ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን እና የኢራኑ ፕሬዝዳንት ፔዝሽኪያን በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ሰኞ ነሐሴ 6/2016 ዓ. ም. ማለዳ ከኢራኑ እስላማዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ጋር በስልክ ተገናኝተው ተወያይተዋል። ውይይታቸውን በማስመልከት የቅድስት መንበር መግለጫ ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፥ ብጹዕነታቸው በአዲሱ ፕሬዝደንት የስልጣን ዘመን መጀመሪያ ላይ መልካምን መመኘታቸውን እና በጋራ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በመካከለኛው ምሥራቅ እየተከሰተ ያለው ነገር ቅድስት መንበርን በእጅጉ እንዳሰጋት፣ እየተካሄደ ያለው አሳሳቢ ግጭት በማንኛውም መንገድ እንዳይስፋፋ እና በምትኩ ለውይይት፣ ለድርድር እና ለሰላም ጥረት እንዲደረግ ማሳሰባቸውን አቶ ማቴዮ ብሩኒ ገልጸዋል።
የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሰላም ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጦርነት ምክንያት መከራ እና ስቃይ የሚደርስባቸውን ሕዝቦች ከችግር ለማትረፍ የሰላም ውይይት እንዲደረግ ዘወትር ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል። ባለፈው ነሐሴ 1/2016 ዓ. ም. ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ማጠቃለያ ላይ ለታዳሚዎች ባሰሙት ንግግር በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ሁኔታ በከፍተኛ ስጋት እየተከታተሉት እንደሚገኙ ገልጸው፥ ግጭቱ እንዳይስፋፋ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
“የሰብዓዊ ዕርዳታ ሁኔታ አሳሳቢ እና በዘላቂነት እየቀረበላት ከማይገኝባት ጋዛ ጀምሮ በሁሉም አቅጣጫ በፍጥነት ተኩስ እንዲቆም ጥሪ አቅርበው፥ ጥላቻን በፍቅር ይሸነፋል፣ በቀልም በይቅርታ ይወገዳል” በማለት ተናግረዋል።