የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ልዩ መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ፤ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ልዩ መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ፤ 

ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ካቶሊክ ምዕመናን የእግዚአብሔር ስጦታዎችን ለሌሎች እንዲያካፍሉ አሳሰቡ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ በአሜሪካ ኢንዲያናፖሊስ ከረቡዕ ሐምሌ 10-14/2016 ዓ. ም. ድረስ ሲካሄድ የቆየውን 10ኛውን ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ዘግተዋል። ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ለቅዱስ ቁርባን እና ለሚስዮናዊነት አዲስ ቁርጠኝነት እንዲኖር ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዮሐ. 15:4 ላይ “በእኔ ኑሩ” በሚለው የብሔራዊ ቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ጭብጥ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮ የአብ ስጦታ እንደሆነ ተናግረው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሌሎች እንዲሆን ከአብ ዘንድ እንደተላከ፥ ሥጋውን እና ደሙን ለዓለም ድነት እንዳቀረበ እና ይህም በቅዱስ ቁርባን ስጦታ እንደሚጠቃለል አስረድተዋል።

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ዘንድሮ በአሜሪካ ኢንዲያናፖሊስ ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴን እሁድ ሐምሌ 14/2016 ዓ. ም. መርተዋል። ብጹዕነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ምእመናን ሕይወታቸውን እና ዓለምን በስኬቶቻቸው ሳይሆን ከእግዚአብሔር በሚያገኙት ስጦታ መመልከት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ምዕመና እራሳቸውን፣ ሌሎች ሰዎችን፣ ቁሶችን፣ ሥራዎችን፣ ማኅበረሰብን፣ ሁነቶችን እና ፍጥረትን በስጦታ አድማስ የሚመለከቱ እንደሆነ ጠይቀው፥ ይህን አመለካከት ማጣት የሚስዮናዊነት ቅንዓት ወደ ማጣት ሊያደርስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የሕያው ኢየሱስ ክርስቶስ ስቃይ
ብፁዕ ካርዲናል ታግል በዮሐ. ምዕ. 6 ላይ እንደተገለጸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስን የተውት የደቀ መዛሙርትን አስቸውጋሪ እውነታ አስታውሰው፥ የቤተ ክርስቲያን ድርጊት አንዳንድ ጊዜ ለዚህ አስተዋጽኦ ማድረጉን እንዲመረምሩ ጋብዘዋል። “የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሆንን እኛ ሌሎች ሰዎች ከኢየሱስ እንዲለዩ አስተዋጽኦ ልናደርግ እንችላለን ወይ?” በማለት ጠይቀው፥ በቅዱስ ቁርባን እና በለውጥ ኃይሉ ላይ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ሊኖረን እንደሚገባ አጥብቀው ጠይቀው፥ በተጨማሪም “ከማኅበረሰቡ እንደተገለሉ የሚሰማቸው ድሆች፣ ስደተኞች እና አረጋውያ የክርስቲያን ማኅበረሰብ አካል መሆናቸው እንዲሰማቸው ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ለቅዱስ ቁርባን ሚስዮናዊነት የቀረበ ጥሪ
“ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መቆየትን የሚመርጡት በሙሉ በእርሱ ለመላክ ፈቃደኞች መሆን አለባቸው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ታግለ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ለራሳችን ብቻ ማድረግ እንደሌለብን አሳስበው፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ለግሉ ማድረግ ደቀመዝሙርነት ሳይሆን ነገር ግን ራስ ወዳድነት ነው” ብለው፥ ምእመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉትን ፍቅር እና ርኅራኄ ለደካሞች፣ ለጠፉት እና ለተለያዩት እንዲያካፍሉ አሳስበዋል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከ መልዕክት
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ቡራኬ እና ጸሎት ለጉባኤው ተካፋዮች ያስተላለፉት ብፁዕ ካርዲናል ታግለ፥ “የጉባኤው ተሳታፊዎች ከሰማያዊው ምግብ የሚያገኙትን ዓለም አቀፋዊ ስጦታዎች ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ለሌሎች እንደሚያካፍሉ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮ በአሜሪካ ኢንዲያናፖሊስ ሲካሄድ የቆየው የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ፥ ስብከታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የሰበካ ካኅን በነበሩበት ጊዜ የሆነውን ታሪክ በማስታወስ ቅዱስ ቁርባን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል።

ለየት ያለ የቅዱስ ቁርባን አክብሮት በሁሉም አጋጣሚዎች እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንድትገኝ ያደረጋትን ሴት ምዕመን ያስታወሱት ብጹዕነታቸው፥ ላሳየችው ቁርጠኝነት ካመሰገኗት በኋላ ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩት ቤተሰቧን እንድታመሰግናቸው በጠየቋት ጊዜ፥ “ለቅዱስ ቁርባን ያለኝ አክብሮት ከቤተሰቤ ለመራቅ ነው” ማለቷን ተናግረዋል።

“ካህን ወይም ዲያቆን በመስዋዕተ ቅዳሴው ማጠቃለያ ላይ ‘በክርስቶስ ሰላም ሂዱ!’ ሲል የምትሰሙት፥ “የሰማችሁትን፣ የዳሰሳችሁትን እና የቀመሳችሁትን ለሌሎች አካፍሉ” ማለቱ እንደሆነ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ
ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግሌ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ
22 July 2024, 16:36