በስዊዘርላንድ ስለ ዩክሬን ሰላም ላይ የተካሄደ ጉባኤ ላይ የተገኙት ብጹእ ካርዲናል ፓሮሊን ፒየትሮ በስዊዘርላንድ ስለ ዩክሬን ሰላም ላይ የተካሄደ ጉባኤ ላይ የተገኙት ብጹእ ካርዲናል ፓሮሊን ፒየትሮ  (© KEYSTONE POOL / ALESSANDRO DELLA VALLE)

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ውይይት ሰላምን ለማስፈን ብቸኛው መንገድ ነው አሉ

በዩክሬን ሰላም እንዲመጣ ከፍተኛ ደረጃ ያለው የሰላም ጉባኤ ላይ ለተሰበሰቡት የዓለም መሪዎች ንግግር ያደረጉት የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮን መልእክት ደግመው በማስታወስ፥ እውነተኛ፣ የተረጋጋ እና ፍትሃዊ ሰላም ለማምጣት ብቸኛው መንገድ በሚመለከታቸው አካላት መካከል የሚደረግ ውይይት ነው ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከሁለት ዓመታት በላይ በዘለቀው የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ላይ የመከረውና በስዊዘርላንድ ቡርኼንስቶክ ከተማ ከሰኔ 8-9 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት የተከሄደው የዩክሬን ሰላም ጉባኤ ትናንት ማምሻውን የጋራ መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

በጉባኤው ከ 93 በላይ አገሮች፤ ሶስት የአውሮፓ ህብረት ተቋማትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር ተሳትፈዋል።

በዚህ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የዘወትር መልዕክት በማስተጋባት፥ በሚመለከታቸው አካላት መካከል የሚደረግ ውይይት እውነተኛ፣ የተረጋጋ እና ብቸኛው የሰላም መንገድ መሆኑን ደጋግመው ተናግረዋል።

የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቅድስት መንበር ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ሲገልጹ “ከዩክሬን እና ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር ያላትን መደበኛ ግንኙነት አጠናክራ ለመጠበቅ” እና ሊሆኑ የሚችሉ የሽምግልና ተነሳሽነቶችን ለመርዳት ቅድስት መንበር ያላትንን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የቅድስት መንበር ልዑካን

በስዊዘርላንድ የቅድስት መንበር ሐዋሪያዊ መልዕክተኛ ብጹእ አቡነ ማርቲን ክረብስ እና የሃገራት እና የዓለም አቀፍ የመንግስት ፅህፈት ቤት ድርጅቶች የግንኙነቶች ክፍል ሃላፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጳውሎስ ቡትናሩ የተካተቱበት የቅድስት መንበር የልኡካን ቡድን በብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የተመራ ሲሆን፥ የስዊዘርላንድ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪን የጋራ ግብዣን8 በመቀበል ነበር ጉባዔው ላይ የተገኙት።

ቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ እና ሰብአዊ ጥረቶችን በማንኛውም መንገድ ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን፥ ከታዛቢነት ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ የመሪዎች ስብሰባ የመጨረሻ መግለጫ ላይ ፊርማዋን አላኖረችም።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በንግግራቸው “በዩክሬን በጥንቃቄ የተዘጋጀ” ያሉትን ተነሳሽነት በደስታ እንደሚቀበሉት ገልጸው፣ ሃገሪቷ እራሷን ከጥቃት ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ፣ በዲፕሎማሲያዊው ግንባርም ያለማቋረጥ በመስራት ፍትሃዊና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በመጓጓት ነው” በማለት ተናግረዋል።

ብጹእነታቸው አክለውም በጦርነት ውስጥ ሆኖ “በመልካም ዓላማ፣ እምነት እና ፈጠራ” ግጭቱን የሚያበቃበትን መንገድ መፈለግ አስፈላጊ መሆኑን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ውይይት ብቸኛው መንገድ ነው

