ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በዩክሬን በርዲቺቭ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ መርተዋል ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በዩክሬን በርዲቺቭ የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ መርተዋል 

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በዩክሬን ለሰላም ጸሎት አቀረቡ

በዩክሬን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በበርዲቺቭ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ መቅደስ ውስጥ እሑድ ሐምሌ 14/2016 ዓ. ም. የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መርተዋል። ዩክሬንን እንዲጎበኟት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላኩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለመጡት ምዕመናን ባደረጉት ስብከት፥ “ክፋት የበላይ ቢመስልም እምነታችሁን ማጣት አይገባም በማለት አበረታትተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በዩክሬን ከሐምሌ 12-17/2016 ዓ. ም. ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፣ በርዲቺቭ በሚገኘው የቀርሜሎስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ባሳረጉበት ጊዜ ባሰሙት ስብከት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና የዩክሬን ሕዝብ የሰላም ጥሪን በድጋሚ አቅርበዋል።

በበርዲቺቭ የሚገኘው የቀርሜሎስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በአገሪቱ ከሚገኙ የመንፈሳዊ ጉዞ ወይም የንግደት መዳረሻዎች መካከል አንዱ ነው። የመስዋዕተ ቅዳሴውን ሥነ-ሥርዓት በዝማሬዎች ያደመቁት ምዕመናኑ ለብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በመስዋዕተ ቅዳሴው መካከል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የለመኑት ምእመናኑ ለሁለት ዓመት ተኩል ለሚጠጋ ጊዜ በጦርነት ሲሰቃይ የቆየው የዩክሬን ሕዝብ በናፍቆት ሲጠብቀው የቆየውን የሰላም ስጦታን እንደሚያገኙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ምንም ነገር እንደሌለ ደግመው በማረጋገጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዩክሬን ሕዝብ ስቃይ እንደሚጋሩት እና ያላቸውንም አባታዊ ወዳጅነት አረጋግጠዋል።

ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም!
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በዩክሬንኛ ቋንቋ ባሰሙት ስብከት፣ የአምልኮ ቦታውን ታሪክ የሚያመለክተውን የመጀመሪያውን ተዓምር አስታውሰው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1627 የኪየቭ እና የዚቶሚር ግዛቶች አስተዳዳሪ የነበረው ጄናስ ታይስኪቪች ከታርታር ጋር በተደረገው ጦርነት ተማርኮ በሰንሰለት መታሰሩን እና ከእስራት ነፃ የሚወጣ ከሆነ ለእግዚአብሔር እና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር የሚሆን መልካም ነገር ለማድረግ ቃል እንደገባ እና አንድ ቀን በእንቅልፍ ላይ ሳለም በሕልሙ አንዳንድ ያልታወቁ ገዳማዊያን እርሱ ከእስር እንዲፈታ ወደ እግዚአብሔር እና ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎት ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።

በበርዲቺቭ የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት
በበርዲቺቭ የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት

ከእስር ከተፈታ ከሦስት ዓመታት በኋላ በሕልሙ ያያቸው ገዳማውያኑ በሉብሊን የሚገኙ የቀርሜሎሳውያን ማኅበር አባላት መሆናቸውን ተገንዝቦ በበርዲቺቭ ገዳም ቤተ ክርስቲያን እንዲሠራላቸው መወሰኑን እና ቤተ ክርስቲያኗ እንደ ጎሮጎሮሳውያኑ በ1642 መባረኳን አስታውሰው፥ በሮም በሚገኝ የእመቤታችን ባዚሊካ ውስጥ የሮም ነዋሪዎች ጠባቂ ተብላ የምትታወቅ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ምስል ቅጂ በመሠዊያው አካባቢ በከፍታ ሥፍራ መቀመጡን እና የምስሉን ቅጂ ቀደም ሲል ከቤተሰቡ ዘንድ ያቆየው የአካባቢዎቹ አስተዳዳሪ ጄናስ ታይስኪቪች፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1647 ለቤተ ክርስቲያኑ በስጦታ ማበርከቱን እና በምስሉ ፊት ቀርበው በመጸለይ ከሕመማቸው የተፈወሱት የኪዬቭ ከተማ ጳጳስም ተአምረኛ ቅዱስ ምስል እንደሆነች ማወጃቸውን አስታውሰዋል።

