አባ ዲዲየር ግራንጂን አባ ዲዲየር ግራንጂን  

አባ ዲዲየር የክኅነት ሕይወት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የትህትና አገልግሎት እንደሆነ ገለጹ

በቫቲካን የስዊስ ዘብ የበሩት እና ባሁኑ ወቅት በክኅነት አገልግሎት ላይ የሚገኙት አባ ዲዲየር ግራንጂን ከስዊስ ዘብነት ወደ ክኅነት ሕይወት ለመምጣ ያደረጉትን ውሳኔ በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የ34 ዓመቱ አባ ዲዲየር ከዜና አገልግሎቱ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልል ውሳኔያቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እና ቤተ ክርስቲያንን በበለጠ መንፈሳዊነት ለማገልገል እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በስዊዘርላንድ ፍሪቦርግ ከተማ ከካቶሊክ እምነት ተከታይ ወላጆች ተወልደው ያደጉት አባ ዲዲየር ግራንጂን ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተሰማቸው ተነሳሽነት ተፈጥሮአዊ እንደሆነ አስረድተዋል። በስዊዘርላንድ የሚሰጠውን የውትድርና ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት አባ ዲዲየር ከ2003 እስከ 2011 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የክብር ዘብ ሆነው አገልግለዋል። የስዊስ ምልምል በመሆን በ21 ዓመት ዕድሜአቸው አገልግሎታቸውን በይፋ የጀመሩት አባ ዲዲየር በአገልግሎት ዓመታት ብዙውን ጊዜ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ከሚመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር በመገናኘት በጥልቅ እምነታቸው ይደነቁ እንደ ነበር ገልጸዋል።

ይህም ለክኅነት ሕይወት መገለጥ አበረታች ሆኖ እንዳገኙት ተናግረው፥ በአገልግሎት ዓመታት ለጸሎት እና ለአስተንትኖ ጊዜን ይሰጡ እንደ ነበር፣ አገልግሎታቸውም ለመንፈሳዊ ብስለት አስፈላጊ ሆኖ እናዳገኙት እና ወደ ክህነት መንገድ በይፋ ለመሸጋገር አስፈላጊ እንደሆነላቸው አስረድተዋል።

ወደ ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ለመግባት የተደረገ ድጋፍ

የአባ ዲዲየር ወላጆች ጠንካራ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ቢሆኑም በልጃቸው የሕይወት ምርጫ መደነቃቸው የሚጠበቅ ነበር። የሆነ ሆኖ ከወላጆቹ የሚሰጠው አዎንታዊ ምላሽ እና ድጋፍ በክኅነት ሕይወት ምርጫ ላይ ቁርጠኝነትን እና መተማመንን የበለጠ አነሳስቶታል። አባታቸው ከማረፋቸው በፊት የሚነግሩት መልዕክትም፥ “ሂድ ቀጥል! ይህ የአንተ መንገድ ነው!” የሚል ነበር።

ዲዲየር ግራንጂን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ
ዲዲየር ግራንጂን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ

በቫቲካን ከተማ እና በስዊዘርላንድ የክብር ዘብ መካከል ያለው ግንኙነት

አባ ዲዲየር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2013 ዓ. ም. የተካሄደውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ሂደት የተከታተሉ ሲሆን፥ በዚህ ወቅት የተገነዘቡት የቤተ ክርስቲያን ታላቅነት እና ተምሳሌትነት እንዲሁም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ትጋት የተመለከቱበት ወሳኝ ወቅት ነብር።

በዚህ ወቅት የተረዷቸው ባሕላዊ እና የአዲስ ግኝት እሴቶች ከደህንነት እና የክብር ዘብ አገልግሎት፣ ከሁለቱም ማለትም ከቫቲካን ከተማ አስተዳደር እና ከጳጳሳዊ የክብር ዘብ ተቋም ዋና ዋና እሴቶች ጋር ይመሳሰላሉ። የስዊስ ዘብ መሆንን እና የክኅነት ሕይወትን ሁለቱን ከሚያገናኛቸው የአገልግሎት እሴቶች መካከል ጥቂቶቹ በግብረ-ገብ መታነጽ እና ወዳጅነት ናቸው። አባ ዲዲየር ራስን ለሌሎች ወይም ለዓላማ ያለማወላወል በቁርጠኝነት ለማቅረብ እንደ መሣሪያ የረዳቸው ጸሎት እንደሆነ በሚገባ አውቀዋል።

በስዊስ ዘብ ውስጥ ሆነ በዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ውስጥ መነሳሳትን ያገኙት፥ “Servus servorum Dei” ወይም የእግዚአብሔር አገልጋዮች አገልጋይ ከሚለው ርዕሥ እንደሆነ አባ ዲዲየር ተናግረው፥ ይህንን ጥንታዊ የሆነውን ጳጳሳዊ ማዕረግ የሚተረጉሙት ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ በታላቅ ትህትና እና በምላሹ ምንም ሳይጠብቁ ለመፈፀም ባላቸውው ፍላጎት እንደሆነ አስረድተዋል።

አባ ዲዲየር ግራንጂን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
አባ ዲዲየር ግራንጂን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ

በቁርጠኝነት ላይ የደረሰ ቀውስ

የፍሪቦርግ ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪ የነበሩት አባ ዲዲየር የእግዚአብሔር አገልጋዮች አገልጋይ የመሆንን ማኅበራዊ ገጽታ ሲገልጹ፣ ከብቸኝነት ስሜት የተነሳ ማግባት አለመቻላቸውን ቢናገሩም ሆኖም ግን ለእምነት ባልንጀሮቹ በሚያቀርቡት አገልግሎት ይህን የቤተሰብ የፍቅር ስሜት ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

አባ ዲዲየር በየጊዜው እያደገ ላለው የምቾት ማኅበረሰብ ያላቸውን ስጋት ሲገልጹ፥ ዓለማዊነት ከመቼውም ጊዜ በልጦ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣ የመስዋዕትነት አስፈላጊነት እና የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነት በክኅነት ሕይወት ብቻ ሳይሆን በትዳር ሕይወትም እየደበዘዘ መምጣቱን ተናግረዋል። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ከእኛ ጋር ስለሆነ ሰዎች የእምነትን ጎዳና ለመከተል ድፍረት እንዲኖራቸው እና ይህን በማድረጋቸው ደስታን እንዲያገኙ አሳስበዋል።

አባ ዲዲየር ግራንጂን የክብር ዘብ በነበሩበት ወቅት
አባ ዲዲየር ግራንጂን የክብር ዘብ በነበሩበት ወቅት

የተስፋ መልዕክት

የክህነት ወይም የምንኩስና ጥሪዎች ቁጥር እየቀነሰ ቢመጣም ሰዎች ልምድ ካላቸው ካኅናት ምክር ማግኘት ይፈልጋሉ። እገዛቸውም ደስታን እና መመሪያን ይሰጣቸዋል። አባ ዲዲየርም በእነዚያ የአገልግሎት ዓመታት ሁሉ በጳጳሳዊ የክብር ዘብ አባልነት ውስጥ የተሰማቸውን ስሜት የሚያጠቃልል መልዕክት ለግሰዋል።

ቤተ ክርስቲያን እና አገልጋዮቿ ሁል ጊዜ ራሳቸውን ለሰው ልጆች አገልግሎት ማዋል እንዳለባቸው ተናግረው፥ “ከቀደመው ሕይወት የሚቀርብን ነገር በሙሉ መቶ እጥፍ ሆኖ ይመለሳል” ሲሉ ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።።

 

08 August 2024, 13:14