ውይይት ብቸኛው መንገድ መሆኑን በተደጋጋሚ ጥሪ ያስተላለፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሲሆኑ፥ በተለይ ለሀገር መሪዎች ባቀረቡት ጥሪ “እውነተኛ፣ የተረጋጋና ፍትሃዊ ሰላም ለማምጣት ብቸኛው መንገድ በሁሉም አካላት መካከል የሚደረግ ውይይት ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ብፁእ ካርዲናሉ “ቅድስት መንበር ባላት ስምምነት መሰረት በጉባኤው ላይ የተሳተፈችው በታዛቢነት ስለሆነ ፊርማውን ለመፈረም እንደማትገደድ እና በተለይ ለዓለም አቀፍ ሕግጋትና ለሰብዓዊ ጉዳዮች ክብር ትኩረት በመስጠት ተሳትፋለች” ብለዋል።

ስለዚህ የመጀመሪያውን አሰራር በተመለከተ “የእያንዳንዱን ሀገር ሉዓላዊነት እና የግዛቱን አንድነት የማክበር መሰረታዊ መርህ ትክክለኛነት” አረጋግጠዋል።

ህጻናትን ወደ አገራቸው መመለስ

ቅድስት መንበር ጦርነቱ ያስከተለው አሳዛኝ ሰብአዊ መዘዝ በእጅጉ እንደሚያሳስባት እና በተለይም ህጻናት ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እና እስረኞች እንዲፈቱ ለማበረታታት ቁርጠኛ ነች ብለዋል።

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከህጋዊ አሳዳጊዎቻቸው ጋር የማገናኘቱን አስፈላጊነት ከገለጹ በኋላ፥ “በነሱ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ዓይነት ብዝበዛ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ አሳስበዋል።

ስለዚህም ይህንን ሂደት ለማመቻቸት ዬትኛውንም አይነት የግንኙነት መንገዶች እንዲጠናከሩ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ጠይቀዋል።
ቅድስት መንበር የዩክሬን ሕፃናትን ከሩሲያ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ዓለም አቀፍ ጥምረት በታዛቢነት እንደምትሳተፍ እና ከዩክሬን እና ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደምትፈጥር አስረድተዋል ። ተጨባጭ ጉዳዮችን ለመፍታት በማሰብ ብጹእ ካርዲናል ማትዮ ዙፒ የኪየቭ እና የሞስኮ ጉብኝት ተከትሎ የተፈጠረው የ ‘አድ ሆክ’ ወይም እንደአስፈላጊነቱ የሚደረግ የውይይት አካሄድ ውጤታማነትንም ገልጸዋል።
እስረኞች
በተጨማሪም የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትኩረታቸውን በሲቪል እና በወታደራዊ እስረኞች ጉዳይ ላይ በማድረግ “የጄኔቫ ስምምነቶችን ባለማክበር በየጊዜው የሚወጡ አሳዛኝ ሪፖርቶች” አንስተው አሳስበዋል።

“ሲቪሎችን በቀጥታ ስለሚመለከተው በተለይ ስለ አራተኛው ኮንቬንሽን ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመሆን አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የጦር እስረኞች ሁኔታን ሊገመግም የሚችል የጋራ የህክምና ኮሚሽን ለማደራጀት ችግሮች አጋጥመዋል” በማለት ተናግረዋል።

የቅድስት መንበር ቁርጠኝነት

ብጹእ ካርዲናሉ የቅድስት መንበር ቁርጠኝነትን ሲያረጋግጡ “ከዩክሬን እና ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር መደበኛ ግንኙነት እንዲኖር እና በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለው እና የተጎዱትን የሚጠቅሙ የሽምግልና ውጥኖችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ናት” ብለዋል።

በተጨማሪም ሃገራት እና ሌሎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት ሰብአዊም ሆነ ፖለቲካዊ ባህሪ ላላቸው ጉዳዮች ድጋፍ ለማድረግ እና የሽምግልና ሁኔታዎችን ማመቻቸት የሚቻልባቸው መንገዶች እንዲፈጠር ታበረታታለች ተብሏል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሲያጠቃልሉ “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ወክዬ ብጹእነታቸው ስቃይ ውስጥ ከሚገኙት የዩክሬን ሕዝብ ጋር ያላቸውን ግላዊ ቅርበት እና ለሰላም ያላቸውን የማያወላውል ቁርጠኝነት ማረጋገጥ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
 

18 June 2024, 13:33