እግዚአብሔር ልብን እንዲለውጥ መጸለይ ይገባል!
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የዩክሬን ቤተ ክርስቲያን ሳታቋርጥ በጸሎት መበርታት እና ትንቢታዊት እንድትሆን አደራ ብለው፥ እግዚአብሔር አምላክ ከመንገዳቸው ወጥተው ለትዕቢታቸው ባሪያ የሆኑትን፣ ዓመፅን እና ሞትን የሚዘሩትን፣ ክብራቸውን የሚረግጡትን ሰዎችን ልብ እንዲለውጥላቸው፣ የድንጋዩን ልብ አውጥቶ የሥጋን ልብ እንዲሰጣቸው መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በርዲቺቭ የሚገኝ የቀርሜሎስ እመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ
በርዲቺቭ የሚገኝ የቀርሜሎስ እመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ

ዘወትር በእግዚአብሔር መታመን ያስፈልጋል!
የዩክሬን ምዕመና በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እና ተስፋ እንዳይቆርጡ ብርታትን የተመኙት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “በተለይ ክፋት የበላይ በሚመስልበት በዛሬው ዓለም፣ ጦርነቱ ያስከተለው ውድመት እና የሰለባዎቹ ስቃይ በመለኮታዊ ቸርነት ላይ ያለንን እምነት ሲያዳክም፣ ለጸሎት የተዘረጉ እጆቻችን ከዛሉ ከእንግዲህ ለመጸለይ እንኳን ጥንካሬ አይኖረንም” ብለው፥ የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስ መመልከት እንደሚገባ፥ ኃጢአት ያሸነፈ ከመሰለበት ከስቅለተ ዓርብ በኋላ ብሩህ የፋሲካ ጎህ መቅደዱን በማስታወስ፥ “አንድ ሰው የትንሳኤውን አድማስ ለማየት በሚታገልበት ጊዜ ሞት ስልጣን ሊኖረው አይችልም” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

ለእመቤታችን አማላጅነት የቀረበ ጸሎት
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በስብከታቸው ማጠቃለያ፥ “በግል መስቀሎቻችን መካከል ከጎናችን የምትቆም እና ወደ ትንሳኤው የምትመራን የኢየሱስ ክርስቶስ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አለች” ብለዋል።

በቤርዲቺቭ የእግዚአብሔር እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ላይ ያሰላሰሉት ብጹዕነታቸው፥ የርህራሄ እና የፍቅር ምልክት እንደሆነችም አስረድተው፥ እርሷ ብርሃን የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የንጋት አብሳሪ እንደሆነች፥ በሐዘን መካከል መጽናናትን ለመስጠት እና አስተማማኝ መሸሸጊያ ለመሆን መዘጋጀቷን ከተናገሩ በኋላ የመደምደሚያ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በስብከታቸው መደምደሚያ፥ “በእግዚአብሔር የተባረክሽ እናታችን ማርያም ሆይ! ሕጻናት እና ወጣቶች ሰላም እና አስተማማኝ የወደፊት ሕይወት እንዲኖራቸው፣ ቤተሰቦች የፍቅር ቦታ እንዲሆኑ፣ አረጋውያን እና ሕሙማን በመከራቸው መጽናናትን እና እፎይታን እንዲያገኙ፣ አገራቸውን ከአደጋ የሚከላከሉትን ከክፋ እንዲተርፉ፥ የጦር እስረኞች ወደ ዘመዶቻቸው በሰላም እንዲመለሱ እና የጦርነት ተጎጂዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዲገቡ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል

 

22 July 2024, 16:53