ቅድስት መንበር በአዕምሯዊ ንብረት ላይ የተደረገውን አዲስ ስምምነት በጸጋ ተቀበለች
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ፥ በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት (WIPO) አባል ሀገራት ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፥ አዲሱን ታሪካዊ ስምምነት በደስታ ተቀብለው “ትልቅ እርምጃ” ብለውታል።
ስምምነቱ ምንን ያካትታል?
የዓለም አቀፍ አእምሯዊ ንብረት ድርጅት (WIPO) አባል አገራት ያደረጉት ስምምነት በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ ያጸደቁትን አዕምሯዊ ንብረትን፣ የጄኔቲክ ሃብቶችን እና ተዛማጅ ባሕላዊ እውቀቶችን የሚያካትት ነው።
ስምምነቱ የፈጠራ ሥራዎቻቸው በዘረመል ሃብቶች እና በተዛማች ባህላዊ እውቀት ላይ ለተመሠረቱ የፈጠራ ባለቤትነት አመልካቾች በዓለም አቀፍ ሕግ አዲስ መስፈርት ያዘጋጀ፥ እና ከአሥር ዓመታት በላይ ጊዜ ውስጥ የመጀመርያው ሲሆን፥ እንዲሁም የዘረመል ሃብቶችን እና ባህላዊ እውቀትን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከተ ስምምነት እንደሆነ ተነግሯል።
በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት (WIPO) ዋና ዳይሬክተር እንዳሉት፥ ስምምነቱ የአዕምሯዊ ንብረት ፈጠራ ሥርዓትን በማበረታት የሁሉንም አገራት እና ማህበረሰቦች ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ይበልጥ አሳታፊ በሆነ መንገድ እየተሻሻለ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል።
"ጠቃሚ እርምጃ ነው"
የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ ለ 65 ኛው ተከታታይ ዓለም አቀፍ አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት አባል አገራት ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፥ ስምምነቱ ወደ ፊት በመጓዝ ላይ ለሚገኝ አዕምሯዊ ንብረት ሥርዓት ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ገልጸው፥ የአካባቢው ተወላጆች እና ማኅበረሰቦች ተሳትፎን፣ የሚኖሩባቸውን ልዩ ባሕላዊ እና ሕጋዊ ሁኔታዎችን በማገናዝብ የምሰጥውን ትኩረት ቅድስት መንበር እንደምታደንቀው ገልጸዋል።
ሊቀ ጳጳሱ አክለውም ስምምነቱ “በባህላዊ እውቀት እና መግለጫዎች ላይ የሚደረገውን ድርድር በዲፕሎማሲያዊ ደረጃ ለማበረታታት ይረዳል ብለዋል። ከዚህም በላይ ስምምነቱ የተደረሰው በመግባባት ላይ ተመሥርቶ በመሆኑ ቅድስት መንበር ወሳኝ አድርጋ ትመለከተዋለች ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ባሌስትሬሮ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ቅድስት መንበር ከዓለም አቀፍ አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ጋር በመተባበር ዓላማውን ወደፊት ለማራመድ የሚደረገውን ገንቢ ውይይት ለማዳበር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠው፥ ይህም ቅድስት መንበር የተቀናጀ የሰው ልጅ ዕድገትን ለመደገፍ የሰጠችው የሰፊ ቁርጠኝነት አካል ነው ብለዋል።