ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ፥ የኢዮቤልዩ በዓል በችግር ወቅት የተስፋ መንገድ እንደሚሆን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ተስፋ ሌላውን አያሳዝንም” በማለት ይፋ ያደረጉትን የግል ሠነድ መሠረት በማድረግ በኅብረት እና በነጻነት ዙሪያ በተካሄደው የሪሚኒ ጉባኤ ላይ ተስፋ እና ይቅር ባይነት በሚሉት ርዕሦች ላይ ተወያይተው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 የሚከበረውን የኢዮቤል መሪ ሃሳብን አስተጋብተዋል። “ያለ ተስፋ የሕይወትን ምንነት መረዳት አንችልም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፊዚኬላ፥ ተስፋ ለክርስቲያናዊ ሕይወት አስፈላጊ እንደሆነ፥ ከእምነት እና ከበጎ አድራጎት ጋርም የም ዕመናኑን የአኗኗር ዘይቤ እንደሚወክል አስረድተዋል።
ወደ ተግባርነት የሚለወጥ ተስፋ
የኢዮቤልዩ መልዕክት በዋናነት በሁለት ነገሮች አንድነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ፥ እነርሱም ተስፋ እና ተጨባጭ የሆኑ የተስፋ ምልክቶችን የመስጠት እና የመሳተፍ ችሎታዎችን በተግባር ላይ ማዋል እንደሆኑ አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፥ “ተስፋ የመላውን ቤተ ክርስቲያን እና የሰውን ልጅ የግል ጉዞ የሚያካትት በመሆኑ በተለይ በእንዲህ ባለ የዕለት ተዕለት ግፍ በበዛበት ዘመን መንፈሳዊ ነጋዲያን ተብለን የምንጠራው ለዚህ ነው” ብለዋል።
የኃጢአት ስርየት የእግዚአብሔር ይቅርታ ነው
በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ቀጥለውም “የኃጢአት ስርየት ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ነጻ ስጦታ እንደሆነ እና የኢዮቤልዩ በዓልም ለእኛ የተሰጠ ታላቅ የይቅርታ አዋጅ ነው” ሲሉ አክለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግል ሐዋርያዊ ሠነዳቸው ላይ ይፋ ያደረጉትን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊዚኬላ አስታውሰው፥ ይቅር መባባል ያለፈውን የሚለውጥ ሳይሆን ነገር ግን መጭውን ጊዜ በተሻለ ሁኔታ እንድንኖር እንደሚረዳ እና ወደ ፊት ለመመልከት አስፈላጊ አቅጣጫ የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል።
“ቂም፣ ግፍ እና በቀል ባለበት ዘመን ኢዮቤልዩ የእግዚአብሔርን ታላቅ ስጦታ ያስታውሰናል” በማለት አጽንዖት ሰጥተው፥ “ይቅርታ የኃጢአትን ስርየት የሚያስገኝ ጸጋ እንጂ ድል መንሳት እንዳልሆነ አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ “የእግዚአብሔርን ምሕረት የምናገኘው በክርስትና ሕይወት በምንፈጽማቸው መንፈሳዊ ንግደት፣ በቅዱስ በር በኩል በማለፍ፣ እምነትን በመመስከር እና በቸርነት ሥራችን ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
የወንጌል ውበት
በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በስብሰባቸው ማጠቃለያ ላይ ከኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅት ጋር እየተካሄደ ያለውን ታላቅ ሥራ ከኦሎምፒክ ውድድሮች ጋር በማነፃፀር ከመድረኩ ጀርባ ሁል ጊዜ የማይታይ ከፍተኛ ጥረት መኖሩን አስረድተዋል።
በልብ ውስጥ ያለውን ፍላጎት ይህም ቤተ ክርስቲያን በኢዮቤልዩ በዓል በኩል ወንጌልን ወደ ሁሉም ሰው ዘንድ የማድረስ ውበት እና ሃላፊነት የበለጠ እርግጠኛ መሆን እንደምትችል እና የኢዮቤልዩ በዓል ልዩ የወንጌል መግለጫ መንገድ ነው” በማለት አስረድተዋል።
የሮም ከንቲባ የኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅት
የኢዮቤልዩ ኮሚሽነር እና የሮማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሮቤርቶ ጓልቲየሪ ስለ ኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት በማስመልከት በቪዲዮ መገናኛ በኩል እንደተናገሩት “ከፍተኛ ዝግጅትን የሚጠይቅ አድካሚ ሥራ ቢሆንም መንፈሳዊ ዕድልም ነው ሲሉ ተናግረዋል። የጣሊያን ዋና ከተማ ሮምን ውብ፣ ቀልጣፋ እና አካታች እንድትሆን ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጠቆሙት የአብሮነት፣ የመደመር፣ ፍጥረትን የመንከባከብ እና ሁሉንም ሰው ከመቀበል ግዴታዎች ጋር የሚጣጣሙ እሴቶችን ለማረጋገጥ ዕድል የሚሰጥ ጥሩ መንገድ ነው” ብለዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያን 2025 ዓ. ም. በሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት ሠላሳ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ምዕመናን፣ በቀን ከ 100,000 የሚበልጡ ምዕመናን ወደ ሮም እንደሚገቡ ከንቲባው ገልጸው፥ ሮም እንግዶቿን ተቀብላ ለማስተናገድ መዘጋጀቷንም ገልጸዋል።