የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የእስያና የኦሼንያ ጉብኝት ለተልዕኮአቸው ያላቸውን ታዛዥነት እንደሚገልጽ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለቱ አኅጉራት ውስጥ የሚገኙ አራት አገራትን 40 ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘው ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. ድረስ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያካሂዱባቸው አገራት ኢንዶኔዥያ፣ ሲንጋፖር፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ እና ቲሞር-ሌስቴ መሆናቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፥ የቅዱስነታቸው ረጅም እና አድካሚ ጉብኝት ለአገልግሎት በሚጠራን በእግዚአብሔር ፊት የትሕትና ተግባር እና ለተልዕኮው ያላቸውን ታዛዥነት የሚያሳይ ነው” በማለት አስረድተዋል።
የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትናንሽ መንጋዎች ባሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚያደርጉት ጉብኝት ለዓለማቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ የሆነበትን ምክንያት በመመርመር ለዓለም ሰላም የሚጨነቁትን ሁሉ ሊነካ ይችላል ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ እና በኦሼንያ አኅጉራት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2020 ዓ. ም. መጀመሪያ ላይ የታቀደ እንደነበር ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ነገር ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዕቅዳቸውን እንዲለውጡ በማድረግ መልሰው እንዲዘጋጁ ማድረጉን ገልጸው ይህም “የአባታዊ ቅርበት ምልክት ነው” በማለት አስረድተዋል።
“እነዚህን ረጃጅም ጉዞዎች ማድረግ ይከብደኛል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ይህንን ጥረት መቀበል የትህትና ተግባር እንጂ አቅም እንዳላቸው ለማሳየት እንዳልሆነ አስረድተው፥ “እንደ ምስክርም በጠራን በእግዚአብሔር ፊት የትህትና ተግባር እና ለተልዕኮው መታዘዝ እንደሆነ እቀበለዋለሁ” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በእስያ እና በኦሼንያ አኅጉራት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አንድን አኅጉር መርጠው ሌሎች እንደሚዘነጉ አድርጎ መመልከቱ ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የተሳሳተ ትርጓሜ መስጠት እንደሆነ ብጹዕ ካርዲናል ታግለ ገልጸው፥ ከዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀጥለው በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሉክሰምበርግን እና ቤልጂየምን ለመጎብኘት ማቀዳቸውን፣ ከዚህ በፊትም በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙ ብዙ አገራትን እንደጎበኙ አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ እና በኦሼንያ አኅጉራት ውስጥ በሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶቻቸው ካቶሊክ ምዕመናን በሚገኙበት ቦታ እና ሁኔታ ሁሉ ሊያበረታቷቸው እንደሚፈልጉ ገልጸው፥ በእነዚህ የዓለም አካባቢዎች አብዛኛው ሕዝብ እንደሚኖርም ልብ ልንል ይገባል ብለዋል። እስያ ከዓለም ሕዝብ ሁለት ሦስተኛው የሚኖርባት አኅጉር እንደሆነች የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ድሆች እና ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበሉ መሆናቸውን ገልጸው፥ በጦርነት፣ በስደት እና በግጭት መካከል እንኳ ቢሆን በድሆች መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን የማየት እና ወንጌልን የመቀበል ምኞት እንዳለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያውቃሉ ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በእስያ እና በኦሼንያ አኅጉራት ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማድረጋቸው በፊት የአገራቱ አብያተ ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆኑ ሲቪል ባለስልጣናት እና የፖለቲካ መሪዎችም አገራቱን እንዲገኙ ጥያቄ ማቅረባቸውን ብጹዕ ካርዲናል ታግለ አስታውሰው፥ ባለስልጣናቱ አገሮቻቸውን እንዲጎበኙላቸው የሚፈልጉት በእምነት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ቅዱስነታቸው በወንድማማችነት መንፈስ የሰው ልጅ አብሮ የመኖር እና ለፍጥረታት እንክብካቤ ጠንካራ ምልክት ሆነው በመቆየታቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
