አዲስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት መድረክ እንዲኖር ጥሪ ቀረበ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፣ ብፁዕ ካርዲናል ፒትሮ ፓሮሊን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት እና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች በተገኙበት 'የሃይማኖት ነፃነት እና አጠቃላይ የሰው ልጅ ልማት፡ አዲስ ዓለም አቀፍ መድረክ' የሚል ጉባኤ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በሮም ተካሂዷል።
በቅድስት መንበር የማልታ ሉዓላዊ ማህበር፣ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የአትላንቲክ የነፃነትና የብልጽግና ማዕከል አማካሪ ምክር ቤት እና በሮም በሚገኘው አርባኒያና ጳጳሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም አዘጋጅነት የተካሄደው የአንድ ቀን ጉባኤ አቬንታይን ሂል በሚገኘው በማልታ ሉአላዊ ማህበር ዋና መሥሪያ ቤት የተካሄደ ሲሆን፥ በጉባኤውም ሀይማኖትን የሚዳስሡ እና አካታች ፖሊሲዎችን እና ተሳትፎዎችን ለማዳበር የሚያስችሉ ማዕቀፎችን እና ስልቶችን በመዳሰስ፥ ዝግጅቱ በተለያዩ የውይይት መድረኮች ተከፋፍሎ እንዲካሔድ ተደርጓል።
በቅድስት መንበር የማልታ ሉአላዊ ማህበር አምባሳደር አንቶኒዮ ዛናርዲ ላንዲ እንግዶቹን በደስታ ተቀብለው ስለ አንድ አስፈላጊ እና ብዙ ጊዜ ግራ አጋቢ ስለሆነ ጉዳይ መናገር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። አቶ አንቶኒ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ይህ ጉባኤ በመላው ዓለም አስከፊው ጦርነት እየተደረገ ባለበት ወቅት የተካሄደ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ጉባኤ በአይነቱ የመጀመሪያው ነው ብለዋል።
የረቡዕ ስብሰባ የጀመረው ዓለም አቀፉን የሃይማኖት ነፃነት ቀውስ በሰው ልጅ ልማት ላይ ያለው ሚና በመወያየት ነበር። የቫቲካን የግዛት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ፀሐፊ ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ቅድስት መንበር በ ‘ሃይማኖት ነፃነትና የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት’ ላይ ያላትን አመለካከት አብራርተዋል።
ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ነፃነትን ለማስከበር ቃል መግባቱን አስታውሰው፣ በወቅቱ ‘ዲጊኒታቲስ ሂዩማኔ’ በመባል የወጣው ሃዋሪያዊ ሰነድ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ የሰዎች እና የማህበረሰቦች፣ የማህበራዊ እና የሲቪል ነፃነት መብትን እንደሚያብራራ ገልጸው፥ “ይህ በእግዚአብሔር ፈቃድና በሰው ልጅ ተፈጥሮ የተቀረጸው ነፃነት ተግባራዊ መሆን አለበት” ሲሉ በሰብዓዊ መብትና በእምነት ነፃነት መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ተመልክተዋል።
“ይህ ብቸኛው የሰብአዊ መብቶች ገጽታ ባይሆንም ከሁሉም በላይ መሰረታዊ ነው ሊባል ይችላል” ያሉት ብጹእነታቸው፥ “ለሌሎች ሰብአዊ መብቶች ሁሉ መሰረት የሚሆነው የህሊና ነፃነት መብት ነው” ብለዋል። ግለሰቦች ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሕሊናቸውን እንዲጠቀሙ የመንግስት ባለስልጣናት መፍቀድ አለባቸው ካሉ በኋላ፥ “ይህ ደግሞ መሰረታዊ መብቶች እንዳይጣሱ ያረጋግጣል” ብለዋል።
ስለዚህም “የእምነት ነፃነት መብት መጣስ አንድን መብት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶችን የመናድ ውጤት እንዳለው ግልጽ ነው” በማለት አብራርተዋል።
4.9 ቢሊየን ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የእምነት ነፃነት ጥሰት ይደርስባቸዋል
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በመቀጠል የሃይማኖት ነፃነት በግለሰብ፣ በቡድን እና በተቋም ደረጃ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ፈተናዎች እያጋጠሙት መሆኑን አንስተዋል።
በአንዳንድ ጥናቶች መሠረት ወደ 4.9 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከባድ ወይም በጣም ከባድ የእምነት ነፃነት በተጣሰባቸው አገሮች ውስጥ መኖራቸው አሳሳቢ ጉዳይ ነው” ሲሉ አክለውም “በዓለም ላይ ካሉት አሥር ዜጎች መካከል ቢያንስ ሰባቱ የዚህ ሰለባ ናቸው፥ በአሁኑ ጊዜ በራሳቸው ሕሊና ላይ ተመስርተው መብቶቻቸውን ለመተግበር ሲሞክሩ ተከልክለዋል ወይም ጉዳት ደርሶባቸዋል” ብለዋል።
