ቅድስት መንበር በሴቶች ላይ በሚደርሰው ህገወጥ ዝውውር ላይ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ብዙውን ጊዜ በስውር የሚካሄደው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሰውን ልጅ ክብር የሚጎዳ እና በተጎጂዎችም ላይ ጥልቅ ጠባሳ የሚፈጥር ሲሆን ይህም ብዙውን ጊዜ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ በሰፊው ይስተዋላል በማለት ያረጋገጡት በጄኔቫ ለሚገኙት የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሲሆኑ፥ ይሄንን ያሉት በሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 56ኛ መደበኛ ጉባኤ ‘አንቀጽ 3፡ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በተለይም ሴቶች እና ህፃናት - ጄኔቫ’ በሚል መሪ ቃል ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. የተደረገውን ልዩ ውይይት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ነው።
ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በጥብቅ ማውገዝ
የመግልጫው ፅሑፍ በተደጋጋሚ እንደገለጸው “ቅድስት መንበር ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በከባድ የሰው ልጅ ክብር ጥሰት ጋር መቆጠር አለበት ብላ ታምናለች” በማለት አጥብቆ አረጋግጧል።
በልዩ ሁኔታ የቅድስት መንበር ልዑካን ስደተኞችን በማስታወስ “በባህር ላይ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ተቀባይነትን እና የተሻለ ሕይወት ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች በምትኩ ብዝበዛና ሞት ሊገጥማቸው አይገባም" ሲሉ አሳስበዋል።
ልዑካን ቡድኑ በተጨማሪም ‘በየብስ እና በባህር የሚደረገው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ብዙ ጊዜ በድብቅ የሚካሄድ እና የማይታይ ነው’ በማለት በጽኑ አውግዟል።
“ይህን አሳዛኝ እና ዓለም አቀፋዊ መቅሰፍት ለመጋፈጥ በግዴለሽነት መቆየት የለብንም” የሚለው መግለጫው “ለእነዚህ እውነታዎች ትኩረት እንዳንሰጥ የሚያደርገውን እና የማይገሰሰውን የሰብአዊነት ክብርን የሚያጠፋውን ይህን የመሰለ የግዴለሽነት ባህል ውድቅ ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው” ይላል መግለጫው።
“ይህን አሳዛኝ እና ዓለም አቀፋዊ መቅሰፍት ለመጋፈጥ ግዴለሽ መሆን የለብንም”
ድሆች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው
በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እና የባርነት ወጥመድ ውስጥ የመውደቅ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፣ ስለዚህም የአዕምሮ፣ የነፍስ እና የሥጋ ሰላምን መልሰው የሚያገኙበት እና የሚያብቡበት አስተማማኝ ቦታ እንዲያገኙ መርዳት የጋራ ኃላፊነታችን መሆኑን ቅድስት መንበር አሳስባለች።
“ይህ በተለይ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው” የሚለው መግለጫው “የዓለም አቀፍ ትብብር እጦት እንዲሁም በአገር ውስጥ፣ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ሃላፊነት ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን ብዙውን ጊዜ በባህር ላይ ለሚሰደዱ ስደተኞች ጥበቃ እጦት አስተዋጽኦ ያደርጋል” የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
ሁሉም ጥረቶች እንዲደረጉ ጥሪ ቀርቧል
ቅድስት መንበር “በዚህ አስከፊ የዓለማችን እውነታ ፊት ቸልተኛ እንድንሆን ሳይሆን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የምንችለውን ሁሉ ጥረት እንድናረግ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሰለባ ለሆኑት ሁሉ ከአምላክ የተሰጣቸውን ክብር እንዲያገኙ ለማረጋገጥ ተጠርተናል” በማለት ጥሪዋን አስተላልፋለች።
ፍላጎቶችን መጫን
የልዑካን ቡድኑ፣ እየተዳከሙ የመጡት እሴቶቻችን እና ግንኙነቶቻችን “ማህበራዊ አቋማችንን እንደሚያበላሽ እና በቤተሰብ ላይ ጎጂ ውጤት እንዳለው” በቁጭት ገልጿል።
“ሃገራት የሴቶችን ክብር በብቃት የሚያስጠብቁ ህጎችን እንዲያወጡ ብቻ ሳይሆን፥ ለሴተኛ አዳሪነት ተጎጂዎች ተግባራዊ ድጋፍ እንዲሰጡ እና የዚህ አይነት ጥቃት መንስኤዎችን ለመፍታትም ተነሳሽነትን ሊያሳዩ ይገባል” በማለት በልዩ ውይይቱ ላይ በግልጽ ተመላክቷል።
የችግሩ ሰለባዎችን መደገፍ
መግለጫው የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ጉባኤዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሴተኛ አዳሪነት ሥርዓት ውስጥ ያሉትን በድፍረት እና በርኅራኄ በማገዝ ብሎም ከዚህ ተግባር ወጥተው ሕይወታቸውን መልሰው እንዲገነቡ ድጋፍ በማድረግ የቆየ ታሪክ እንዳላቸው አስታውሷል።
ሆኖም የሴቶች እና ልጃገረዶች ጥቃት እና ብዝበዛ በማያቋርጥ ሁኔታ እና ስፋት መቀጠሉን ቅድስት መንበር በመግለጽ፣ የችግሩ ሰለባዎችን ለመርዳት ተጨባጭ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስባለች።