ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሊባኖስ የሚያደርጉትን የአምስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀመሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በመካከለኛው ምስራቅ አገር ሊባኖስ የሚያደርጉት የአምስት ቀናት ጉብኝት ከዚህ በፊት በተዘጋጀላቸው የሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር መሠረት እንደሆነ ታውቋል። ብፁዕነታቸው በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት የአገሪቱ መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ባለሥልጣናትን፣ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችን እና በአገሪቱ ውስጥ የሰብአዊነት ዕርዳታ መዋቅሮችን ከሚመሩ የማልታ ሉዓላዊ ማኅበር አባላትን እንደሚጎበኟቸው ታውቋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ሰኔ 16/2016 ዓ. ም. በሊባኖስ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የጀመሩት ከአገሪቱ መንግሥታዊ ባለሥልጣናት፣ ከማሮናዊት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች፣ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና የሃይማኖት አባቶች ጋር በመገናኘት እንደ ነበር ተገልጿል።
ብፁዕነታቸው ሰኞ ሰኔ 17/2016 ዓ. ም. በሊባኖስ የማልታ ሉዓላዊ ማኅበር አምባሳደር ክቡር ማርያ ኤሜሪካ ኮርቴዘ እና የመንግሥት ተወካዮች በተገኙበት በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ካቴድራል ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በሊባኖስ የማልታ ሉዓላዊ ማህበር የሚተዳደሩ አንዳንድ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማዕከላትን ከጎበኙ እና አንዳንድ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ከተሳተፉ በኋላ ሰኔ 20/2016 ዓ. ም. ወደ ቫቲካን እንደሚመለሱ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ገልጿል።
ለችግሩ ተቋማዊ መፍትሄን መፈለግ
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በቅርቡ በጣሊያን የመንግሥት ተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፥ በሊባኖስ ውስጥ በሚገኝ የማልታ ሉዓላዊ ማኅበር በኩል ሊባኖስን እንዲጎበኙ ግብዣ እንደቀረበላቸው ገልጸው፥ ይህም አገሪቱን በደረሰባት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ትልቅ ማኅበራዊ ተጽዕኖ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
“የሊባኖስ ቀውስ ሁሉን አቀፍ ቀውስ ነው” ያሉት ብፁዕነታቸው፥ “በእርግጥ በሊባኖስ ውስጥ የሚገኝ የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ ሁሌም እንደሚያደርገው፣ ለችግሩ ተቋማዊ መፍትሄን እንዲያገኝ የሚያግዙት መሆኑን ገልጸዋል።
የማልታ ሉዓላዊ ማኅበር ቀውስን ለማስወገድ በግንባር ቀደምትነት ይሠራል
በሊባኖስ ውስጥ የሚገኝ የማልታ ሉዓላዊ ማኅበር ከ70 ዓመታት በላይ በቀዳሚነት መሠረታዊ የሆኑ የጤና አጠባበቅ እና ማኅበራዊ ድጋፎችን ለሕዝቡ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ከማኅበሩ የወጣው መግለጫ አስታውቋል።
እንደ ጎርጎሮሳዊው ከ 2020 ዓ. ም. ጀምሮ ማኅበሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማበረታታት እና በሊባኖስ ውስጥ እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ሲባል በእርሻ ሥራዎች ላይ ቁርጠኝነቱን ማሳየቱ ታውቋል።
ማኅበሩ በሊባኖስ ውስጥ አሁን ያለውን 69.26% የእርሻ መሬትን በያዝነው ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 75% ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
80% የሚሆን ሕዝቧ በድህነት ውስጥ በሚኖርባት እና በተለይም በቅድስት ሀገር ጦርነት በመጀመሩ ምክንያት እየጨመረ በመጣው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሊባኖስን ለሚያጋጥማት ከባድ የኢኮኖሚ ውድቀት የእርሻ ሥራዎችን ማሳደግ ለቀውሱ ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ እንደሆነ ተገልሷል።