የቫቲካን ባንክ የውስጥ ገጽታ የቫቲካን ባንክ የውስጥ ገጽታ  

የቫቲካን ባንክ እ.አ.አ 2023 ዓ.ም የተጣራ ትርፍ 30.6 ሚሊዮን ዩሮ ማግኘቱን ሪፖርት አድርጓል

የሃይማኖት ሥራዎች ኢንስቲትዩት (IOR) ወይም የቫቲካን ባንክ በመባል የሚታወቀው ተቋም የ 30.6 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ በማሳየት እ.አ.አ የ2023 አመታዊ ሪፖርቱን አሳትሟል።

የእዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

ለአስራ ሁለተኛው ተከታታይ አመታት በተለምዶ የቫቲካን ባንክ በመባል የሚታወቀው የሃይማኖት ስራዎች ኢንስቲትዩት (IOR) ዓመታዊ ሪፖርቱን በ IAS-IFRS አለምአቀፍ የሂሳብ መስፈርት እና ደረጃ መሰረት የተዘጋጀውን እ.አ.አ የ2023 ዓ.ም የፋይናንስ ሪፖርቶችን ይፋ ማደረጉ ተገለጸ።

የሒሳብ መግለጫዎቹ ይፋ በሆኑበት ወቅት ጋር የተያያዘው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲህ ብሏል፡- “እነዚህ የፋይናንስ መግለጫዎች ከኦዲተር ማዛርስ ኢታሊያ ኤስ.ፒ.ኤ.፣ ከኦዲተር ቢሮ ንጹህ አስተያየት አግኝተዋል፣ እና እ.አ.አ ሚያዝያ 30 ቀን 2024፣ በ IOR የበላይ ቁጥጥር ቦርድ በሙሉ ድምጽ ጸድቀዋል። በህግ እንደተደነገገው፣ ከዚያም እንዲገመገሙ ወደ ካርዲናሎች ኮሚሽን ተልከዋል” ሲል መግለጫው አክሎ ገልጿል።

IOR በካፒታላይዜሽን እና በገንዘብ ፍሰት መጠን በጣም ጠንካራ ከሆኑ ተቋማት ውስጥ አንዱ ሲሆን ከካቶሊክ ስነ-ምግባር ጋር የተጣጣመ የኢንቨስትመንት መለኪያ የሚከተል ተቋም ነው።

መግለጫው በመቀጠል፣ “ከስልታዊ ዕቅዱ ግቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃይማኖታዊ ለሆኑ ሥራዎች እና እ.አ.አ በ2023 በዓለም ዙሪያ ላሉ ቤተ ክርስቲያን የመሥራት ተቀዳሚ ሚናውን ሲወጣ፣ IOR የሚከተሉትን ውጤቶች አግኝቷል።

• 30.6 ሚሊዮን ዩሮ የተጣራ ገቢ፣

• + 23% የተጣራ የወለድ ህዳግ፣ + 49% የመሃል ህዳግ፣ + 31% የተጣራ ኮሚሽን ህዳግ፣

• አጠቃላይ የደንበኛ ንብረቶች +4% 5.4 ቢሊዮን ዩሮ ደርሷል፣

• 60% ደረጃ 1 ጥምርታ እና 48% ወጪ/ገቢ ጥምርታ።

እ.አ.አ የ2023 ዓ.ም የፋይናንስ መግለጫዎች ጤናማነት እና የIOR ካፒታል መስፈርቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የካርዲናሎች ኮሚሽን ለሃይማኖት እና በጎ አድራጎት ስራዎች 13.6 ሚሊዮን ዩሮ ለማከፋፈል ወስኗል።

እ.ኤ.አ. በ 2023 ዓ.ም የተጣራ ትርፍ ዕድገት የተገኘው የወለድ ህዳግ ፣ የመሃል ህዳግ እና የኮሚሽን ህዳግ አወንታዊ አስተዋፅዖ በማግኘቱ ነው። ምንም እንኳን የደንበኞችን አገልግሎት ለማሻሻል የታለሙ ኢንቨስትመንቶች እና ዲጂታላይዜሽን ቢደረጉም የወጪ ቁጥጥር ለአስተዳደር ጥረቶች ዋና ነገር ሆኖ ቀጥሏል።

በመጨረሻም “በንብረት አያያዝ ረገድ ተቋሙ ከካቶሊክ እምነት (የእምነት ወጥ ኢንቨስትመንት) ጋር ለሚጣጣሙ መርሆዎች በጣም ቁርጠኛ ነው። በIOR የሚተዳደሩ ምርቶች ጥራት ባለፉት አመታት ለተሰሩት ስራዎች ምስክር ናቸው፣ይህም IOR በሥነ ምግባራዊ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃ ዋቢ እንዲሆን አስችሎታል።

 

17 June 2024, 13:12