ሊቀ ጳጳስ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ ሊቀ ጳጳስ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ 

ቅድስት መንበር አስቸኳይ የአየር ንብረት እርምጃ እና የስደተኞች ጥበቃ እንዲደረግ ጠየቀች

በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) 34ኛው የፕሮግራሞች እና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጉባኤ ላይ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ የአየር ንብረት ለውጥ መላመድ፣ የአደጋ ስጋት ቅነሳ እና የአየር ንብረት ፍልሰተኞችን ለመጠበቅ አጠቃላይ፣ የሰው ልጅን ያማከለ አካሄድ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በጄኔቫ በተካሄደው 34ኛው የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የፕሮግራሞችና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊት ሊቀ ጳጳስ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ ባደረጉት ንግግር “ለአየር ንብረት ለውጥ ዝግጁነት፣ ለአደጋ ስጋት ቅነሳ እና ለአየር ንብረት ለውጥ መላመድ” አስቸኳይ የሆነ ሁሉን አቀፍ እና ሰውን ያማከለ አካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ስጋት አስተጋብተዋል

ቅድስት መንበርን ወክለው ንግግራቸውን የጀመሩት ሊቀ ጳጳስ ኤቶሬ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ስጋት በማስተጋባት፥ በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን በማጉላት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ በመጣው የተፈናቃዮች ቁጥር ይበልጥ ግልጽ ሆኗል ብለዋል።

ይህንንም በማስመልከት “በ 2014 ዓ.ም. በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት ወደ 33 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ በ 2015 ደግሞ በጎርፍ፣ አውሎ ንፋስ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የሰደድ እሳት እና ሌሎች አደጋዎች ምክንያት 26.4 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል” ብለዋል ሊቀ ጳጳሱ።

እነዚህ አሃዞች የሰው ልጅ ምን ያክል ለአየር ንብረት ለውጥ እና ለተፈጥሮ አደጋዎችን እንደተጋለጠ አጉልተው እንደሚያሳዩ ገልጸው፥ “ከቁጥሮቹ በስተጀርባ ህይወታቸው አደጋ ላይ የወደቀ እውነተኛ ሰዎች መኖራቸውን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም” ብለዋል።

ለእነርሱ “የአየር ንብረት ለውጥ ረቂቅ ሐሳብ አይደለም” ስለዚህም “እግዚአብሔር ከሰጣቸው ክብር ጋር እንዲበለጽጉና እንዲኖሩ በማድረግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል” ብለዋል።

ለስደተኞች የሚደረግ ጥበቃ

ስለ ‘ግሎባል ኮምፓክት ለአስተማማኝ፣ ህጋዊ እና መደበኛ የፍልሰት ጉዳይ’ ያነሱት ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ በድንገት በሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች እና የአካባቢ ለውጦች ምክንያት አገራቸውን ለቀው ለመውጣት የተገደዱ ስደተኞችን የመቀበልና የማቆየት አሠራርን ለማዳበር የተቀመጡትን ዓላማዎች አጉልተው አንስተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፣ ሃገራት መላመድን፣ ችግሮቹን መቀነስን እና መቋቋምን ጨምሮ ተጨባጭ መፍትሄዎችን መስጠት እንዳለባቸው ያሳሰቡት “ዓለም አቀፍ ከለላ ማግኘት በማይችሉበት ጊዜ እንኳን መንግስታት ተጨባጭ መፍትሄዎችን ሳይሰጧቸው ሊተዋቸው አይገባም” በማለት ነበር። “ይህ በማይቻልበት ጊዜ ስደትን እንደ አንድ ልምምድ እውቅና መስጠት ብሎም ለመደበኛ ስደት የመንገዶችን ተደራሽነት እና ተለዋዋጭነት መጨመር አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ሶስት ወሳኝ ነጥቦች

ሊቀ ጳጳሱ በመቀጠል ኮሚቴው ትኩረት እንዲያረግበት ሦስት ወሳኝ ነጥቦችን አንስተዋል። የመጀመሪያው እንደ ጎርፍ እና አውሎ ንፋስ ባሉ ፈጣን ጅምር ክስተቶች ወይም እንደ በረሃማነት እና የባህር ከፍታ መጨመር ባሉ ሂደቶች ምክንያት በአየር ንብረት ቀውስ እና በስደት መካከል ያለውን ግንኙነት መቀበል ነው ብለዋል።

በሊቀ ጳጳሱ የቀረበው ሁለተኛው ነጥብ የመከላከል አቅምን ማሳደግ፣ ስለ አደጋዎቹ ግንዛቤን ማዳበር እና የህብረተሰቡን ተቋቋሚነት በማጎልበት ሕይወትን ለመታደግ እና በተፈጥሮ አደጋዎች የሚደርሰውን ቁሳዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ መቀነስ ነው ብለዋል።

በመጨረሻም ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት፣ የስደት ውሳኔዎችን በመደገፍ እና አሳታፊነት እና ውህደትን ለማጎልበት የአብሮነት ትስስሮችን በመዘርጋት፣ መፈናቀሉ የማይቀር ሆኖ ከተገኘ ሰዎችን ለመፈናቀል እንዲዘጋጁ በንቃት ማስገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።

ለተቀናጀ ሥነ-ምህዳር የተደረገ ጥሪ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቅርቡ እንዳስታውሱን፣ 'የአየር ንብረት ፍልሰተኞችን ክብር እና መብት መጠበቅ የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት ቅድስና መጠበቅ እንደሆነ እና የጋራ ቤታችንን እንድንንከባከብ እና እንድንጠብቅ መለኮታዊ ትእዛዝ እንዲከበር መጠየቅን እንደሚያጠቃልል፣ ወይም ለአየር ንብረት ቀውሱ በከፊል ኢኮኖሚ የተደገፉ ምላሾችን መስጠት ተጨማሪ መፈናቀልን ሊያስከትል እንደሚችል አስምረውበታል።

ሊቀ ጳጳስ ኤቶር ባሌስትሬሮ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ ጤናማ እና የተሳለጠ ሥነ ምህዳር እንዲኖር ቅድስት መንበር ያቀረበችውን ጥሪ እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ‘ላውዳቶ ሲ’ በተሰኝ ሃዋሪያዊ ደብዳቤ አማካይነት ያቀረቡትን ጥሪ ደግመው በማቅረብ፥ “ይህ የአደጋ ስጋትን ለመቆጣጠር እና የአካባቢ ችግሮችን ለመከላከል ወሳኝ ዘዴ ነው” ብለዋል።

በመጨረሻም “እንዲህ ዓይነቱ የተሳለጠ የሥነ-ምህዳር ጥበቃ ከጋራ ጥቅም ጽንሰ-ሀሳብ የማይነጣጠል ነው” ካሉ በኋላ “ይህም ለወደፊት ትውልዶች፣ ለትናንሽ ደሴቶች፣ ታዳጊ ሀገራት እና በጣም ተጋላጭ ለሆኑት የሞራል ግዴታዎች እንደሆኑ፥ ከሁሉም በላይ ለእርስ በርሳችን እና ለጋራ መኖሪያችን የምናረገው እንክብካቤ በጥልቅ የተሳሰሩ ናቸው” ብለዋል።
 

17 June 2024, 14:51