በወቅቱ የእምነት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተዳዳሪ በነበሩት በብፁዕ ካርዲናል ኢቫን ዲያስ ግብዣ መሠረት በፓፑዋ ኒው ጊኒ በሚገኝ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ በሁለት ወራት ውስጥ የፓፑዋ ኒው ጊኒ ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤቶችን እና የሰለሞን ደሴቶችን መግብኝታቸውን ገልጸው፥ በተጨማሪም ኢንዶኔዥያ እና ሲንጋፖርን እንደጎበኟቸው፥ ቲሞርን እና ሌስቴን ባይጎበኙትም ነገር ግን ከአገሩ በርካታ ጳጳሳት፣ ካኅናት እና ምእመናን ጋር መገናኘታቸውን አስታውሰዋል።
“እስያ የተለያዩ ዓለማትን ያካተተች አኅጉር ናት” በማለት የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ወደ እስያ አኅጉር ያደረጉት ጉብኝት ለእምሮአቸው እና ልባቸው ሰፊ አድማስ እና ልምድ እንደከፈተላቸው ገልጸው፥ ክርስትና በእስያም ውስጥ በሚያስደንቅ ሁኔታ መያዙን፣ ከመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ብዙ እንደተማሩ እና ወንጌል በተለያዩ የሰው ዘር አውድ ውስጥ የሚገለጽበት እና የተካተተበት እንደሆነ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ታግለ አክለውም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና አጃቢዎቻቸው እንዲሁም ጋዜጠኞች ከዚህ ጉብኝት አዲስ ልምድን እና ከመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ብዙ እንደሚማሩ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
በእስያ እና በኦሼንያ አኅጉራት የክርስቲያን ማኅበረሰቦች በሁሉም ቦታ ማለት ይቻላል በቁጥር አናሳ እንደሆኑ ተናግረው፥ እንደ አውሮፓ ባሉ ቦታዎች ቤተ ክርስቲያን አሁንም በተወሰነ ባሕላዊ፣ ማኅበራዊ እና አልፎ ተርፎም በሲቪሉ ዘንድም ክብር ማግኘቷን ገልጸዋል።
በብዙ የምዕራብ አገራት ቤተ ክርስቲያናት እንደ ትንሽ መንጋ መታየት መጀመሯን ገልጸው፥ በችግር መካከል ትሕትና እንዲኖረን ከፈልግን በምሥራቅ አገራት ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት መመልከት ጥሩ ሊሆን ይችላል ብለው፥ የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመርያዎቹ ሐዋርያት እና ደቀ መዛሙርት ልምድ በእነዚህ አገራት ዘንድ በተደጋግመዋል መታየቱን ገልጸዋል።
ኢንዶኔዥያ በባህል፣ በቋንቋ፣ በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ሁኔታዎች ብዙ ዓይነት ልዩነቶች እንዳላት ብጹዕነታቸው ገልጸው፥ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሙስሊም ነዋሪዎች ያሉባት አገር እንደሆነችም አስረድተዋል። ለኢንዶኔዢያ ካቶሊክ ማኅበረሰብ የተሰጠው ታላቅ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በብዝሃነት አብሮ መኖር እንደሆነ አስረድተው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ወንድማማችነት እና አዲስ ሕይወትን እንደሚያመጣ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
ኢንዶኔዢያ ውስጥ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ የሚገኝበት መሬት ከአገሪቱ የመጀመርያው ፕሬዚደንት የተሰጠ እንደሆነ የተነገራቸው ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ይህ ጠቃሚ መልዕክት በኢንዶኔዥያ ሕዝብ መካከል ሁሉም ሰው እንደ ወንድም እና እህት መታየቱን ያመለክታል ብለዋል።
በእስያ የወጣቶች ቀን ላይ መሳተፋቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ የክርስቲያኖች ቁጥር ዝቅተኛ ከመሆኑ አንጻር በርካታ ወጣት ሙስሊሞችም በዝግጅቱ ከተሳተፉት በጎ ፈቃደኞች መካከል እንደሚገኙ ገልጸው፥ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ክብር በመስጠት ተግባራቸውን የሚወጡ ሁለት ረዳት ሙስሊም ወጣቶችን እንደሰጧቸው ተናግረዋል።
በፓፑዋ ኒው ጊኒ ያለች ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ብትሆንም ነገር ግን ለዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን አንድ ሰማዕት እንዳበረከተች አስረድተዋል። ፓፑዋ ኒው ጊኒ የመድብለ ባህላዊ ሀገር እንደሆነች፣ የተለያዩ ጎሳዎች አልፎ አልፎ እርስ በርስ ቢጋጩም ብዝሃነት ሃብት የሆንባት ሀገር እንደሆነች አስረድተዋል።
