ካርዲናል ሆሌሪች፥ የሲኖዶሳዊነት ውይይቶች ያስገኟቸውን የመጀመሪያ ፍሬዎች መነሻ ማድረግ እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የአውሮፓ ኅብረት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች፥ የሲኖዶስ ጉባኤ በሲኖዶሳዊነት ላይ ካካሄደው ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ የተገኘውን አዲሱ የተግባር ሠነድ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
የቫቲካን ዜና አገልግሎት አዲሱ የተግባር ሠነድ የያዛቸውን አንዳንድ ጭብጦች በጥልቀት ተመልክተው ማብራሪያ እንዲሰጡበት የጠየቋቸው የ16ኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች፥ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በወንድ እና ሴት ምእመናን የጋራ ኃላፊነት፣ በቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት፣ በጋራ ጥምቀት አማካይነት ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ጋር የሚደረገውን የኅብረት ጉዞን በማስመልከት አዲሱ የተግባር ሠነድ በያዛቸው ጭብጦች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የተግባር ሠነዱ የያዛቸው የመጀመርያ ምዕራፍ ማጠቃለያ ጭብጦች መኖሩን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች፥ በዚህ የመጀመሪያ ምዕራፍ የተግባር ሠነድ በኩል የአብያተ ክርስቲያናት ምላሾች መገኘታቸውን ገልጸው፥ በተግባር ሠነዱ ውስጥ ሥነ-መለኮታዊ አስተያየቶች መካተታቸውንም ገልጸው፥ እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ የተግባር ሠነዱ የያዛቸው ጭብጦች እንጂ የሲኖዶሱ የመጨረሻ ውጤቶች አለመሆናቸው አስረድተዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ በተካሄደው የሲኖዶሳዊነት ውይይት ላይ አባላቱ ሃሳባቸውን ከገለጹ በኋላ የተዘጋጀው የተግባር ሠነድ፥ በሲኖዶሳዊነት ላይ የሚደረጉ አስፈላጊ ውይይቶችን ለማበረታታ የቀረበ እንደ ነበር አስረድተዋል።
ቤተ ክርስቲያን በተልዕኮዋ ሲኖዶሳዊት እንዴት መሆን እንደምትችል የቀረበው ጭብጥ አስፈላጊ እና ጠቃሚ እንደ ሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች፥ ቤተ ክርስቲያን በተልዕኮ ላይ እንደሆነች ተናግረው የጥምቀትን ምስጢር የተቀበሉት ሰዎች በሙሉ ወንጌልን ለዓለም ለማወጅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት የተልዕኮ ሚና እንዳለባቸው እና “ይህም የእኛ ተግባር ነው” በማለት አስረድተዋል።
የሲኖዶሱ ተወካዮች ብቻ ሳንሆን በተለያዩ መንገዶች ባለፉት ሦስት ዓመታት የሲኖዶሳዊነትን ምንነት የተገነዘቡት እና የተለማመዱት የእግዚአብሔር ሕዝቦች በሙሉ የሲኖዶስ ፍሬዎች እንዳሉ እና እነዚህም ፍሬዎች ለወንጌል ተልዕኮ የሚያዘጋጃቸው መሆኑን ተናግረዋል።
“በእርግጠኝነት ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክኅነት ብቻ የምትወሰን አይደለችም” ያሉት የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች፥ “ቤተ ክርስቲያን የተጠመቁት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሁሉ ናት” ብለዋል። ሴት እና ወንድ ምዕመናን፣ ሁሉም ወንጌልን ለማወጅ እና ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት በእግዚአብሔር የተጠሩት ናቸው በማለት አክለዋል። ስለዚህ ሁሉም ወንጌልን በመስበክ የጋራ ኃላፊነት አለብን ብለዋል። ይህ ማለት ደግሞ የተቀቡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን፣ ብጹዓን ጳጳሳትን እና ካኅናትን ይተዋል ማለት ሳይሆን የጥሪያቸውን ትርጉም በሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያገኙታል ብለዋል።
በወንድ እና ሴት ምእመናን መካከል ያለውን ተሳትፎ እና የጋራ ኃላፊነት በማስመልከት ሲናገሩ፥ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምንም ልዩነት እንደሌለ፥ በመንበረ ታቦት ዙሪያ የሚቀርቡ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባባት አገልግሎት እና በአዲሱ የትምህርተ ክርስቶስ ማስተማር አገልግሎት መመሪያ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሴቶች እና ለወንዶች እኩልነት የአገልግሎት ዕድል መክፈታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች ገልጸዋል።
በመላው ዓለም ያልተነሳ በመሆኑ የሴቶች የክህነት ሹመት ጉዳይ ሲኖዶሱ እንዳልተመለከተው የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ አንዳንድ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በሴቶች የዲቁና አገልግሎት ላይ ጥያቄ ባነሱበት ወቅት በዚህ ነጥብ ላይ ሥነ-መለኮታዊ ጥናት እንዲያደርግ ተልዕኮ የተሰጠው ምክር ቤት መቋቋሙን ገልጸው፥ ዲቁና ምን እንደሆነ የበለጠ ለመረዳት፥ ዲቁና በክኅነት የአገልግሎት ሹመት መሳተፍ ሳይሆን ከቤተ ክርስቲኦያን የአገልግሎት ዓይነቶች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል።
ወደ ፊት የክኅነት አገልግሎት ሹመት ለሴቶች ይሰጥ እንደሆነ የተጠየቁት የ16ኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች፥ ጉዳዩ የሂደቱ አካል እንደሆነ ገልጸው ነገር ግን ሁሉም ሂደቶች በዚህ የሲኖዶሳዊነት ውይይት ወቅት ተፈጻሚ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ የለበትም ብለው፥ ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊነት ጎዳና ላይ እንደምትጓዝ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ በታሪክ ሂደት በሲኖዶሳዊነት መንገድ እንደሚመላለስ እና መልስን የሚሹ ሌሎች ጥያቄዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
“እኛ የተጠመቅን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከሆንን፥ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የክርስቲያን ማኅበረሰቦች ዘንድም ጥምቀት አለ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች፥ “እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት እናከብራለን፣ እንወዳቸዋለንም” ብለው፥ “በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥም መንፈስ ቅዱስ ሥራውን እየሠራ እንደሚገኝ እናያለን” ብለዋል።
ስለዚህ ወንጌልን ለዓለም መመስከር የሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የተለመደ ተግባር ነው ብለው፥ በልዩነታችን መካከል ሆነን በአንድነት ወንጌልን ለዓለም መስበክ አለብን ብለዋል። በዚህ ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ውስጥ ከሌሎች የክርስትና ቤተ እምነቶች የተውጣጡ ልዑካን ግልጽ በመሆን መሳተፋቸውን እና ጉባኤውንም ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው መመልከታቸውን የ16ኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች በቫቲካን ሐምሌ 2/2016 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።