ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ 

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ውይይት እና ልማት ለሰላም ቁልፍ እንደሆኑ ገለጹ

በኒውዮርክ ከመስከረም 12-20/2017 ዓ. ም. በመካሄድ ላይ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ለጉባኤው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፥ ውይይት እና ልማት ለሰላም ቁልፍ እንደሆኑ ገልጸዋል። ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የተባበሩት መንግሥታት የ 2024 የከፍተኛ ደረጃ ጉባኤ ዛሬ ብዝሃ-አገራትን ላጋጠማቸው ቀውስ ተስፋን እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት በመግለጽ፥ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ሰላማዊ፣ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ዓለም ለነገው ትውልድ ለማመቻቸት ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወቅታዊ ዓለማቀፍ ግጭቶችን ለመፍታት፣ ፍትህ እና ሰላምን ለማስፈን እና ወደ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስሜት ለመመለስ ውይይት ቁልፍ ሆኖ ቆይቷል ሲሉ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።

“የወደፊቱ ስምምነት”
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊው ንግግር ያደረጉት፥ በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ የጸደቀውን “የወደፊት ስምምነት” በማስመልከት ሲሆን፥ ጉባኤው ከግጭት እስከ የአየር ንብረት ለውጥ እና ሰብዓዊ መብቶችን የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዓለም አቀፍ አስተዳደርን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ታውቋል።

የዓለም መሪዎች ለነገዎቹ ትውልዶች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ሰላማዊ፣ ዘላቂ እና አካታች ዓለም ላይ ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመውሰድ የገቡት ወሳኝ ቃል እሁድ ዕለት በአንዳንድ ሀገራት የማሻሻያ ሃሳብ ቢያቀርቡም በስምምነት ማለፉ ታውቋል።

ተስፋ የተጣለበት ምክንያት
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለጉባኤው ባደረጉት ንግግር፥ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ዝግጅት አሁን ያለውን የብዝሃ-አገራት ቀውስ ለማስወገድ ምንጭ እና የተስፋ ምክንያት መሆን እንዳለበት ጠቁመው፥ “ቀውሱ የተፈጠረው በአገሮች መካከል ያለው መተማመን በመሸርሸሩ ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሳይሰላቹ ዘወትር የሚናገሩት ይህ ተስፋ፣ ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን ወደ ጎን በማድረግ የተሻለ ነገን ለማመቻቸት፣ በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ክብር መርሆዎች፣ የአገራት ሁለንተናዊ ዕድገት፣ እኩልነት እና የሉዓላዊ ክብርን ለማጎልበት የሚደረግ ተስፋ አይደለም” ብለዋል።

ድህነትን ማስወገድ
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በቅድስት መንበር ቅድሚያ የተሰጡባቸውን ሦስት ቁልፍ ጉዳዮችን ሲጠቁሙ፥ ከእነዚህም መካከል ዋነኛው ድህነትን ማስወግድ እንደሆነ ተናግረዋል። ልማት የሰላም ስም መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ድህነትን ማጥፋት የቀጣይ ተግባራት ዋና ግብ ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ማጥፋት
ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ የጠየቁት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በተለይም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዲወገድ በድጋሚ ተማጽነው፥ ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶችን እና የተሳሳቱ የኢኮኖሚ ፍላጎቶችን ወደ ጎን በመተው የሰው ልጅ በሙሉ የሁለንተናዊ ልማት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ጊዜ ማረጋገጥ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎትን “AI” መቆጣጠር

የቴክኖሎጂ ዕድገት የወደፊት አስፈላጊነት በመገንዘብ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ቀጥለውም፥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)ን ወይም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የመቆጣጠር አንገብጋቢ አስፈላጊነትን ጠቁመው፥ የሥነ-ምግባር ጉዳዮችን የሚፈታ አጠቃላይ የቁጥጥር ማዕቀፍ የመረጃ ጥበቃ፣ ተጠያቂነት፣ አድልዎ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት “AI” በሥራ ስምሪት ላይ ያለውን ተጽእኖ ጠቁመው፥ ለሰው ልጅ የዕድገት ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ እንደ ድህነት፣ ግጭት እና ብዝበዛ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት የመጪውን ትውልድ ጥቅም ማጤን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

“የዕድገት ሁኔታን ለማመቻቸት፣ በድህነት፣ በግጭት፣ በብዝበዛ እና በሱሰኝነት ምክንያት የሚመጡትን ጨምሮ ይህን የሚያደናቅፉ በርካታ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አስፈላጊ ሁኔታዎች መሟላታቸውን በማረጋገጥ መልካም የወደፊት ሕይወት ዋስትናን ለሁሉም መሰጠቱ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።


በሥነ-ተዋልዶ ጤና መብቶች እና ጾታ
“የወደፊት ስምምነት” ሠነድ ማጽደቅን በማስመልከት ሲናገሩ፥ በተባበሩት መንግሥታት መግለጫዎች ውስጥ በተለምዶ ጥቅም ላይ በሚውሉ ሁለት አወዛጋቢ ቃላት ላይ ያላቸውን አቋም የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን እነርሱም የሥነ-ተዋልዶ ጤና መብቶች እና ጾታ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዚህ ረገድ ቅድስት መንበር በጋብቻ ያላት አቋም በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ ጋብቻ እንደሆነ ገልጸው፥ በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ፅንስ ማስወረድ መጨመሩን ቅድስት መንበር እንደምትቃወመው በድጋሚ ተናግረዋል። እንዲሁም የሥርዓተ-ፆታ ግንዛቤ በሥነ-ሕይወት ጾታዊ ማንነት (ወንድ ወይም ሴት) ላይ የተመሠረተ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ንግግራቸውን ሲደመድሙ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተባባሱ ካሉ ግጭቶች እና አለመመጣጠን አንፃር ቆራጥ እርምጃ እንዲወሰድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ጥሪ በማስተጋባት፥ በሀገሮች መካከል “እውነተኛ ውይይት” እንዲኖር ጠይቀው፥ “ውይይት ለወደፊት ግባችን አስፈላጊው መንገድ ነው” ብለዋል።

በዚህ ጉባኤ ለመገኘት እሑድ መስከረም 12/2017 ዓ. ም. ኒውዮርክ የገቡት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ እስከ መስከረም 20/2017 ዓ. ም. ድረስ የሚቆየውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 79ኛ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚካፈሉ ታውቋል። በጉባኤው ማጠቃለያም ቅድስት መንበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሆነችበት 60ኛ ዓመት መታሰቢያ መስዋዕት ቅዳሴን እንደሚመሩ ይጠበቃል።

 

 

25 September 2024, 16:16