የሲኖዶስ መሪዎች መጭውን ጠቅላላ ጉባኤ በማስመልከት ዝርዝር መግለጫ ሰጡ የሲኖዶስ መሪዎች መጭውን ጠቅላላ ጉባኤ በማስመልከት ዝርዝር መግለጫ ሰጡ  (Vatican Media)

የሲኖዶስ መሪዎች መጭውን ጠቅላላ ጉባኤ በማስመልከት ዝርዝር መግለጫ ሰጡ

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ እና የሲኖዶሱ ጠቅላይ ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች ከሌሎች የሲኖዶሱ ጽሕፈት ቤተ ተወካዮች አባ ኮስታ እና ሞንሲኞር ባቶኪዮ ጋር ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 17/2017 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደውን ጠቅላላ ጉባኤን በማስመልከት መግለጫ ያውጡ ሲሆን፥ የተመራውም በቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት እንደሆነ ታውቋል ከጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች፣ ከጦር ጉዳተኞች፣ በማኅበረስብ ከተገለሉት እና ከስደተኞች ምስክርነት የሚቀርብበትን ይህን የንስሐ ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በበላይነት እንደሚመሩት ታውቋል። አራት የመድረክ ንግግሮች እና ታዋቂ ሰዎች በሚገኙበት በዚህ የንስሐ ወቅት ከቻይና የሚመጡ ሁለት ብጹዓን ጳጳሳት እንደሚሳተፋ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የሲኖዶስ ጉባኤ የጸሎት ጊዜ እንጂ መደበኛ ስብሰባ የሚካሄድበት መድረክ አይደለም” ያለው መግለጫው  “የምትጸልይ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር አብ እና የመንፈስ ቅዱስን ቃል የምታዳምጥበት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ኃጢአት ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታ የምትለምንበት ጊዜ ነው” ብሏል። ከመስከረም 22 እስከ ጥቅምት 17/2017 ዓ. ም. ድረስ በሮም የሚካሄደውን 16ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሁለተኛ ዙር በማስመልከት የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች ሰኞ መስከረም 6/2017 ዓ. ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሲኖዶሱ ሂደቶች መክፈቻ ላይ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 9/2021 ዓ. ም. ባሰሙት ንግግር፥ “የሲኖዶሱ ዋና ተዋናይ መንፈስ ቅዱስ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው እንደ ነበር ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

የቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አቶ ፓውሎ ሩፊኒ በቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽሕፈት ቤተ በኩል የቀረቡትን የሲኖዶስ አስተዋጽኦዎች አስተዋውቀዋል።

መንፈሳዊ ሱባኤ እና የንስሐ ዋዜማ

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ እንዳብራሩት፣ ልክ እንደ መጀመሪያው ዙር ይህ ሁለተኛው እና የመጨረሻው ሲኖዶሳዊ ጉባኤ የሚጀምረው ከሁለት ቀናት በፊት ማለትም መስከረም 20 እና 21/2017 ዓ. ም. ቫቲካን ውስጥ እንደሚደረግ፣ በዶሚኒካን ካኅን ቲሞቲ ራድክሊፍ እና በነዲክቲያን እናት ኢግናዚያ አንጀሊኒ በሚመሩት አስተንትኖ የሚጀመር መሆኑን ገልጸው፥ በሲኖዶሳዊነት ጉባኤ ወቅት የሚቀርቡ ጸሎቶችን የሚመሩት አባ ማትዮ ፌራሪ ሲሆኑ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን የሚከታተሉት የካማልዶሊ መነኮሳን እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ማክሰኞ መስከረም 21/2017 ዓ. ም. ምሽት ከሱባኤ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የሚቀርበውን የንስሐ ጊዜ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት የሚመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሆኑ ታውቋል። የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን በኅብረት ያዘጋጁት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት፣ የሮም ሀገረ ስብከት፣ ከፍተኛ የገዳማውያን እና ገዳማውያት ኅብረት እና ዓለም አቀፍ የገዳማውያን እና ገዳማውያት ኅብረት እንደሆኑ ታውቋል።

የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ በቫቲካን መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፍ ሲሆን፥ ለሁሉም በተለይም ለወጣቶች ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል። የሲኖዶሱ ጠቅላይ ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች በመግለጫቸው፥ “የቤተ ክርስቲያን መልዕክት ለወጣቶች በአደራ ተሰጥቶአቸውል” ብለው፥ “ወጣቶች በእኛ ኃጢያት እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባለው ኃጢያት ምክንያት ይሰቃያሉ” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው፣ የጦርነት ሰለባዎች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የስደት እና የግድየለሽነት መከራ ተጠቂ ሦስት ግለሰቦች ምስክርነቶችን ያቀርባሉ። ቀጥሎም ተገቢውን ባለማድረግ ወይም ራስን መከላከል በማይችሉ ሰዎች ላይ ለሚደርስባቸው መከራ እና ጉዳት ተጠያቂ ከሚሆኑት መካከል እራሳችንን አንዱ አድርገን ኃጢአቶቻችንን የምንናዘዝበት ጊዜ ይኖራል” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በተለይም የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን በተሳሳተ መንገድ በመጠቀም በሰላም፣ በፍጥረት፣ በአገሬው ነባር ተወላጆች፣ በስደተኞች፣ በሴቶች፣ በቤተሰብ፣ በወጣቶች ላይ የሚፈጸሙ ኃጢአቶች፤ በድህነት እና በሲኖዶሳዊነት ላይ የተሠሩ ኃጢአቶችን የሚናዘዙበት ወቅት እንደሆነ አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መላውን ምዕመን በመወከል ከእግዚአብሔር እና ከሰው ልጆች በሙሉ ይቅርታን በመጠየቅ ሥነ-ሥርዓቱን እንደሚደመድሙ ተነግሯል።

የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ጸሎት

ቫቲካን ውስጥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ያረፈበት ተብሎ በሚነገርበት አደባባይ ዓርብ ጥቅምት 1/2017 ዓ. ም. ምሽት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን ታውቋል። ይህ ቀን ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የተከፈተበት 62ኛ ዓመት የሚከበርበት ዕለት እንደሆነ ታውቋል። በመጨረሻም ጥቅምት 11/2017 ዓ. ም. በረቂቁ የመጨረሻ ሠነድ ላይ ለማስተንተን የሚያግዝ ተጨማሪ የሱባኤ ቀን እንደሚኖር ተነግሯል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ እንደተናገሩት፣ በጉባኤው መካከል በግል የሚደረጉ ጸሎቶች፣ የጋራ ውይይቶች፣ የመደማመጥ፣ የፍቅር እና የወንድማማች ጊዜ እንደሚኖር ገልጸዋል።

ለሁሉም ክፍት የሚሆኑ አራት የንግግር መድረኮች

ሌላው አዲሱ የጉባኤው ገፅታ አራት የነገረ-መለኮት እና የሐዋርያዊ አገልግሎት የንግግር መድረኮች ሲሆን፥ ይህም እውቅና የተሰጣቸው ጋዜጠኞችን ጨምሮ ለሁሉም የጉባኤው ተሳታፊዎች ክፍት ይሆናሉ። ሁለቱ መድረኮች ክፍት የሚሆኑት መስከረም 29 ሲሆን፥ የመጀመሪያው በኢየሱሳውያን ማኅበር ጠቅላይ ቤት ውስጥ የሚካሄድ “የእግዚአብሔር ሕዝብ የተልዕኮ ርዕሥ” የሚል ሲሆን፥ ሁለተኛው “በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የጳጳስ ሚና እና ሥልጣን” በሚል ርዕሥ በቅዱስ አውግስጢኖስ ገዳም ውስጥ የሚዘጋጅ የንግግር መድረክ እንደሆነ ታውቋል። የተቀሩት ሁለት መድረኮች በጥቅምት 6/2017 ዓ. ም.  የሚካሄዱ ሲሆን መሪ ሃሳቦችም “በአጥቢያ እና በኩላዊት ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው የጋራ ግንኙነት” በሚል ርዕሥ በኢየሱሳውያን ማኅበር ጠቅላይ ቤት የሚካሄድ እና “የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተግባር እና የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ” በመል ርዕሥ በቅዱስ አውጎስጢኖስ ገዳም የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነ ታውቋል። እነዚህ መድረኮች የነገረ መለኮት እና የሕገ ቀኖና ሊቃውንትን፣ ብጹዓን ጳጳሳትን እና ሌሎች ምሑራንን የሚያካትቱ በመሆናቸው ሰፊ የውይይት ዕድል እንደሚኖራቸው ታውቋል። የንግግር መድረኩ ለብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት በመስመር ላይም ክፍት እንደሚሆን ተገልጿል።

የጉባኤው ተካፋዮች ቁጥር

የሲኖዶሱ ጠቅላይ ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች እንዳስረዱት፥ በዚህ ሁለተኛ ዙር ጉባኤ ላይ የተሳታፊዎች ቁጥር ከመጀመሪያው ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንደሆነ፥ 272 ብጹዓን ጳጳሳት እና 96 ጳጳሳት ያልሆኑትን ጨምሮ 368 ድምጽ ሰጪ አባላት እንደሚገኙበት አስረድተዋል። በዋናነት ለውጥ የተደረገባቸው 26 ቦታዎች ሲኖሩ፥ ልዩ ጥሪ የተደረገላቸው 8 ግለሰቦች መኖራቸውን፣ የወዳጅነት ግብዣ የተደረገላቸው ልዑካን ቁጥር ከ12 ወደ 16 ከፍ ማለቱን፥ ይህም እህት አብያተ ክርስቲያናት በሲኖዶሳዊነት ጉዞ ላይ ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ እንደሆነ ተናግረው፥ ከቻይና የሚመጡ ሁለት ብጹዓን ጳጳሳት መኖራቸውንም ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች አረጋግጠዋል።

 

17 September 2024, 16:32