸሩ እግዚአብሔር እና ለእመቤታች ቅድስት ማርያም ወላዲተ አምላክ አማላጅነት አደራ በመስጠት በመወያያ ርዕሦች ላይ በተቀመጡ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የበጎ አድራጎት ዘይቤ
ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሬቲ ከማቴ. ምዕ. 7፤12-14 ተወስዶ በዕለቱ በተነበበው ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ መዕዳን፥ “የክርስቲያን በጎ አድራጎት ዘይቤ በትህትና እና በእምነት የተሞላ፣ ምንም ለሌላቸው ሰዎች ለመስጠት በሚፈልግ ዘይቤ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” ብለው፥ ከሌሎች ልንቀበል የምንፈልገውን ያህል የምንሰጥበት መሆን አለበት” ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሬቲ በማከልም፥ ይህ ብቻ ሳይሆን እኛ ወደ ድሆች ሄደን ልናገኛቸው ይግባል” ብለዋል። በመቀጠል የበጎ አድራጎት ሠራተኞች ለሚመሩት የመስዋዕትነት ሕይወት እንዲሁም ወደ አደገኛ እና በአስከፊ ሁኔታዎች ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች መካከል ሆነው ለሚያቀርቡት አገልግሎት ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል። ድካማቸውንም እግዚአብሔር እንደሚቆጥርላቸው ለጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ታዳሚዎች አረጋግጠውላቸዋል። በተጨማሪም በቃለ ምዕዳናቸው አገልግሎቱ ለሌሎች መልካም እንድናደርግ የቀረበ ጥሪ እንደሆነ አስረድተው፥ “እኛ ወንድማማቾች እና እህትማማቾች እንጂ ሀብታሞች ወይም ድሆች አይደለንም” ብለዋል።

ተቋማዊ ሚናዎችን ሳንመለከት ነገር ግን እራስ ለሌሎች አገልግሎት መስጠት
“እኛ ዲያቆናት ነን፣ እኛ አገልጋዮች ነን፣ እኛ በመስቀል የተሰቀለው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን” በማለት የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ ጉጄሬቲ፥ ስለሆነም ይህ የተልዕኳችን መመዘኛ መሆን አለበት” ብለዋል። ስለዚህም “በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም ውስጥ ለማገልገል የመረጥንበት መንገድ ጥሪ ስለሆነ መንፈስ ቅዱስን እንድንመለከት፣ በተቋማዊ ሚና ላይ ብቻ እንዳንቆይ የተሰጠን ማስጠንቀቂያው ነው” በማለት ገልጸዋል። በመቀጠልም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ዕርዳታን የሚሰጡ መንግሥታትን እና መንግሥታዊ ተቋማትን ሲያስጠነቅቁ፥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አርአያ መከተል እንደሚገባ በማሳሰብ፥ ቅድስት ድንግል ማርያም ምንም እንኳን ነፍሰ ጡር ብትሆንም ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ያደረገችውን ጉዞ አስታውሰዋል።

የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አባላት በዓለም ዙሪያ ለመመስከር የተጠሩበት መንገድ በእርግጠኝነት ቀላል እንዳልሆነ፣ ነገር ግን በትልቅ ልግስና የተከናወነ ጉዞ እንደሆነ አስረድተዋል። ደስታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ጋር የሚስማማ ብቻ ሳይሆን የዚህ ደስታ መገለጫዎች ለመሆን ያነሳሳን ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ጥሪ ውስጥ የተካተተ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘት
ምልአተ ጉባኤ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 19/2016 የቀጠለ ሲሆን፥ በተለይ በቅድስት ሀገር፣ በዩክሬን፣ በኢትዮጵያ እና በካራባክ ክልል ላይ በሚታይ የሰላም እጦት ላይ ከመወያየቱ በተጨማሪ ከእነዚህ አካባቢዎች ውጭ በሚደረጉ የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ሐዋርያዊ እንክብካቤ ላይም ተወያይቷል። በመጨረሻም የጉባኤው ተካፋዮች ሐሙስ ሰኔ 20/2016 ጠዋት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸው ተገልጿል።

 

26 June 2024, 17:32