በዚህ ረገድ በጣም ተጋላጭ የሆኑት ክርስቲያኖች እንደሆኑ አስረድተው፥ “ከ365 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ክርስቲያኖች በግምት ከሰባት አንዱ በእምነታቸው ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ስደት ይደርስባቸዋል” ካሉ በኋላ፥ በ2015 ዓ.ም. ብቻ በአብያተ ክርስቲያናት እና በክርስቲያናዊ ንብረቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ተዘግቧል” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋራገር እንደ ሌሎች ተናጋሪዎች ሁሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ መስከረም 2008 ዓ.ም. በተባበሩት መንግስታት ጉባኤ ላይ የተናገሩትን በማስታወስ፥ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ለሆኑት ዓለማዊ እና መንፈሳዊ ቁሶች: እንደ መኖሪያ ቤት፣ የተከበረ እና በቂ ደመወዝ ያለው ሥራ፣ በቂ ምግብ እና የመጠጥ ውሃ፣ የሃይማኖት ነፃነት እና በአጠቃላይ የመንፈሳዊ ነፃነት እና ትምህርት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል” ካሉ በኋላ፥ በመቀጠል “የጎረጎሳዊያኑ የ2030 አጀንዳ ያልተሟላ ነው ምክንያቱም መንፈሳዊውን ገጽታ በመተው የሰው ልጅ ዓለማዊ እድገት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው” ብለዋል።
ሃገራት ገለልተኝነትን መለማመድ አለባቸው
የቫቲካኑ ዲፕሎማት “አንድ ግለሰብ ለጋራ ጥቅም አስተዋፅዖ ሲያደርግ ደህንነትን የሚያገኝበት ሂደት ነው” በማለት በተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት ላይ በማስተንተን እንደተናገሩት “የሃይማኖታዊ ነፃነት ዘላቂ የሰው ልጅ እድገትን ለማምጣት ወሳኝ ሚና ይጫወታል” ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ መንግስታት ገለልተኝነትን እንዲለማመዱና ለሀይማኖት ቡድኖች እና ሁሉም ግለሰቦች ሃይማኖታዊ እምነታቸው በአደባባይ እንዲገለጹ እኩል መብት እንዲሰጡ እና ሁልጊዜም የጋራ ተጠቃሚነትን ማስከበር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በማጠቃለያቸውም “የእምነት ነፃነትን ማግኘት የቻሉ ሰዎች የራሳቸውን ሁለንተናዊ እድገት ማስመዝገብ የሚችሉ ሲሆን የሰፊው ህብረተሰብ የልማት ወኪሎች ይሆናሉ” ብለዋል።
የሰው ልጅ የተቀናጀ ልማት፡ የመመሪያ መርህ
በመቀጠልም ንግግር ያደረጉት በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኖትር ዴም ዩኒቨርሲቲ የኪዩፍ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ሃላፊ የሆኑት ስኮት አፕልቢ በተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ዓለም አቀፍ ተሳትፎን ስለሚጠይቀው የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ልማት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሁሉም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በተለይም በእርሳቸው አስተያየት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በአጽንኦት የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ልማትን እንደ መመሪያ መርሕ እንደወሰዱት አስታውሰው፥ ይህም ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር መተሳሰብን የሚደግፍ ፅንሰ-ሀሳብ መሆኑን እና በመካከላቸው ያለውን ጉልህ ትስስር ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ጠቅሰው፣ የሀይማኖት ነፃነት እና አጠቃላይ የሰው ልጅ እድገት እና ዛሬ ላይ ስላለው ጠቀሜታው አብራርተዋል።
የሰው ልጅ የተቀናጀ እድገት ለሃይማኖታዊ ነፃነት አስተዋፅዖ ያደርጋል
የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት እሳቤ ‘ከማህበረሰቦች የተነጠለ ሰው’ ከሚለው ሀሳብ ጋር የማይጣጣም፣ ነገር ግን ሰውን እንደ ማህበረሰብ የሚመለከት እና በሰብአዊ መብቶች ላይ ለሚደረጉ ውይይቶች ዋጋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የእምነት ነፃነት መብት ላይ የሚገባውን ያህል ወሳኝ እና ቆራጥ በሆነ መልኩ ስላልተሰራበት ባለመሆኑ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ ማዕቀፍ ውስጥ በተሻለ ሁኔታ መመስረት እንዳለበትም ሃሳብ ሰጥተዋል።
“የተቀናጀ የሰው ልጅ እድገት” ይላሉ አቶ አፕልቢ “የሃይማኖት ነፃነትን ለመጠበቅ እና የሰብአዊ መብቶችን ለማጠናከር በሚሰራው ሥራ ላይ ተጨማሪ ማጠናከሪያ ይሆናል” ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የተደረገው አበረታች ዉይይት የሃይማኖታዊ ነፃነትን እና የሰው ልጅን ሁለንተናዊ እድገት በተለይም የተገለሉትን፣ አልፎ ተርፎም ሙሉ በሙሉ የተረሱትን ለመድረስ የዋና ዋና ባለድርሻ አካላትን እንቅስቃሴ በማገናዘብ በየደረጃው ያለውን ፍላጎት አንስተዋል።
ረቡዕ ከሰአት በኋላ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረጉ ውይይቶችን ያካተተ የሰው ልጅ እድገትን፣ ሰብአዊ ክብርን እና የእምነት ነፃነትን በአንድ ላይ በማያያዝ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በተጨማሪም ሃሳቦችን ወደ ፖሊሲ ስለመቀየር እና የሃይማኖት ነፃነትን በሰው ልጅን ሁለንተናዊ እድገት መነጽር ማየት እንዴት ለውጥ እንደሚያመጣ፣ ብሎም ለሃይማኖታዊ ነፃነት እና ለሰው ልጅ አጠቃላይ እድገት እንዴት ውይይቱን ወደ ተግባር መለወጥ የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በመወያየት ጉባኤው ተደምድሟል።