የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጉባኤ በተግባር ሠነዱ ላይ ውይይት በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የነገረ መለኮት ሊቃውንት በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ካካሄዱት ስብሰባ ቀጥሎ ባለፈው ዓመት የተመረጡት የሲኖዶሱ መደበኛ ጉባኤ አባቶች እና እናቶች በጥቅምት ወር 2017 ዓ. ም. ለሚካሄደው ጉባኤ መሪ በሚሆናቸው የተግባር ሠነድ ‘Instrumentum laboris’ (IL) ላይ በመወያየት ላይ ይገኛሉ።
ከ114ቱ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች እና ከ9ኙ የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የቀረቡ ሪፖርቶች፣ በመላው ዓለም ከሚገኙ የልዩ ልዩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተቋማት፣ የሥነ-መለኮት 'ትምህርት ቤቶች' እና ግለሰቦች የተሰጡ ምላሾች ታክለውበት የመጀመሪያው የተግባር ሠነድ ረቂቅ ተዘጋጅቷል።
በተጠያቂነት ላይ የሚደረግ ልምምድ
የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች በማብራሪያቸው “ይህን ሰፊ ምክክር ለማካሄድ የፈለግነው የሲኖዶሳዊነት ሂደቱን ያበረታታው እና ከቁምስና ደረጃ ተነስቶ የመጣው የምዕመናኑ አስተያየት ውይይት ተካሂዶበት ተመልሶ መላውን ምዕመናን እንዲደርሳቸው ለማድረግ ነው” በማለት አስረድተዋል። ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥ ጥረታቸው “የሲኖዶሱን ሥራ ትክክለኛነት የሚመሰክር የተጠያቂነት ተግባር ነው” ሲሉም አክለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ሰኞ ዕለት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተገናኙበት ወቅት ቅዱስነታቸው አባላቱ ሥራቸው ተግተው እንዲቀጥሉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።
የሐዋርያዊ ተሐድሶ ንቁ ኃይል
የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት 15ኛ መደበኛ ጉባኤ አባላት ሰኞ ሰኔ 17/2016 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ከተገናኙ በኋላ የወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በሁለቱ ጠቅላላ ጉባኤዎች መካከል ያለው ወቅት ሲኖዶሱ ልዩ ችግሮችን ለመፍታት ሳይሆን ነገር ግን ወደ ሲኖዶሳዊነት እና ወደ ሐዋርያዊ ተሐድሶ ውስጥ መግባት መሆኑን ምእመናን እንዲገነዘቡ አሳስቦ፥ ይህም በመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ መተማመንን የሚጠይቅ ቤተ ክርስቲያን የመሆን መንገድ እንደሆነ ገልጿል።
ከሲኖዶሱ መደበኛ ጉባኤ ውይይት ሰፋ ካለ ግምገማ በኋላ በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ የሲኖዶሳዊነት አዲስ የተግባር ረቂቂ እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል። የተግባር ረቂቁ ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድ ተልኮ ከመጽደቁ በፊት እንደገና ወደ መደበኛው ምክር ቤት እንደሚላክ ተገልጿል።
መግለጫው በመጨረሻም የተግባር ሠነዱ ‘Instrumentum laboris’ (IL) በመጭው ሐምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢ እንደሚታተም አስታውቋል።