በፓፑዋ ኒው ጊኒ ተፈጥሮ ያልተበላሸባቸው ቦታዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ከሁለት ዓመት በፊት አዲስ ካቴድራል ለመመረቅ መሄዳቸውን ተናግረው፥ ለባሕላዊ ጥበባቸው ምስጋና ይግባውና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው እንዲቆዩ እና ከወንዝ በቀጥታ መጠጣት እንደሚችሉ ገልጸው፥ ይህ ልማድ ያደጉ በሚባሉ አገሮች ውስጥ አለመኖሩን ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ኢንዶኔዥያ እና ከዚያም ወደ ቲሞር-ሌስቴ መድረሳቸው አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ እነዚህ ሁለቱ ሀገራት የጦርነት ታሪክ ያላቸው ቢሆኑም አሁን በዘላቂ ሰላም እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
በአገሪቱ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ መንግሥት ቤተ ክርስቲያን የምታካሂዳቸውን የትምህርት አገልግሎቶችን እንደሚደግፍ እና ቤተ ክርስቲያን ራሷ ለነጻነት በተደረገው ጦርነት ወቅት ለሕዝቡ ምልክት ከነበሩት መካከል አንዷ ነበረች እና የቲሞር-ሌስቴ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸው እምነት ለነጻነት በተደረጉት የትግል ዓመታት እንደረዳቸውም ተናግረዋል።
ሲንጋፖር በዓለም ውስጥ ካሉት ሃብታም አገሮች መካከል አንዷ እንደሆነች የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ደረጃ ላይ የደረሰ፣ በቴክኖሎጂ ያደገ፣ ውስን ሃብት ያለው ሕዝብ ቢሆንም በሥርዓት ጭምር ማደጓን ማየት አስደናቂ ነው ብለዋል።
የሲንጋፖር መንግሥት ለሁሉም ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦች ነፃነቶችን ያረጋገጠ እና በሃይማኖት ላይ ጥቃት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል። በአገሪቱ ውስጥ ሰዎች በሰላም እንደሚኖሩ እና ቱሪስቶችም እንዲሁ ከቦታ ቦታ በሰላም እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸው፥ ሁሉም ሚዛን እንዲሆን እና ታሪክ እንደሚያስተምረን ሕግ አስከባሪ አካላት ሕግን ማስጠበቅ ሲገባቸው እሴቶችን እንዳይቃረኑ አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት ታሪክን በተለይም የወንጌል ተልዕኮዎች ታሪክን ከዛሬው ባሕላዊ ዕይታ ጋር የመተርጎም እና ከዘመናት በፊት በኖሩ ሚስዮናውያን ራእያችንን የመጫን አዝማሚያ እና ፈተና መኖሩን የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ይልቁንም ታሪክን በጥንቃቄ መተርጎም እንደሚገባ ተናግረው፥ ሚስዮናውያን የቤተ ክርስቲያን ስጦታዎች እንደሆኑ እና ወንጌልን ወደ ምድር ዳርቻ ሄደው ለህዝቡ እንዲሰብኩ ኢየሱስ ክርስቶስ የጠራቸው እና ለእርሱ የሚታዘዙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አልፎ አልፎ የአገር መሪዎች በቅኝ ግዛት ወቅት ሚሲዮናውያንን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንደሚወስዷቸው የየተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ሆኖም እነዚያ ሚስዮናውያን የተጓዙት ለወንጌል አገልግሎት እንጂ በቅኝ ገዢዎች ለመጨቆን እንዳልነበር አስረድተው፥ ብዙ ካኅናት፣ ሚስዮናውያን እና ምዕመናን ከመንግሥታቸው ትዕዛዝ በተቃራኒ ተንቀሳቅሰው በሰማዕትነት ማለፋቸውን አስታውሰዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት በሃይማኖት ነፃነት ላይ ጥናት መደረጉን የሚገልጽ ጽሑፍ መታተሙን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታግለ፥ ዛቻና ስደት በነበሩባቸው አገሮች የአዲስ ክርስቲያኖች ቁጥር እየጨመረ የመምጣቱ እውነትነት ይፋ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰማዕትነት እውን በሆነበት ቦታ ሁሉ እምነት እንደሚስፋፋ እና አማኝ ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ ሕይወታቸውን እንዲሰጡ የሚያደርጋቸው ይህ ሁሉ ጥንካሬ ከየት ይመጣል? ብለው፥ ይህ የሚያሳየው ወንጌል በተግባር ላይ እንደሆነ፥ በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ ተናግረው፥ የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤታቸው ዓላማ በየአገራቱ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናትን መርዳት እንጂ ከእነርሱ የተለየ አስተሳሰብን ወይም ባህልን ለመጫን አለመሆኑን አስረድተዋል።